በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት

የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ መከበር ያለበት ለምንድን ነው?

የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ መከበር ያለበት ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ከሰዎች ጋር ምን ዓይነት ውይይት እንደሚያደርጉ የሚያሳይ ምሳሌ ከዚህ በታች ቀርቧል። ሚልካ የምትባል አንዲት የይሖዋ ምሥክር ሰሎሜ የምትባልን ሴት ቤቷ ሄዳ እያወያየቻት እንዳለ አድርገን እናስብ።

“ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት”

ሚልካ፦ ታዲያስ ሰሎሜ፣ እንዴት ነሽ? ባለፈው ሳምንት በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ስላየሁሽ በጣም ደስ ብሎኛል። * በዓሉ እንዴት ነበር?

ሰሎሜ፦ እዚያ በመገኘቴ ደስ ብሎኛል፤ ሆኖም ያልገባኝ ነገር አለ። ሰዎች፣ በገና በዓል የኢየሱስን ልደት፣ በፋሲካ ደግሞ ትንሣኤውን እንደሚያከብሩ አውቃለሁ፤ ሞቱን የሚያከብር ሰው ግን አጋጥሞኝ አያውቅም።

ሚልካ፦ እውነት ነው፤ የገና በዓልና ፋሲካ በመላው ዓለም የታወቁ ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች ግን የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ማክበር አስፈላጊ እንደሆነ እናምናለን። ጥቂት ደቂቃዎች ካሉሽ ይህን የምናደርግበትን ምክንያት አጠር አድርጌ ባብራራልሽ ደስ ይለኛል።

ሰሎሜ፦ እሺ፣ ትንሽ ጊዜ አለኝ።

ሚልካ፦ የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ የምናከብረው ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ይህን እንዲያደርጉ ስላዘዘ ነው። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ሌሊት ምን እንደተከናወነ እንመልከት። ከታማኝ ተከታዮቹ ጋር ስለተመገበው አንድ ልዩ ራት ሲጠቀስ ሰምተሽ ታውቂያለሽ?

ሰሎሜ፦ የጌታ ራት ማለትሽ ነው?

ሚልካ፦ ልክ ነሽ። በዚያ ወቅት ኢየሱስ ለተከታዮቹ ግልጽ መመሪያዎች ሰጥቷቸዋል። ኢየሱስ የተናገረውን በሉቃስ 22:19 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ታነቢዋለሽ?

ሰሎሜ፦ እሺ። “በተጨማሪም ቂጣ አንስቶ አመሰገነ፣ ከቆረሰውም በኋላ ሰጣቸውና ‘ይህ ስለ እናንተ የሚሰጠውን ሥጋዬን ያመለክታል። ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት’ አላቸው።”

ሚልካ፦ አመሰግንሻለሁ። ኢየሱስ በጥቅሱ መጨረሻ ላይ “ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት የሰጠውን መመሪያ ልብ በዪ። ደግሞም መታሰቢያውን እንዲያከብሩ ተከታዮቹን ከማዘዙ በፊት ሊያስቡት የሚገባው ነገር ምን እንደሆነ በግልጽ ነግሯቸዋል። ኢየሱስ ለተከታዮቹ ሕይወቱን እንደሚሰጥ ተናግሯል። ይህን ሐሳብ በማቴዎስ 20:28 ላይም በተመሳሳይ መንገድ ገልጾታል። ጥቅሱ “የሰው ልጅም የመጣው ለማገልገልና በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት እንጂ እንዲገለገል አይደለም” ይላል። በአጭሩ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በየዓመቱ የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ የሚያከብሩት ኢየሱስ ያቀረበውን ቤዛዊ መሥዋዕት ለማስታወስ ነው። የኢየሱስ ሞት ታዛዥ የሆኑ ሰዎች በሙሉ ሕይወት እንዲያገኙ መንገድ ከፍቷል።

ቤዛ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

ሰሎሜ፦ ኢየሱስ የሞተው እኛ ሕይወት እንድናገኝ እንደሆነ ሰዎች ሲናገሩ እሰማለሁ። እውነቱን ለመናገር ግን ይህ ምን ማለት እንደሆነ አይገባኝም።

ሚልካ፦ ይህን ሐሳብ ለመረዳት የሚቸግርሽ አንቺ ብቻ አይደለሽም። ስለ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚገልጸው ሐሳብ ጥልቅ ትምህርት ነው። ያም ሆኖ በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኙት ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው እውነቶች አንዱ ነው። በነገራችን ላይ ስለዚህ ጉዳይ ለመወያየት ጊዜ አለሽ?

