ዮሴፍ እስር ቤቱ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ይላል፤ ሲሠራ ከነበረው አድካሚ ሥራና ከሚወብቀው አየር የተነሳ ላቡ ይንጠባጠባል። እንደ እሳት በምትፋጀው ፀሐይ ምክንያት እስር ቤቱ እንደ ምድጃ ግሏል። ዮሴፍ እስር ቤቱ ውስጥ ከመቆየቱ ብዛት ዙሪያ ገባውን በደንብ ያውቀዋል። ከወኅኒ ቤቱ ውጭ ያለውን ዓለም ካየ ዓመታት ተቆጥረዋል። እርግጥ ነው፣ ዮሴፍ በእስር ቤቱ ውስጥ በጣም የተከበረ ሰው ነው። ይሁን እንጂ ያው እስረኛ ነበር።

ዮሴፍ በኬብሮን ጉብታዎች ላይ የአባቱን በጎች ይጠብቅ ስለነበረበት ጊዜ ደጋግሞ ያስብ እንደነበር ግልጽ ነው! አባቱ ያዕቆብ ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቆ ወደሚገኝ ቦታ ሲልከው ዕድሜው 17 ዓመት ገደማ ነበር። አሁን እንዲህ ዓይነቱን ነፃነት መልሶ ማግኘት የማይታሰብ ነገር ይመስላል! ቅናት ያሳበዳቸው ወንድሞቹ በጥላቻ ተነሳስተው ዮሴፍን ለባርነት ሸጠውታል። ወደ ግብፅ ከተወሰደ በኋላም ጲጥፋራ በሚባል ግብፃዊ ባለሥልጣን ቤት ውስጥ ማገልገል ጀመረ። የጲጥፋራ ሚስት አስገድዶ ሊደፍራት እንደሞከረ በሐሰት በመወንጀል እስር ቤት እንዲጣል እስካደረገችበት ጊዜ ድረስ በጌታው ዘንድ የታመነ ነበር። *ዘፍጥረት ምዕራፍ 37 እና 39

አሁን ዮሴፍ 28 ዓመት ሆኖታል፤ በባርነትና በእስራት አሥር የሚያህሉ ዓመታትን አሳልፏል። በአጭሩ ለመግለጽ፣ ዮሴፍ ያሳለፈው ሕይወት እሱ ከጠበቀው ፍጹም ተቃራኒ ነበር። ታዲያ ዮሴፍ ከእስራት ነፃ ይወጣ ይሆን? የሚወደውን አረጋዊ አባቱንና ታናሽ ወንድሙን ብንያምን ዳግመኛ ማየት ይችል ይሆን? እዚህ ጉድጓድ ውስጥ ተጥሎ የሚቆየው እስከ መቼ ነው?

አንተስ እንደ ዮሴፍ ተሰምቶህ ያውቃል? አንዳንድ ጊዜ ሕይወታችን በልጅነታችን ከምናስበው የተለየ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም የሚያጋጥሙን ችግሮች ከመደራረባቸው የተነሳ መውጫ ቀዳዳው ሊጠፋብን ወይም መከራውን ችለን መኖር ሊያቅተን ይችላል። እስቲ ዮሴፍ ካሳየው እምነት ምን ልንማር እንደምንችል እንመልከት።

ይሖዋ ከዮሴፍ ጋር ነበረ

ዮሴፍ፣ አምላኩ ይሖዋ ፈጽሞ እንዳልረሳው ያውቅ ነበር፤ ይህም መጽናት እንዲችል ረድቶታል። ዮሴፍ በባዕድ አገር በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ሆኖም እንኳ ይሖዋ እሱን ከመባረክ ወደኋላ አላለም። ዘገባው “ዮሴፍ እዚያ እስር ቤት ባለበት ጊዜ ሁሉ፣ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ቸርነቱንም አበዛለት፣ በወህኒ አዛዡም ዘንድ ሞገስን ሰጠው” የሚለው ለዚህ ነው። (ዘፍጥረት 39:21-23) ዮሴፍ ጠንክሮ መሥራቱን በቀጠለ መጠን አምላክም እሱን ለመባረክ ተጨማሪ ምክንያት ያገኛል። ዮሴፍ፣ ይሖዋ ምንጊዜም ከእሱ ጋር እንደሆነ ማወቁ ምንኛ አጽናንቶት ይሆን!

