በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ግንቦት 2015

 መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ይሖዋ መሐሪና ይቅር ባይ እንደሆነ ተማርኩ

ይሖዋ መሐሪና ይቅር ባይ እንደሆነ ተማርኩ
  • የትውልድ ዘመን: 1954

  • የትውልድ አገር: ካናዳ

  • የኋላ ታሪክ: አጭበርባሪና ቁማርተኛ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግኩት በሞንትሪያል ከተማ ሲሆን አካባቢያችን የማደግ ተስፋ ያለው አይመስልም ነበር። የስድስት ወር ልጅ ሳለሁ አባቴ በመሞቱ ቤተሰቡን የማስተዳደሩ ኃላፊነት በእናቴ ጫንቃ ላይ ወደቀ። በቤተሰባችን ውስጥ ካለነው ስምንት ልጆች መካከል የመጨረሻው እኔ ነበርኩ።

 

እያደግኩ ስሄድ ሕይወቴ ከዕፅ፣ ከቁማርና ከዓመፅ ጋር የተቆራኘ ሆነ፤ እንዲሁም በየዕለቱ ከወንጀለኞች ጋር አዘውትሬ እገናኝ ነበር። አሥር ዓመት ሲሆነኝ ለሴተኛ አዳሪዎችና ለአራጣ አበዳሪዎች መላላክ ጀመርኩ። ብዙ ጊዜ እዋሽ ነበር፤ ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ሰዎችን አታልዬ የራሴን ፍላጎት ማስፈጸም ያስደስተኝ ነበር። እንዲህ ማድረግም ሱስ ሆነብኝ።

አሥራ አራት ዓመት ሲሆነኝ ሰዎችን በማታለል ረገድ የተዋጣልኝ ሆኜ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ብዛት ያላቸው ወርቅ ቅብ ሰዓቶች፣ የእጅ አምባሮችና ቀለበቶች ገዝቼ 14 ካራት የሚል ማኅተም ካደረግኩባቸው በኋላ በጎዳናዎች ላይና በገበያ ማዕከሎች ባሉ የመኪና ማቆሚያዎች እሸጣቸው ነበር። በቀላሉ ገንዘብ ማግኘቴ ያስደስተኝ ነበር። በአንድ ወቅት በአንድ ቀን ብቻ 10,000 ዶላር አግኝቻለሁ!

በ15 ዓመቴ ከጠባይ ማረሚያ ትምህርት ቤት ከተባረርኩ በኋላ የምኖርበት ቦታ አልነበረኝም። ጎዳና ላይ ወይም መናፈሻ ቦታዎች ውስጥ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እምብዛም የማልቀርባቸው ጓደኞቼ ቤት አድር ነበር።

ሰዎችን በማጭበርበሬ የተነሳ ብዙ ጊዜ ለምርመራ ፖሊሶች ፊት እቀርብ ነበር። የተሰረቁ ዕቃዎችን ስለማልሸጥ እስር ቤት ገብቼ አላውቅም። ይሁን እንጂ በማጭበርበር ድርጊት እንዲሁም አስመስሎ በመሥራትና ያለ ፈቃድ በመሸጥ ወንጀል ተከስሼ ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ መቀጫ ከፍያለሁ። ማንንም ስለማልፈራ ለአራጣ አበዳሪዎች ገንዘብ በማመላለስ እላላክ ነበር። ይህ ሥራ አደገኛ ስለነበረ አንዳንድ ጊዜ ሽጉጥ እይዝ ነበር። ከተደራጁ የወንጀለኞች ቡድን ጋር አብሬ የሠራሁባቸው ጊዜያትም አሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሰማሁት የ17 ዓመት ወጣት ሳለሁ ነበር። በወቅቱ የምኖረው ከአንዲት የሴት ጓደኛዬ ጋር ሲሆን እሷም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምራ ነበር። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ደንቦች ጥብቅ እንደሆኑ ይሰማኝ ስለነበር እሷን ተውኳትና ከሌላ ሴት ጋር መኖር ጀመርኩ።

 በሕይወቴ ውስጥ ለውጥ ለማድረግ የተነሳሳሁት ሁለተኛዋም የሴት ጓደኛዬ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በጀመረች ጊዜ ነበር! የሴት ጓደኛዬ በሕይወቷ ውስጥ ለውጥ አድርጋ ይበልጥ ገርና ታጋሽ ስትሆን በጣም ተገረምኩ። እኔም በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንድገኝ የቀረበልኝን ግብዣ ተቀበልኩ። በዚያ ያገኘኋቸው ሥርዓታማና ደግ ሰዎች ጥሩ አቀባበል አደረጉልኝ። እኔ ከማውቃቸው ሰዎች በጣም የተለዩ ነበሩ! በቤተሰቤ ዘንድ ተፈላጊ እንደሆንኩ ተሰምቶኝ አያውቅም፤ እንዲሁም በልጅነት ዘመኔ ሁሉ ፍቅርና ርኅራኄ እንደተነፈግኩ ሆኖ ይሰማኝ ነበር። በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያየሁት ልባዊ ፍቅር እመኘው የነበረ ነገር ነው። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና ያቀረቡልኝን ግብዣ በደስታ ተቀበልኩ።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማርኩት ነገር ሕይወቴን አትርፎልኛል። በቁማር የተነሳ ከተዘፈቅኩበት ከ50,000 ዶላር በላይ የሆነ ዕዳ ለመውጣት ስል ከሁለት ጓደኞቼ ጋር ለመዝረፍ ዕቅድ ይዤ ነበር። ሆኖም በዚህ ጉዳይ ከእነሱ ጋር ሳልተባበር በመቅረቴ ደስተኛ ነኝ! ጓደኞቼ ግን ባቀድነው መሠረት ለዘረፋ ተሰማሩ። አንደኛው ታሰረ፤ ሌላው ደግሞ ተገደለ።

