“ይህ በእኔ ላይ ለምን ደረሰ? አምላክስ ለምን ፈቀደ?” በብራዚል የሚኖረው የ24 ዓመቱ ሲድና እነዚህ ጥያቄዎች በአእምሮው ይጉላሉ ነበር። የውኃ ላይ ሸርተቴ ሲጫወት በደረሰበት አደጋ ሳቢያ ያለ ተሽከርካሪ ወንበር መንቀሳቀስ የማይችል ሰው ሆነ።

ሰዎች በአደጋ፣ በበሽታ፣ የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣት፣ በተፈጥሮ አደጋ ወይም በጦርነት ምክንያት ለመከራ ሲዳረጉ ወዲያውኑ በአምላክ ቅር ይሰኛሉ። ይህ አዲስ ነገር አይደለም። በጥንት ዘመን የኖረው ኢዮብ በላይ በላዩ የመጣ የመከራ ውርጅብኝ ወርዶበት ነበር። ከዚህ የተነሳ ባለማወቅ አምላክን ተወቃሽ አደረገ፦ “እርዳታ ለማግኘት ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ አንተ ግን አትመልስልኝም፤ በፊትህ ቆምኩ፤ አንተ ግን ዝም ብለህ ታየኛለህ። በጭካኔ በእኔ ላይ ተነሳህ፤ በእጅህ ብርታት አጠቃኸኝ።”—ኢዮብ 30:20, 21

ኢዮብ የመከራው ምንጭ ማን እንደሆነ እንዲሁም ለምን መከራ እንደደረሰበት ወይም አምላክ መከራ እንዲደርስበት ለምን እንደፈቀደ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ደስ የሚለው ነገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደዚህ ያሉ መከራዎች ሰዎች ላይ የሚደርሱት ለምን እንደሆነና እኛ ምን ማድረግ እንደሚኖርብን ይገልጻል።

አምላክ በሰዎች ላይ መከራ እንዲደርስ ይፈልጋል?

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን አስመልክቶ “እሱ ዓለት፣ የሚያደርገውም ነገር ሁሉ ፍጹም ነው፤ መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸውና። እሱ ፈጽሞ ፍትሕን የማያጓድል ታማኝ አምላክ ነው፤ ጻድቅና ትክክለኛ ነው” በማለት ይናገራል። (ዘዳግም 32:4) እውነታው ይህ ከሆነ፣ “ጻድቅና ትክክለኛ” የሆነ አምላክ ሰዎችን ለመቅጣት ወይም ለማንጻት ሲል መከራ ያመጣባቸዋል ብሎ ማሰብ እርስ በርሱ የሚጣረስ አልፎ ተርፎም ለመቀበል የሚከብድ አይደለም?

በተቃራኒው ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ “ማንም ሰው ፈተና ሲደርስበት ‘አምላክ እየፈተነኝ ነው’ አይበል። አምላክ በክፉ ነገር ሊፈተን አይችልምና፤ እሱ ራሱም ማንንም በክፉ ነገር አይፈትንም” ይላል። (ያዕቆብ 1:13) እንዲያውም አምላክ ከጅምሩ ለሰው ልጆች ፍጹም ሕይወት ሰጥቷቸው እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ለመጀመሪያዎቹ ሰዎች ማለትም ለአዳምና ለሔዋን የሚኖሩበት ውብ ስፍራ፣ ለሕይወት የሚያስፈልጋቸውን ነገርና አርኪ ሥራ ሰጥቷቸዋል። አምላክ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም” በማለት ነገራቸው። በእርግጥም አዳምና ሔዋን፣ በአምላክ ቅር እንዲሰኙ የሚያደርጋቸው ምንም ምክንያት አልነበረም።—ዘፍጥረት 1:28

ይሁንና በዛሬው ጊዜ ሰዎች የሚኖሩበት ሁኔታ ከፍጽምና እጅግ የራቀ ነው። እንዲያውም በታሪክ ዘመናት በሙሉ የሰው ዘር አስከፊ ሥቃይ ሲደርስበት ቆይቷል። “ፍጥረት ሁሉ እስካሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በመሠቃየት ላይ እንደሚገኝ እናውቃለን” የሚለው ሐሳብ ፍጹም እውነት ነው። (ሮም 8:22) እንዲህ የሆነው ለምንድን ነው?

በሰዎች ላይ መከራ የሚደርሰው ለምንድን ነው?

በሰዎች ላይ መከራ የሚደርስበትን ምክንያት ለመረዳት ወደኋላ ተመልሰን መከራ እንዴት እንደጀመረ ማየት ይኖርብናል። አዳምና ሔዋን፣ አንድ ዓመፀኛ መልአክ (ከጊዜ በኋላ ሰይጣን ዲያብሎስ ተብሎ ተጠርቷል) ስለገፋፋቸው አምላክ ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ያወጣውን መሥፈርት ሳያከብሩ ቀሩ፤ ይህን ያደረጉት “መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ” እንዳይበሉ የሰጣቸውን ትእዛዝ በመጣሳቸው ነው። ዲያብሎስ የአምላክን ትእዛዝ ቢጥሱ እንደማይሞቱ ለሔዋን በነገራት ጊዜ አምላክን ይዋሻል ብሎ የወነጀለው ያህል ነበር። በተጨማሪም ሰይጣን፣ አምላክ ተገዢዎቹን ጥሩና መጥፎ የሆነውን ነገር የመወሰን መብት እንደነፈጋቸው በመናገር ክስ ሰንዝሯል። (ዘፍጥረት 2:17፤ 3:1-6) ሰይጣን የሰው ዘር ከአምላክ አገዛዝ ነፃ ቢወጣ የተሻለ እንደሚሆን የተናገረ ያህል ነበር። ይህ ሁሉ ነገር አንድ አንገብጋቢ ጉዳይ ይኸውም ‘አምላክ የመግዛት ብቃት አለው?’ የሚል ጥያቄ አስነስቷል።