ሰሎሜ፦ አዎ፣ መወያየት እንችላለን።

 ሚልካ፦ በጣም ጥሩ፤ ወደዚህ ልመጣ ስል ስለ ቤዛው እያነበብኩ ስለነበረ ይህን ርዕስ ቀለል ባለ መንገድ ላብራራልሽ እሞክራለሁ።

ሰሎሜ፦ እሺ።

ሚልካ፦ ቤዛውን ለመረዳት በመጀመሪያ፣ አዳምና ሔዋን በኤደን ገነት ውስጥ ኃጢአት በሠሩ ጊዜ የተፈጠረውን ሁኔታ ማወቅ ያስፈልገናል። በሮም 6:23 ላይ ያለውን ሐሳብ ማንበባችን ጉዳዩን ለመረዳት ያስችለናል። እባክሽ ጥቅሱን ታነቢዋለሽ?

ሰሎሜ፦ እሺ፤ እንዲህ ይላል፦ “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነውና፤ አምላክ የሚሰጠው ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።”

ሚልካ፦ አመሰግንሻለሁ። እስቲ ጥቅሱን በዝርዝር እንመልከተው። በመጀመሪያ፣ ጥቅሱ “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው” በማለት እንደሚጀምር ልብ በዪ። ይህ፣ አምላክ በሰው ልጆች ታሪክ መጀመሪያ ላይ ያወጣው መመሪያ ነው፤ የኃጢአት ደሞዝ ወይም ቅጣት ሞት ነው። እርግጥ ነው፣ መጀመሪያ ላይ ማንም ኃጢአተኛ አልነበረም። አዳምና ሔዋን የተፈጠሩት ፍጹም ተደርገው በመሆኑ ልጆቻቸው በሙሉ ፍጹማን ሆነው ሊወለዱ ይችሉ ነበር። ስለዚህ ማንም ቢሆን እንዲሞት የሚያደርገው ምክንያት አልነበረም። አዳምና ሔዋን እንዲሁም ዘሮቻቸው በሙሉ ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ደስታ የሰፈነበት ዘላለማዊ ሕይወት ነበር። የሚያሳዝነው ግን ሁኔታው እንደታሰበው አልሆነም፤ ምን እንደተከናወነ ታስታውሻለሽ?

ሰሎሜ፦ አዎ፤ አዳምና ሔዋን ከተከለከለው ፍሬ በሉ።

ሚልካ፦ ትክክል። አዳምና ሔዋን ከተከለከለው ፍሬ ሲበሉ ማለትም አምላክን ላለመታዘዝ ሲመርጡ ኃጢአት ሠርተዋል። በሌላ አባባል ፍጽምናቸውን ለማጣት ማለትም ኃጢአተኞች ለመሆን የወሰኑ ያህል ነበር። አዳምና ሔዋን ያደረጉት ምርጫ በእነሱ ብቻ ሳይሆን በዘሮቻቸው ሁሉ ላይ ከባድ መዘዝ የሚያስከትል ነው።

ሰሎሜ፦ ምን ማለትሽ ነው?

ሚልካ፦ እስቲ አንድ ምሳሌ ልስጥሽ። መጋገር ትወጃለሽ?

ሰሎሜ፦ አዎ! ከምወዳቸው ነገሮች አንዱ ነው።

ሚልካ፦ አዲስ ምጣድ ገዝተሻል እንበል። ሆኖም አንድም ጊዜ ሳትጠቀሚበት ተሰነጠቀ። በዚህ ምጣድ ላይ የምትጋግሪው ዳቦ ሁሉ ምን ይሆናል? የስንጥቁን ቅርጽ ይዞ አይወጣም?

