በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ግንቦት 2015

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

መጨረሻው ቀርቧል?

መጨረሻው ቀርቧል?

አምላክ፣ ሰዎች አንዳቸው ሌላውን እየገዙና የሰውን ዘር ሕልውና ስጋት ላይ እየጣሉ እንዲቀጥሉ ይፈቅድላቸዋል? አይፈቅድላቸውም፤ ምክንያቱም እስካሁን እንዳየነው ለብዙ መቶ ዘመናት የቆየውን መከራና ጭቆና ወደ ፍጻሜ ለማምጣት እርምጃ ይወስዳል። የሰዎችና የምድር ፈጣሪ ይህን እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ እየቀረበ መሆኑን አንተም እንድታውቅ ይፈልጋል። ታዲያ ይህን እንድታውቅ የሚያደርገው እንዴት ነው?

እስቲ የሚከተለውን ምሳሌ ተመልከት፦ ከዚህ ቀደም ሄደህ ወደማታውቅበት ቦታ በመኪና ከመጓዝህ በፊት ኢንተርኔት ላይ የምታገኛቸውን የመረጃ ምንጮች፣ ካርታዎችንና በጽሑፍ የተዘጋጁ አቅጣጫ ጠቋሚዎችን ትመለከት ይሆናል። ከዚያም አቅጣጫ ጠቋሚዎቹ ላይ የተገለጹትን ምልክቶችና መልክዓ ምድራዊ ገጽታዎች ስታይ ወዳሰብክበት ቦታ እየተቃረብክ እንደሆነ ይሰማሃል። በተመሳሳይም አምላክ ጉልህ ስለሆኑ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች የሚገልጸውን ቃሉን ሰጥቶናል። ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸውን እነዚህን ክስተቶች በምናይበት ጊዜ ወደ መጨረሻው በጣም እንደቀረብን እርግጠኞች እንሆናለን።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሁኔታ እንደሚከሰትና ይህም በመጨረሻው ቀን እንደሚደመደም ይናገራል። በዚህ ወቅት በታሪክ ዘመናት ሁሉ ታይተው የማያውቁ ዓለም አቀፋዊ ክስተቶችና ሁኔታዎች ይታያሉ። እስቲ በአምላክ ቃል ውስጥ የተጠቀሱትን አንዳንድ የመጨረሻው ቀን ገጽታዎች እንመልከት።

1. ዓለም አቀፍ ብጥብጥ በማቴዎስ ምዕራፍ 24 ላይ የተመዘገበው ትንቢት በምድር ላይ የሚፈጸሙ ክስተቶችን ይዘረዝራል፤ እነዚህ ክስተቶች የተለያዩ ገጽታዎች ያሉት ምልክት ክፍል ናቸው። ይህ ምልክት “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” የሆነውን ጊዜ ለይቶ የሚያመለክት ሲሆን ወደ “መጨረሻው” የሚመራ ይሆናል። (ቁጥር 3, 14) እነዚህ የምልክቱ ገጽታዎች ጦርነቶችን፣ የምግብ እጥረትን፣ በተለያየ ስፍራ የሚከሰት የምድር ነውጥን፣ የክፋት መብዛትን፣ የፍቅር መጥፋትንና የሃይማኖት መሪዎች ሰዎችን ለማሳሳት የሚያደርጓቸውን ጥረቶች ያካትታሉ። (ቁጥር 6-26) እርግጥ ነው፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እንዲህ ዓይነቶቹ ክስተቶች ባለፉት መቶ ዘመናት ሲፈጸሙ የነበሩ ናቸው። ይሁን እንጂ መጨረሻው እየቀረበ ሲመጣ እነዚህ ክስተቶች በሙሉ በአንድ ዘመን ውስጥ ይፈጸማሉ። ከእነዚህ በተጨማሪ የሚከተሉት ሦስት ምልክቶች በዚያ ዘመን ውስጥ ይፈጸማሉ።

2. የሰዎች ባሕርይ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ፍጻሜው የሚመሩትን ‘የመጨረሻ ቀናት’ ለይተው ከሚያሳውቋቸው ነገሮች አንዱ የሰዎች ባሕርይ መበላሸቱ እንደሆነ ይናገራል። እንዲህ ይላል፦ “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ፣ ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:1-4) እርግጥ ነው፣ በአጠቃላይ ሲታይ ሰዎች አክብሮት የሚባል ነገር የሌላቸው መሆኑ አዲስ ነገር አይደለም፤ ይሁንና የሰዎች ባሕርይ ከላይ የተዘረዘረው ዓይነት ሁኔታ ላይ የሚደርሰው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ብቻ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስም ይህን ዘመን “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ” ብሎ የሚጠራው ለዚህ ነው። ታዲያ የሰዎች ባሕርይ አደገኛ በሆነ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱን አስተውለሃል?