ዲያብሎስ ከዚያ በኋላም ሌላ አከራካሪ ጥያቄ አንስቷል። ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት በራስ ወዳድነት ተነሳስተው እንደሆነ በመግለጽ ክስ ሰንዝሯል። ዲያብሎስ ታማኙን ኢዮብን በተመለከተ ከአምላክ ጋር ሲነጋገር “እሱን፣ ቤቱንና ያለውን ነገር ሁሉ በአጥር ከልለህ የለም? . . . ሆኖም እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ አጥፋ፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል” ብሎታል። (ኢዮብ 1:10, 11) ሰይጣን በቀጥታ የተናገረው ስለ ኢዮብ ቢሆንም የሰነዘረው ሐሳብ ሰዎች ሁሉ አምላክን የሚያገለግሉት በራስ ወዳድነት ተነሳስተው እንደሆነ የሚገልጽ አንድምታ አለው።

አምላክ መልስ የሰጠበት መንገድ

ለእነዚህ መሠረታዊ አከራካሪ ጉዳዮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት መስጠት የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው? ፍጹም ጥበብ ያለው አምላክ ከሁሉም የተሻለ መፍትሔ አለው፤ መፍትሔው ደግሞ ቅር አያሰኘንም። (ሮም 11: 33) አምላክ ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ለመፍቀድና የማን አገዛዝ የተሻለ እንደሆነ ከውጤቱ እንዲታይ ለማድረግ ወሰነ።

በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ያሉት አሳዛኝ ሁኔታዎች የሰው አገዛዝ ሙሉ በሙሉ ከንቱ መሆኑን በግልጽ ያሳያሉ። በዓለም ላይ ያሉ መንግሥታት ሰላም፣ ደኅንነትና ደስታ ማስፈን የተሳናቸው ከመሆኑም ሌላ ምድር የጥፋት ቋፍ ላይ እንድትገኝ አድርገዋል። ይህ ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ “[ሰው] አካሄዱን እንኳ በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም” የሚለውን መሠረታዊ እውነት ያጠናክራል። (ኤርምያስ 10:23) ለሰው ዘር ዘላቂ ሰላም፣ ደስታና ብልጽግና በእርግጠኝነት ማምጣት የሚችለው የአምላክ አገዛዝ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም ይህ የአምላክ ዓላማ ነው።—ኢሳይያስ 45:18

ታዲያ አምላክ ለሰው ዘር ያለውን ዓላማ ከፍጻሜ የሚያደርሰው እንዴት ነው? ኢየሱስ ተከታዮቹን “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም” ብለው እንዲጸልዩ ማስተማሩን አስታውስ። (ማቴዎስ 6:10) አዎን፣ አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ በመንግሥቱ አማካኝነት ለመከራ መንስኤ የሆኑትን ነገሮች በሙሉ ያስወግዳል። (ዳንኤል 2:44) ድህነት፣ በሽታና ሞት የተረሱ ነገሮች ይሆናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለድሆች የሚያደርገውን ነገር በተመለከተ ‘እርዳታ ለማግኘት የሚጮኸውን ድሃ ይታደገዋል’ ይላል። (መዝሙር 72:12-14) የታመሙትን በተመለከተ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ “በዚያም የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’ አይልም” የሚል ተስፋ ይዟል። (ኢሳይያስ 33:24) ከዚህም አልፎ ኢየሱስ በአምላክ ዝክር ውስጥ ያሉትን ሙታን አስመልክቶ ‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበትና የሚወጡበት ሰዓት ይመጣል’ ብሏል። (ዮሐንስ 5:28, 29) እንዴት ያሉ የሚያስደስቱ ተስፋዎች ናቸው!

አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት መጣል በእሱ ላይ ያደረብንን ማንኛውንም ቅሬታ ለማስወገድ ይረዳናል

የተሰማንን ቅሬታ ማስወገድ

በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው ሲድና አደጋው ከደረሰበት ከ17 ዓመታት በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “ለደረሰብኝ አደጋ ይሖዋ አምላክን ፈጽሞ ተወቃሽ አላደረግኩም፤ መጀመሪያ ላይ ግን ቅር ተሰኝቼበት እንደነበረ አልክድም። አንዳንድ ጊዜ ቅስሜ ስብር ይላል፤ ደግሞም ስለደረሰብኝ የአካል ጉዳት ሳስብ አለቅሳለሁ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ሳጠና አደጋው ከአምላክ የመጣ ቅጣት እንዳልሆነ መረዳት ችያለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሁሉም መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል’ ይላል። ወደ ይሖዋ መጸለዬና የሚያጽናኑኝን ጥቅሶች ማንበቤ በመንፈሳዊ ጠንካራ እንድሆንና ብሩሕ አመለካከት እንድይዝ ረድቶኛል።”—መክብብ 9:11፤ መዝሙር 145:18፤ 2 ቆሮንቶስ 4:8, 9, 16

አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያትና መከራ ያስከተለው ውጤት ሁሉ በቅርቡ እንደሚወገድ ማስታወሳችን በአምላክ ላይ ያደረብንን ማንኛውንም ቅሬታ ለማስወገድ ይረዳናል። አምላክ “ከልብ ለሚፈልጉት ወሮታ ከፋይ መሆኑን” በእርግጠኝነት እናምናለን። በእሱና በልጁ ላይ እምነት የጣለ ሰው ሁሉ ለሐዘን አይዳረግም።—ዕብራውያን 11:6፤ ሮም 10:11