“አባቴ ከሞተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ባለቤቴ ሌላ ሴት እንደወደደ ነገረኝ” በማለት ጃኔት ትናገራለች። “ከዚያም ሳይሰናበተን ድንገት ልብሱን ጠቅልሎ እኔንና ሁለት ልጆቼን ጥሎን ሄደ።” ጃኔት ሥራ ብታገኝም ደሞዟ የቤቱን ዕዳ ለመክፈል የሚበቃ አልነበረም። ደግሞም የሚያሳስባት የገንዘብ ጉዳይ ብቻ አይደለም። እንዲህ ብላለች፦ “የወደቀብኝ ከባድ ኃላፊነት የፈጠረብኝ ጭንቀት ብቻዬን ልሸከመው የምችለው አልነበረም። ሌሎች ወላጆች እንደሚያደርጉት እኔም ለልጆቼ ማድረግ ባለመቻሌ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኝ ነበር። ሰዎች ስለ እኔም ሆነ ስለ ልጆቼ ያላቸው አመለካከት አሁንም ያስጨንቀኛል። ትዳሬን ለመታደግ ምንም ጥረት እንዳላደረግኩ አድርገው ያስቡ ይሆን ብዬ እጨነቃለሁ።”

ጃኔት

ጃኔት ስሜቷን ለመቆጣጠርና ከአምላክ ጋር ያላትን ዝምድና ለማጠናከር የረዳት ጸሎት ነው። “በጣም የሚከብደኝ፣ ሁሉም ነገር ጸጥ ረጭ የሚልበትና የሚያስጨንቁኝን ሐሳቦች መቋጨት የማልችልበት የሌሊቱ ሰዓት ነው። ጸሎትና መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንቅልፍ እንዲወስደኝ ይረዳኛል። በጣም የምወደው ጥቅስ ፊልጵስዩስ 4:6, 7 ነው፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ ‘ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።’ ብዙ ጊዜ ስጸልይ አድሬአለሁ፤ ይሖዋ የሚሰጠውም ሰላም አረጋግቶኛል።”

ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ‘አባታችሁ ገና ሳትለምኑት እንኳ ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል’ በማለት ስለ ጸሎት የተናገረው የሚያጽናና ሐሳብ ማንኛውንም ዓይነት ጭንቀት ለመቋቋም ይረዳል። (ማቴዎስ 6:8) ደግሞም አምላክን መለመን ያስፈልገናል። ጸሎት ‘ወደ አምላክ መቅረብ’ የምንችልበት ዋነኛው መንገድ ነው። እኛ ወደ አምላክ ከቀረብን ‘እሱ ወደ እኛ ይቀርባል።’—ያዕቆብ 4:8

በጸሎት አማካኝነት ጭንቀታችንን መግለጻችን ጥሩ ስሜት እንዲሰማን ከማድረግ ያለፈ ጥቅም አለው። በተጨማሪም “ጸሎት ሰሚ” የሆነው ይሖዋ በእምነት አጥብቀው ለሚፈልጉት ሁሉ ሲል እርምጃ ይወስዳል። (መዝሙር 65:2) ኢየሱስ ለተከታዮቹ  “ምንጊዜም ተስፋ ሳይቆርጡ የመጸለይን አስፈላጊነት” ያስተማራቸው ለዚህ ነው። (ሉቃስ 18:1) አምላክ ለእምነታችን ወሮታ እንደሚከፍል እርግጠኞች በመሆን አመራር እንዲሰጠንና እንዲረዳን ሁልጊዜ መለመን አለብን። እኛን ለመርዳት ፍላጎትም ሆነ ችሎታ እንዳለው ፈጽሞ መጠራጠር የለብንም። በዚህ መንገድ ‘ዘወትር መጸለያችን’ ጠንካራ እምነት እንዳለን ያሳያል።—1 ተሰሎንቄ 5:17

እምነት አለን ሲባል ምን ማለት ነው?