ሰሎሜ፦ አዎ ይይዛል።

ሚልካ፦ በተመሳሳይም አዳምና ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ ለመጣስ በመረጡ ጊዜ በኃጢአትና በአለፍጽምና ምክንያት “ስንጥቅ” ወይም እንከን ያለባቸው ሆኑ። ኃጢአተኞች የሆኑት አንድም ልጅ ከመውለዳቸው በፊት በመሆኑ ልጆቻቸው በሙሉ “የስንጥቁን” ምልክት ይዘው ይወለዳሉ። ሁሉም የሚወለዱት ኃጢአተኞች ሆነው ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ኃጢአት” የሚለው ቃል አንድን ድርጊት ብቻ ሳይሆን የወረስነውን ሁኔታም ያመለክታል። በመሆኑም እኔና አንቺ በግላችን ምንም ያጠፋነው ነገር ባይኖርም እንዲሁም አዳምና ሔዋን ኃጢአት በሠሩበት ጊዜ ባንወለድም እንኳ እኛንም ሆነ ወደፊት የሚወለዱ ዘሮቻቸውን በሙሉ ለአለፍጽምና እና ለኃጢአት ኩነኔ ዳርገውናል፤ ይህ ደግሞ ሞት አስከትሎብናል። በሮም 6:23 ላይ እንዳነበብነው የኃጢአት ቅጣት ሞት ነው።

ሰሎሜ፦ ይህ ግን ፍትሐዊ አይመስልም። በአዳምና በሔዋን ኃጢአት ምክንያት የሰው ልጆች በሙሉ ለዘላለም የሚሠቃዩት ለምንድን ነው?

ሚልካ፦ ልክ ነሽ፣ ፍትሐዊ አይመስልም። ይሁንና ነገሩ በዚህ ብቻ አልተቋጨም። ፍትሑ ፍጹም የሆነው አምላክ፣ አዳምና ሔዋን በኃጢአታቸው እንዲሞቱ ሲወስን ዘሮቻቸው ለሆንነው ለእኛ ግን ተስፋ ሰጠን። አምላክ ከዚህ አበሳ የምንገላገልበት መንገድ አዘጋጅቷል። ይህም የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ነው። እስቲ ሮም 6:23ን እንደገና እንመልከተው። ጥቅሱ “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው” ካለ በኋላ “አምላክ የሚሰጠው ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው” ይላል። ስለዚህ ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የምንወጣበትን መንገድ የከፈተልን የኢየሱስ ሞት ነው። *

 ቤዛው—ተወዳዳሪ የሌለው የአምላክ ስጦታ

ሚልካ፦ በዚህ ጥቅስ ላይ ትኩረት እንድታደርጊበት የምፈልገው ሌላም ነጥብ አለ።

ሰሎሜ፦ ምንድን ነው?

ሚልካ፦ ጥቅሱ “አምላክ የሚሰጠው ስጦታ . . . በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው” እንደሚል ልብ በዪ። ለእኛ ሲል የተሠቃየውና ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠን ኢየሱስ ሆኖ ሳለ ጥቅሱ ቤዛው “አምላክ የሚሰጠው ስጦታ” እንደሆነ አድርጎ የሚናገረው ለምንድን ነው? ቤዛው “ኢየሱስ የሚሰጠው ስጦታ” ያልተባለው ለምንድን ነው? *

ሰሎሜ፦ እኔ እንጃ፤ አላውቅም።

ሚልካ፦ አዳምንና ሔዋንን የፈጠራቸው አምላክ ነው፤ በመሆኑም በኤደን ገነት ውስጥ ትእዛዙን በጣሱ ጊዜ የበደሉት እሱን ነው። አምላክ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሰብዓዊ ልጆቹ ሲያምፁበት በጣም አዝኖ መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ይሖዋ አንድ መፍትሔ እንዳዘጋጀ ወዲያውኑ ተናገረ። * ከመንፈሳዊ ፍጡሮቹ አንዱ ወደ ምድር እንዲመጣ፣ ፍጹም ሰው ሆኖ እንዲኖርና በመጨረሻም ሕይወቱን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ዝግጅት አደረገ። ስለዚህ የቤዛው ዝግጅት የአምላክ ስጦታ ነው ማለት ይቻላል። ቤዛው የአምላክ ስጦታ ነው እንድንል የሚያደርገን ሌላም ምክንያት አለ። ኢየሱስ ሲገደል አምላክ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል አስበሽ ታውቂያለሽ?

