“ማይክን ሳውቀው ብዙ ዓመቴ ነው። ማይክ የይሖዋ ምሥክሮች እምነት ተከታይ ነው። ይሄ ሃይማኖቱ ግን ሁልጊዜ ግራ ያጋባኛል። ይሖዋ የሚባለው ማን ነው? የይሖዋ ምሥክሮች ዓመት በዓሎችን የማያከብሩት ለምንድን ነው? ማይክ ከመናፍቃን ጋር ኅብረት ፈጥሮ ይሆን?”—ቤኪ፣ ካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“ጎረቤቶቼ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በጀመሩ ጊዜ ‘ለመሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለው ስም ምን ማለት ነው?’ የሚል ጥያቄ ተፈጠረብኝ። እንዲህ ዓይነት የሃይማኖት ስም ይኖራል ብዬ አስቤ አላውቅም!”—ዜነን፣ ኦንታሪዮ፣ ካናዳ

“እኔና ባለቤቴ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን የሚመጡት ቤተ ክርስቲያን ባለመሄዳችን በሚሰማን የበደለኛነት ስሜት ለመጠቀም ፈልገው ነው ብለን እናስብ ነበር። እንዲሁም ዋና ዋናዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ፍላጎታችንን ማርካት ካልቻሉ እንደ ይሖዋ ምሥክሮች ያለ ምንነቱ የማይታወቅ ኑፋቄማ ምንም አይጠቅመንም ብለን አሰብን።”—ኬንት፣ ዋሽንግተን፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“እውነቱን ለመናገር ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ማንነትም ሆነ ስለ ዓላማቸው የማውቀው ነገር አልነበረም።”—ሴሲልየ፣ ኤስቤርግ፣ ዴንማርክ

የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት ወይም በአደባባይ ሲሰብኩ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ሲያሠራጩና ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ እንዲማሩ ሲጋብዙ አይተህ ታውቅ ይሆናል። እንዲያውም ይህን መጽሔት የሰጡህ እነሱ ሊሆኑ ይችላሉ። ያም ሆኖ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ማንነት ጥያቄ ሊኖርህ ይችላል። ምናልባት አንተም ከላይ የተጠቀሱት ሰዎች ከተናገሩት ሐሳብ ጋር የሚመሳሰል አመለካከት ይኖርህ ይሆናል።

እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ተፈጥረውብህ ከሆነ መልሶቹን የት ማግኘት ትችላለህ? የይሖዋ ምሥክሮች በእርግጥ ምን ብለው እንደሚያምኑ፣ አገልግሎታቸውን ለማካሄድና የአምልኮ ቦታቸውን ለመገንባት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከየት እንደሚያገኙ እንዲሁም ወደ ቤትህ የሚመጡትና መንገድ ላይ ቀርበው የሚያነጋግሩህ ለምን እንደሆነ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሴሲልየ እንዲህ ብላለች፦ “ኢንተርኔት ላይ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ነገር አንብቤያለሁ። ደግሞም አንዳንድ አሉባልታዎችን ሰምቻለሁ፤ በጭፍን ጥላቻ የተነገሩ ብዙ ወሬዎችንም አዳምጫለሁ። ከዚህ የተነሳ ለይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ አመለካከት አልነበረኝም።” ይሁንና ሴሲልየ ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮችን አነጋግራ ለጥያቄዎቿ አጥጋቢ መልስ አግኝታለች።

አንተስ የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ ላሉህ ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ ብታገኝ ደስ ይልሃል? ከሆነ ለጥያቄዎችህ አጥጋቢ መልስ ሊሰጡህ የሚችሉትንና የዚህ መጽሔት አዘጋጆች የሆኑትን የይሖዋ ምሥክሮችን እንድትጠይቅ እናበረታታሃለን። (ምሳሌ 14:15) ቀጥሎ የቀረቡት ርዕሶች ስለ እኛ ማንነት፣ ምን ብለን እንደምናምንና ስለምናከናውነው ሥራ እንድታውቅ ይረዱሃል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።