3. ምድር እየተበላሸች ነው መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ‘ምድርን እያጠፉ ያሉትን የሚያጠፋበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። (ራእይ 11:18) ሰዎች ምድርን እያበላሹ ያሉት በየትኞቹ መንገዶች ነው? ኖኅ የኖረበት ዘመን ከዚህ ጋር ተመሳሳይ እንደነበር ተገልጿል፦ “ምድር በእውነተኛው አምላክ ፊት ተበላሽታ ነበር፤ እንዲሁም በዓመፅ ተሞልታ ነበር። አዎ፣ አምላክ ምድርን ተመለከተ፤ ምድርም ተበላሽታ ነበር።” በመሆኑም አምላክ ያንን ብልሹ ኅብረተሰብ አስመልክቶ ሲናገር ‘አጠፋቸዋለሁ’ ብሏል። (ዘፍጥረት 6:11-13) አንተስ ምድር በዓመፅ እየተሞላች እንደሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን አስተውለሃል? በተጨማሪም ሰዎች በታሪክ ውስጥ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ጊዜ ላይ ይኸውም በምድር ላይ ያለውን ሰብዓዊ ሕይወት በሙሉ ቃል በቃል ጠራርገው ማጥፋት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ይህን ማድረግ የሚያስችል መሣሪያ አላቸው። ምድር በሌላም መንገድ እየተበላሸች ነው። የሰው ልጆች ምድርን በአግባቡ ባለመያዛቸው ለሕይወት አስፈላጊ  የሆኑት ነገሮች ማለትም የምንተነፍሰው አየር፣ የእንስሳትና የዕፀዋት ሥነ ምህዳር እንዲሁም ውቅያኖሶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሹ ነው።

ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ከመቶ ዓመት በፊት የሰው ልጅ ራሱን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት የሚያስችል ኃይል ነበረው?’ አሁን ግን ሰዎች በጣም የተራቀቁ የጦር መሣሪያዎችን በማከማቸትና ከባቢ አየርን በማበላሸት ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት የሚያስችል አቅም እንዳላቸው እያሳዩ ነው። በቴክኖሎጂ መስክ እየታየ ያለው ፈጣን እድገት የሚያስከትለው መዘዝ ከሰዎች የመረዳት ችሎታ በላይ ወይም ከቁጥጥራቸው ውጭ የሆነ ይመስላል። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ የምድርን የወደፊት ዕጣ መወሰንም ሆነ መቆጣጠር አይችልም። በዚህ ምድር ላይ ያለው ሕይወት በሙሉ ከመጥፋቱ በፊት አምላክ ምድርን እያጠፉ ያሉትን ለማጥፋት ጣልቃ ይገባል። አምላክ እንዲህ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል!

4. ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ አንድ ሥራ እንደሚከናወን በትንቢት ተነግሯል፤ ይህ ደግሞ የመጨረሻው ቀን ምልክት ሌላው ገጽታ ነው፤ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴዎስ 24:14) ይህ የስብከት ዘመቻ ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ አብዛኞቹ ሃይማኖቶች አዳዲስ አባላትን ለማፍራት ካደረጉት ጥረት የተለየ ነው። በመጨረሻዎቹ ቀናት “የመንግሥቱ ምሥራች” ይሰበካል። ይህን መልእክት የሚያሳውቅ ከይሖዋ ምሥክሮች ሌላ የምታውቀው ሃይማኖታዊ ቡድን አለ? እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ሃይማኖታዊ ቡድኖች እንዲህ ዓይነት መልእክት የሚሰብኩ ይመስላሉ፤ ይሁንና እነዚህ ሰዎች የስብከት እንቅስቃሴያቸው በአንድ አካባቢ ብቻ የተወሰነ ነው? ወይስ ይህን ምሥራች “ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር” ያውጃሉ?