ይሁንና እምነት ምንድን ነው? እምነት አምላክን እንደ አንድ እውን አካል አድርጎ ‘ማወቅን’ ይጨምራል። (ዮሐንስ 17:3) ይህን ማድረግ የምንችለው ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ስለ አምላክ በመማር ነው። አምላክ እያንዳንዳችንን እንደሚመለከትና ሊረዳን እንደሚፈልግ ከቃሉ እንረዳለን። ሆኖም ጠንካራ እምነት ስለ አምላክ መሠረታዊ ነገር ብቻ በማወቅ የተወሰነ አይደለም። ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረትን ይጨምራል። ከአንድ ሰው ጋር በአንድ ጀምበር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት እንደማይቻል ሁሉ ከአምላክ ጋርም እንዲህ ዓይነት ወዳጅነት ለመመሥረት ጊዜ ይጠይቃል። ስለ እሱ እያወቅን ስንሄድ፣ “እሱን ደስ የሚያሰኘውን” ነገር ስናደርግና እኛን ለመርዳት ሲል የሚወስደውን እርምጃ ስንመለከት እምነታችን “እያደገ” ይሄዳል። (2 ቆሮንቶስ 10:15፤ ዮሐንስ 8:29) ጃኔት ጭንቀቷን እንድትቋቋም የረዳት እንዲህ ዓይነት እምነት ነው።

ጃኔት እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “በእያንዳንዱ እርምጃዬ የይሖዋን እጅ ማየቴ እምነቴን ለመገንባት ረድቶኛል። በተደጋጋሚ ጊዜ መፍትሔ የሌለው የሚመስል በደል ደርሶብናል። ደግሜ ደጋግሜ ስጸልይ ይሖዋ ፈጽሞ ባላሰብኩት አቅጣጫ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅልናል። ለእሱ ምስጋና በማቀርብበት ጊዜ ያደረገልኝ ብዙ ነገር ትዝ ይለኛል። እሱ ሁሌም በትክክለኛው ጊዜ እንደሚደርስልን አይቻለሁ። ደግሞም ከልብ የሚወዱኝ እውነተኛ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ሰጥቶኛል። እነዚህ ወዳጆቼ ምንጊዜም ከጎኔ የማይጠፉ ሲሆን ለልጆቼም ጥሩ ምሳሌ ናቸው።” *

በሚልክያስ 2:16 ላይ ይሖዋ ‘ፍቺን እጠላለሁ’ ያለው ለምን እንደሆነ ይገባኛል። ታማኝ ለሆነ አንድ የትዳር ጓደኛ እንደ ክህደት ያለ ስሜትን የሚጎዳ ነገር የለም። ባለቤቴ ጥሎን ከሄደ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም አሁንም በውስጤ የባዶነት ስሜት የሚሰማኝ ጊዜ አለ። እንዲህ በሚሰማኝ ጊዜ ሌሎችን ለመርዳት ጥረት አደርጋለሁ፤ ይህም ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።” ጃኔት ራስን ማግለል ተገቢ እንዳልሆነ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት በዚህ መንገድ ተግባራዊ ማድረጓ ጭንቀቷን እንድትቋቋም ረድቷታል። *ምሳሌ 18:1

አምላክ “አባት ለሌላቸው ልጆች አባት፣ ለመበለቶች ደግሞ ጠባቂ ነው።”—መዝሙር 68:5

ጃኔት እንዲህ ብላለች፦ “አምላክ ‘አባት ለሌላቸው ልጆች አባት፣ ለመበለቶች ደግሞ ጠባቂ’ መሆኑን ማወቄ ከምንም ነገር በላይ ያጽናናኛል። ባለቤቴ ጥሎን ቢሄድም ይሖዋ ግን ፈጽሞ አልተወንም።” (መዝሙር 68:5) ጃኔት፣ አምላክ “በክፉ ነገር” እንደማይፈትነን ታውቃለች። ከዚህ ይልቅ እሱ ጥበብን “ለሁሉም በልግስና ይሰጣል”፤ እንዲሁም ጭንቀቶቻችንን ለመቋቋም የሚረዳንን ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ ይሰጠናል።—ያዕቆብ 1:5, 13፤ 2 ቆሮንቶስ 4:7

ይሁን እንጂ የምንጨነቀው ሕይወታችን ለአደጋ የተጋለጠ በመሆኑ የተነሳ ከሆነስ?

^ አን.10 ጭንቀትን ለመቋቋም የሚረዳ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት “ሕይወትህን መቆጣጠር ትችላለህ?” የሚለውን በሐምሌ 2015 ንቁ! ላይ የወጣውን ርዕስ ተመልከት። www.jw.org/am ላይም ይገኛል።