በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ሰኔ 2015

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ በሳይንስ ተተክቷል?

ሳይንስ የደረሰባቸው ነገሮች ውስን ናቸው

ሳይንስ የደረሰባቸው ነገሮች ውስን ናቸው

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አምላክ የለሾች ተብለው የሚጠሩትን ሰዎች አመለካከት የሚገልጹ በርካታ መጻሕፍት በሰፊው ተሰራጭተዋል። እነዚህ የኅትመት ውጤቶች የብዙዎችን ቀልብ የሳቡ ሲሆን ለብዙ ውይይትና ክርክር መነሻ ሆነዋል። ይህን በተመለከተ የነርቭ ሳይንስ ሊቅ የሆኑት ዴቪድ ኢግልማን “አንዳንድ አንባቢዎች . . . የሳይንስ ሊቃውንት ሁሉንም ነገር የሚያውቁ ይመስላቸዋል” በማለት ጽፈዋል። አክለውም “ጥሩ አመለካከት ያላቸው የሳይንስ ሊቃውንት ግን ምንጊዜም የሌሎችን ሐሳብ የሚቀበሉ ሲሆን ያስመዘገቡት ታሪክም ቢሆን አዳዲስና ያልተጠበቁ ግኝቶች የሞሉበት ነው” ብለዋል።

ባለፉት ዘመናት ሁሉ ተሰጥኦ ያላቸው የሳይንስ ሊቃውንት ተፈጥሮን በተመለከተ ግራ ለሚያጋቡ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ባደረጉት ጥረት አስገራሚ የሆኑ እመርታዎችን አስመዝግበዋል። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ፣ በዚህ ሂደት ውስጥ ከባድ ስህተቶችን ፈጽመዋል። አይዛክ ኒውተን ታላላቅ ከሚባሉት የሳይንስ ሊቃውንት አንዱ ነበር። ይህ የሳይንስ ሊቅ የስበት ኃይል ፕላኔቶችን፣ ከዋክብትንና የከዋክብት ረጨቶችን በጽንፈ ዓለም ውስጥ አንድ ላይ ተሳስረው እንዲቀመጡ የሚያደርጋቸው እንዴት እንደሆነ አሳይቷል። ለኮምፒውተር ንድፍ አወጣጥ፣ ለሕዋ ጉዞ እንዲሁም ለኑክሌር ፊዚክስ የሚያገለግል ካልኩለስ የሚባል የሒሳብ ዘርፍ ፈልስፏል። ይሁን እንጂ ኒውተን ኮከብ ቆጠራንና ምትሃታዊ ፎርሙላዎችን ተጠቅሞ የእርሳስ ማዕድንንና ሌሎች ብረቶችን ወደ ወርቅ ለመለወጥ ጥረት አድርጓል።

ከኒውተን በፊት ከ1,500 ከሚበልጡ ዓመታት ቀደም ብሎ ቶለሚ የሚባል የግሪክ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ ሰማያትን በዓይኖቹ ብቻ በመቃኘት ምርምር ያደርግ ነበር። ምሽት ላይ በሰማይ የሚታዩት ፕላኔቶች የሚጓዙበትን መስመር ያጠና ሲሆን በካርታ ሥራም የተካነ ነበር። ይሁን እንጂ ምድር የሁሉም ነገር እምብርት ናት ብሎ ያምን ነበር። በከዋክብት ጥናት ምሁር የሆኑት ካርል ሳጋን ስለ ቶለሚ እንዲህ ብለው ጽፈዋል፦ “ምድርን ማዕከል ያደረገው [የቶለሚ] ጽንፈ ዓለም ከ1,500 ዓመታት በኋላ ተቀባይነት ማጣቱ አንድ ሰው ከፍተኛ እውቀት ያለው መሆኑ ምንም ስህተት እንዳይፈጽም ዋስትና እንደማይሆን የሚያስገነዝብ ነው።”

በዛሬው ጊዜም የሳይንስ ሊቃውንት ምርምር ሲያደርጉ ተመሳሳይ የሆነ ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ጽንፈ ዓለምን በተመለከተ የተሟላ ማብራሪያ የማግኘታቸው ጉዳይ አጠያያቂ ነው። ሳይንስ እድገት እያደረገ እንደመጣና ጥቅም እንዳስገኘልን ባይካድም የደረሰባቸው ነገሮች ውስን መሆናቸውን ማስታወሳችን ተገቢ ነው። የፊዚክስ ሊቅ የሆኑት ፖል ዴቪስ የሚከተለውን ታዝበዋል፦ “ለሁሉም ነገር የተሟላና የማይለዋወጥ ማብራሪያ ለማግኘት መጣር ከንቱ ልፋት ነው።” ይህ አባባል አንድ የማይካድ ሐቅ ይኸውም ሰዎች ተፈጥሮን ሙሉ በሙሉ መረዳት እንደማይችሉ ያስገነዝባሉ። በመሆኑም ሳይንስ ወደ ሕልውና ስለመጣው ስለ እያንዳንዱ ነገር ማብራሪያ መስጠት ይችላል ተብሎ የሚነገረውን ነገር ከመቀበላችን በፊት በጥንቃቄ ማጤናችን ብልህነት ነው።

በግልጽ ማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ ልናገኝ የማንችለውን መመሪያ ይሰጠናል

መጽሐፍ ቅዱስ በተፈጥሮ ላይ ስለሚታዩት ድንቅ ነገሮች ሲናገር “እነሆ፣ እነዚህ የመንገዱ ዳር ዳር ናቸው፤ ስለ እሱ የሰማነው የሹክሹክታ ያህል ብቻ ነው!” ይላል። (ኢዮብ 26:14) ከሰው የማሰብም ሆነ የመረዳት ችሎታ በላይ የሆነ ብዙ የእውቀት ክምችት አለ። በእርግጥም ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት የተጻፉት የሚከተሉት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ዛሬም እውነት ናቸው፦ “የአምላክ ብልጽግና፣ ጥበብና እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱም ፈጽሞ የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይደረስበት ነው!”—ሮም 11:33