የአምላክ መንግሥት በመላው ዓለም በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች እየተሰበከ ነው

www.jw.org የተባለው ድረ ገጻችን ‘በመንግሥቱ ምሥራች’ ላይ ያተኮረ ነው። በድረ ገጹ ላይ ይህን መልእክት የያዙ ጽሑፎችን ከ700 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ማግኘት ይቻላል። ከይሖዋ ምሥክሮች ሌላ እንዲህ ባለ ዓለም አቀፍ ደረጃ የመንግሥቱን ምሥራች ለማወጅ ተነሳሽነት ያለው ሌላ ቡድን ታውቃለህ? ኢንተርኔት ሥራ ላይ ከመዋሉ ከረጅም ጊዜ በፊትም የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች ለማሰራጨት በሚያደርጉት ጥረት ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝተው ነበር። ከ1939 አንስቶ በመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ሽፋን ላይ “የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ” የሚሉት ቃላት ሲወጡ ቆይቷል። ስለ ሃይማኖቶች የሚናገር አንድ መጽሐፍ፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት የስብከት ሥራ “በፍጥነቱም ሆነ በስፋቱ ተወዳዳሪ የሌለው” እንደሆነ ገልጿል። የስብከቱ ሥራ ትኩረት የሚያደርገው የአምላክ መንግሥት በሚወስደው እርምጃ አማካኝነት በቅርቡ ‘መጨረሻው እንደሚመጣ’ በሚገልጸው ምሥራች ላይ ነው።

በዓለም ታሪክ ውስጥ ወሳኝ የሆነው ጊዜ

በዚህ ርዕስ ውስጥ የተገለጹት አራት የምልክቱ ገጽታዎች በአንተ የሕይወት ዘመን ውስጥ ሲፈጸሙ ተመልክተሃል? ይህ መጽሔት ከመቶ ለሚበልጡ ዓመታት ለአንባቢዎቹ፣ የምንኖረው መጨረሻው በቀረበበት ጊዜ ላይ እንደሆነ ራሳቸው ማረጋገጥ እንዲችሉ ለመርዳት የዓለምን ክስተቶች በተመለከተ  መረጃዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ተጠራጣሪዎች የቀረቡት እውነታዎችና አኃዛዊ መረጃዎች በግል ስሜት ላይ የተመሠረቱ እንደሆኑና እንደግለሰቡ አመለካከት ሊተረጎሙ እንደሚችሉ በመናገር ማስረጃውን አይቀበሉም። በተጨማሪም የዓለም ሁኔታዎች እየተባባሱ የሄዱ የሚመስሉት ዓለም አቀፍ የመገናኛ መንገዶች እየተስፋፉ ስለመጡ እንደሆነ ይናገራሉ። ያም ሆነ ይህ፣ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ አንድ ልዩ ዘመን በሚደመደምበት ጊዜ ላይ እንደምንገኝ የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች አሉ።

አንዳንድ ባለሙያዎች በዚህች ምድር ላይ ከፍተኛ ለውጦች ወደሚካሄዱበት ጊዜ እየተቃረብን እንደሆነ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ2014 ቡለቲን ኦቭ ዚ አቶሚክ ሳይንቲስትስ የተባለው ጋዜጣ ላይ የሳይንስና ደህንነት ቦርድ ያወጣው ጽሑፍ የተባበሩት መንግሥታትን የፀጥታ ምክር ቤት በሰው ዘር ሕልውና ላይ ከፍተኛ ስጋት እንደተጋረጠበት አስጠንቅቆ ነበር። እነዚህ የሳይንስ ሊቃውንት እንዲህ ብለዋል፦ “በሰው ዘር ሕልውና ላይ የተጋረጡ ስጋቶችን አስመልክቶ የተደረገው ጥናት ሥልጣኔን ስጋት ላይ የሚጥሉ ቴክኖሎጂያዊ አደጋዎች እየጨመሩ ሄደዋል ብለን እንድንደመድም አድርጎናል።” ብዙ ሰዎች በዓለም ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ወቅት ላይ እንደሆንን ይናገራሉ። የዚህ መጽሔት አዘጋጆችና አንባቢዎች ይህ ልዩ ወቅት በእርግጥም የመጨረሻው ቀን እንደሆነና መጨረሻውም ቅርብ እንደሆነ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ የላቸውም። የወደፊቱን ጊዜ ከመፍራት ይልቅ የመጨረሻው ቀን በሚያመጣው ውጤት ልትደሰት ትችላለህ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ከመጨረሻው ቀን በሕይወት መትረፍ ትችላለህ!