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴን ስቀጥል ብዙ ለውጦች ማድረግ እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ 1 ቆሮንቶስ 6:10 ላይ “ሌቦች ወይም ስግብግቦች ወይም ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ቀማኞች የአምላክን መንግሥት አይወርሱም” እንደሚል ተማርኩ። ይህን ጥቅስ ሳነብ ያለሁበት አሳሳቢ ሁኔታ አስለቀሰኝ። ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ መለወጥ እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ። (ሮም 12:2) ዓመፀኛና ግልፍተኛ የነበርኩ ሲሆን የመዋሸት ልማድም ነበረኝ።

ያም ሆኖ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ይሖዋ መሐሪና ይቅር ባይ እንደሆነ ተማርኩ። (ኢሳይያስ 1:18) ይሖዋ የቀድሞ አኗኗሬን እንድለውጥ ይረዳኝ ዘንድ አጥብቄ ተማጸንኩት። በእሱ እርዳታ ቀስ በቀስ ባሕሪዬን መለወጥ ቻልኩ። ከዚያም ጋብቻችንን ሕጋዊ አደረግን፤ ይህ በሕይወታችን ከወሰድናቸው እርምጃዎች አንዱ ነበር።

የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሥራ ላይ በማዋሌ እስከ ዛሬ ድረስ በሕይወት መኖር ችያለሁ

በ24 ዓመቴ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ነበርኩ። በወቅቱ ሕጋዊ ሥራ መፈለግ ነበረብኝ። ሆኖም በቂ ትምህርትም ሆነ የትምህርት ማስረጃ አልነበረኝም። አሁንም እንደገና ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት አቀረብኩ። ከዚያም ሥራ ለመፈለግ ወጣሁ። ለሚቀጥሩት ሰዎች፣ ሕይወቴን መለወጥና በሐቀኝነት መሥራት እንደምፈልግ ነገርኳቸው። መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናሁ እንደሆነና የተሻልኩ ዜጋ መሆን እንደምፈልግ እነግራቸው ነበር። አብዛኞቹ እኔን ለመቅጠር ፈቃደኞች አልሆኑም። በመጨረሻም ቃለ መጠይቅ ላደረገልኝ አንድ ሌላ ሰው፣ ከዚህ በፊት ስለነበረኝ መጥፎ አኗኗር በግልጽ ከነገርኩት በኋላ ሰውየው “ለምን እንደሆነ ባላውቅም አንተን መቅጠር እንዳለብኝ ተሰምቶኛል” አለ። እኔም ይህ የጸሎቴ መልስ እንደሆነ ተሰማኝ። ከጊዜ በኋላ እኔና ባለቤቴ ተጠምቀን የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን።

ያገኘሁት ጥቅም፦

የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሥራ ላይ በማዋሌና ክርስቲያናዊ አኗኗር በመከተሌ እስከ ዛሬ ድረስ በሕይወት መኖር ችያለሁ። የራሴ የምለው ጥሩ ቤተሰብ አለኝ። ይሖዋ ይቅር እንዳለኝ እርግጠኛ ስለሆንኩ ንጹሕ ሕሊና አለኝ።

ላለፉት 14 ዓመታት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ነገር እንዲያውቁ በመርዳት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተካፈልኩ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ ባለቤቴም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከጎኔ ተሰልፋለች። ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ 22 የሥራ ባልደረቦቼ ይሖዋን ማምለክ እንዲጀምሩ በመርዳት ደስታ አግኝቻለሁ። አሁንም ወደ ገበያ ማዕከሎች እሄዳለሁ፤ ሆኖም ወደዚያ የምሄደው በአንድ ወቅት አደርገው እንደነበረው ሰዎችን ለማጭበርበር አይደለም። ከዚህ ይልቅ እዚያ ለማገኛቸው ሰዎች ስለማምንበት ነገር እመሰክርላቸዋለሁ። ወደፊት በሚመጣው ከአጭበርባሪዎች ነፃ የሆነ አዲስ ዓለም ውስጥ የመኖር ተስፋ እንዳላቸው እነግራቸዋለሁ።—መዝሙር 37:10, 11