በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ነሐሴ 2015

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት መኖር ይችላል?

ስንሞት ምን እንሆናለን?

ስንሞት ምን እንሆናለን?

“ሰው ሲሞት ወደ ሰማይ ወይም ወደ ሲኦል አሊያም ወደ መንጽሔ ይሄዳል ብዬ አስብ ነበር። እርግጥ ወደ ሰማይ የሚያስገባ ጥሩ ነገር እንዳልሠራሁ አሊያም ለሲኦል የሚያበቃ ክፉ ነገር እንዳልሠራሁ አውቃለሁ። በሌላ በኩል መንጽሔ ውስጥ ምን እንዳለ በትክክል የማውቀው ነገር አልነበረም። ሰዎች ሲያወሩ ከሰማሁት ውጭ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለዚህ ጉዳይ የሚገልጽ ሐሳብ አንብቤ አላውቅም።”—ላየነል

“ሰዎች ሁሉ ሲሞቱ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ የሚለውን ትምህርት አውቃለሁ፤ ሆኖም አሳማኝ ሆኖ አላገኘሁትም። ሞት የሁሉም ነገር ፍጻሜ እንደሆነ አድርጌ ስለማስብ ሙታን ምንም ተስፋ እንደሌላቸው ይሰማኝ ነበር።”—ፈርናንዶ

‘ሰው ሲሞት ምን ይሆናል? በሞት ያጣናቸው የምንወዳቸው ሰዎች የሆነ ቦታ ሄደው እየተሠቃዩ ይሆን? ዳግመኛ እናያቸው ይሆን? ከሆነስ እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን?’ የሚሉትን ጥያቄዎች አስበህባቸው ታውቃለህ? እባክህ ቅዱሳን መጻሕፍት ስለዚህ ጉዳይ ምን ብለው እንደሚያስተምሩ ለማስተዋል ሞክር። እስቲ በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሞት ምን እንደሚል እንመልከት። ከዚያም የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ተስፋ እንመረምራለን።

 የሞቱ ሰዎች በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም፤ ከእንግዲህም የሚያገኙት ብድራት የለም፤ ምክንያቱም የሚታወሱበት ነገር ሁሉ ተረስቷል። እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኃይልህ አከናውን፤ አንተ በምትሄድበት በመቃብር ሥራም ሆነ ዕቅድ፣ እውቀትም ሆነ ጥበብ የለምና።” *መክብብ 9:5, 10

በአጭር አነጋገር፣ መቃብር ሰዎች ሲሞቱ የሚያርፉበት ቦታ ሲሆን ቃሉ ምሳሌያዊ ቦታን ወይም ሁኔታን ያመለክታል፤ መቃብር ውስጥ ማሰብም ሆነ መሥራት አይቻልም። ታማኙ ኢዮብ መቃብርን እንዴት ይመለከተው ነበር? ኢዮብ በአንድ ቀን ንብረቱንና ልጆቹን በሙሉ አጣ፤ ከዚያም ክፉኛ የሚያሠቃይ እባጭ መላ ሰውነቱን ወረሰው። አምላክን “ምነው በመቃብር [“በሲኦል፣” የ1954 ትርጉም] ውስጥ በሰወርከኝ” በማለት ተማጽኖ ነበር። (ኢዮብ 1:13-19፤ 2:7፤ 14:13) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢዮብ ሲኦልን የማቃጠያ ቦታ አድርጎ አልተመለከተውም፤ ቢሆን ኖሮ ይበልጥ ወደሚሠቃይበት ቦታ ለመሄድ አይመኝም ነበር። ከዚህ ይልቅ እፎይታ የሚያገኝበት ቦታ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር።

የሞቱ ሰዎች ስለሚገኙበት ሁኔታ ማወቅ የምንችልበት ሌላም መንገድ አለ። በአምላክ መንፈስ መሪነት በተጻፈው በቃሉ ውስጥ የሚገኘውን ከሞት ስለተነሱ ስምንት ሰዎች የሚናገረውን ታሪክ መመርመር እንችላለን።—“ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ስምንት ትንሣኤዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ከስምንቱ ሰዎች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ከሞት ሲነሱ ተድላ ወይም ሥቃይ ወዳለበት ቦታ ሄደው እንደነበር አልተናገሩም። እነዚህ ሰዎች ሲሞቱ እንዲህ ወዳለ ቦታ ሄደው ቢሆን ኖሮ ስለዚህ ጉዳይ ለሰዎች አያወሩም ነበር? ደግሞስ ተናግረው ቢሆን ኖሮ ሁላችንም እንድናነበው በአምላክ መንፈስ መሪነት በተጻፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይካተትም ነበር? በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የትም ቦታ ላይ እንዲህ ያለ ሐሳብ ተመዝግቦ አናገኝም። እነዚህ ስምንት ሰዎች ይህን በተመለከተ ሊናገሩ የሚችሉት ነገር እንደሌለ ግልጽ ነው። ለምን? ምክንያቱም ድብን ያለ እንቅልፍ የወሰዳቸው ያህል ስለነበር የሚያውቁት ነገር አልነበረም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን ለመግለጽ እንቅልፍን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ የተጠቀመበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ታማኙ ዳዊትም ሆነ እስጢፋኖስ ‘በሞት እንዳንቀላፉ’ ተገልጿል።—የሐዋርያት ሥራ 7:60፤ 13:36

ታዲያ የሞቱ ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው? ከዚህ እንቅልፍ መንቃት ይችላሉ?

^ አን.7 በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ “መቃብር” ተብሎ የተተረጎመው ቃል የዕብራይስጡን “ሲኦል” እና የግሪክኛውን “ሐዲስ” ያመለክታል። አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ሲኦል የሚለው ቃል የሞቱ ሰዎች እየተቃጠሉ የሚሠቃዩበት ቦታ እንደሆነ ያስባሉ፤ ይሁንና ይህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የለውም።