ሰሎሜ፦ አይ፣ አስቤበት አላውቅም።

ሚልካ፦ ግቢሽ ውስጥ አንዳንድ አሻንጉሊቶች አያለሁ። ልጆች አሉሽ አይደል?

ሰሎሜ፦ አዎ፣ አንድ ወንድ ልጅና አንዲት ሴት ልጅ አሉኝ።

ሚልካ፦ ወላጅ እንደመሆንሽ መጠን፣ የኢየሱስ ሰማያዊ አባት የሆነው ይሖዋ አምላክ፣ ኢየሱስ በተገደለበት ዕለት ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል እስቲ ቆም ብለሽ አስቢ። የሚወደው ልጁ ሲያዝ፣ ሲሾፍበትና በቡጢ ሲመታ ይሖዋ ምን ተሰምቶት ይሆን? ደግሞስ ኢየሱስ በእንጨት ላይ ሲቸነከርና በሥቃይ ሲያጣጥር ቆይቶ ሲሞት አባቱ ምን ተሰምቶት ይሆን?

ሰሎሜ፦ በጣም አዝኖ መሆን አለበት። ከዚህ በፊት አስቤበት አላውቅም ነበር!

ሚልካ፦ እውነት ነው፣ አምላክ በዚያ ዕለት ምን እንደተሰማው በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ያም ቢሆን አምላክ ስሜት እንዳለው እናውቃለን፤ በውድ ልጁ ላይ ይህ ሁሉ እንዲደርስ የፈቀደው ለምን እንደሆነም እናውቃለን። ሁኔታው ታዋቂ በሆነ አንድ ጥቅስ ማለትም በዮሐንስ 3:16 ላይ ግሩም በሆነ መንገድ ተገልጿል። እባክሽ ይህን ጥቅስ ታነቢው?

ሰሎሜ፦ እሺ። እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”

ቤዛዊው መሥዋዕት ከሁሉ የላቀ የፍቅር መግለጫ ነው

ሚልካ፦ አመሰግንሻለሁ። የዚህን ጥቅስ የመጀመሪያ ክፍል እስቲ እንደገና ተመልከቺው። “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ” ይላል። ቁልፉ ፍቅር ነው። አምላክ፣ ልጁን ለእኛ እንዲሞትልን ወደዚህ ምድር ለመላክ ያነሳሳው ፍቅር ነው። በእርግጥም ቤዛዊው መሥዋዕት ከሁሉ የላቀ የፍቅር መግለጫ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ በየዓመቱ የሚያከብሩት ይህን ዝግጅት ለማስታወስ ነው። ያደረግነው ውይይት ለጥያቄሽ መልስ ለማግኘት አስችሎሻል?

ሰሎሜ፦ አዎ፤ ጊዜ ወስደሽ ይህን ጉዳይ ስላወያየሽኝ አመሰግንሻለሁ።

አንተስ ለመረዳት ያስቸገረህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ አለ? የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያምኑባቸው ነገሮች ወይም ስለ ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው ለማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ስትገናኝ ጥያቄህን ከማቅረብ ወደኋላ አትበል። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከአንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ ናቸው።

^ አን.5 የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ ያቀረበውን መሥዋዕት ለማስታወስ በዓመት አንድ ጊዜ የሞቱን መታሰቢያ ያከብራሉ። በዚህ ዓመት መታሰቢያው የሚከበረው ዓርብ፣ መጋቢት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. (ሚያዝያ 3 ቀን 2015) ነው።

^ አን.32 የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ከኃጢአት ነፃ የሚያወጣን እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ከቤዛው ተጠቃሚ ለመሆን እኛ ምን ማድረግ እንዳለብን ወደፊት በዚህ ዓምድ ሥር በሚወጣ ርዕስ ላይ ይብራራል።

^ አን.36 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው አምላክና ኢየሱስ የየራሳቸው ማንነት አላቸው። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 4 ተመልከት።

^ አን.38 ዘፍጥረት 3:15ን ተመልከት።