ታዲያ ይሖዋ፣ ዮሴፍ ዕድሜውን ሙሉ እስር ቤት ውስጥ እንዲማቅቅ ይፈቅድ ይሆን? ዮሴፍ ስለዚህ ጉዳይ በእርግጠኝነት የሚያውቀው ነገር አልነበረም፤ ሆኖም ጉዳዩን አስመልክቶ ለአምላክ እንደጸለየ ጥርጥር የለውም። ደግሞም ብዙ ጊዜ እንደሚያጋጥመው ሁሉ ዮሴፍም የጸሎቱን መልስ ያገኘው እሱ በጠበቀው መንገድ አልነበረም። አንድ ቀን፣ እስር ቤት ውስጥ የሆነ ግርግር ተፈጠረ፤ ይህ የሆነው የፈርዖን የቅርብ ባለሟሎች የሆኑ ሁለት አዳዲስ እስረኞች ወደ እስር ቤቱ ስለመጡ ነበር። አንደኛው ባለሥልጣን የንጉሡ የዳቦ ጋጋሪዎች አለቃ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ነበር።—ዘፍጥረት 40:1-3

የወኅኒ ቤቱ አለቃ፣ እነዚህ ሁለት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በዮሴፍ  ጥበቃ ሥር እንዲሆኑ አደረገ። * አንድ ቀን እነዚህ ባለሥልጣናት ግራ የሚያጋባ ሕልም አዩ። ዮሴፍ ጠዋት ሲያያቸው አንድ ችግር እንደገጠማቸው አስተዋለ። ስለዚህ “ምነው ዛሬስ ፊታችሁ ላይ ሐዘን ይነበባል?” ብሎ ጠየቃቸው። (ዘፍጥረት 40:3-7) ሰዎቹም ያጋጠማቸውን ሁኔታ ምንም ሳያስቀሩ ለዮሴፍ ነገሩት፤ ይህን ለማድረግ የደፈሩት ዮሴፍ ደግነት ያሳያቸው ስለነበር ሳይሆን አይቀርም። ዮሴፍ አይወቀው እንጂ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ያደረገው ውይይት ወደፊት ሕይወቱን የሚቀይር ነበር። ይሁንና ዮሴፍ ሌሎችን በደግነት ባይይዝ ኖሮ እነዚህ ሰዎች እሱን ለማነጋገር ፈቃደኛ ይሆኑ ነበር? ዮሴፍ ያደረገው ነገር እኛም ‘ለሌሎች ሰዎች አሳቢነት በማሳየት በአምላክ ላይ እምነት እንዳለኝ አሳያለሁ?’ ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ ያደርገናል።

ዮሴፍ አብረውት ለታሰሩት ሰዎች ደግነትና አክብሮት ያሳይ ነበር

ሁለቱ ሰዎች ግራ የሚያጋባ ሕልም እንዳለሙና የሚተረጉምላቸው ሰው በማጣታቸው እንደተጨነቁ ለዮሴፍ ነገሩት። ግብፃውያን ለሕልም ትልቅ ቦታ ይሰጡ ነበር፤ በመሆኑም ሕልም የመተርጎም ችሎታ አለን በሚሉ ሰዎች ላይ ከፍተኛ እምነት ይጥሉ ነበር። ሁለቱ ሰዎች፣ ሕልሙን እንዲያዩ ያደረገው የዮሴፍ አምላክ ይሖዋ እንደሆነ አላወቁም። ዮሴፍ ግን ይህን ተረድቶ ነበር። ስለዚህ “ሕልምን የሚፈታው አምላክ አይደለም? እስቲ ያያችሁትን ሕልም ንገሩኝ” በማለት አረጋጋቸው። (ዘፍጥረት 40:8 NW) ዮሴፍ የተናገረው ይህ ሐሳብ በዛሬው ጊዜ ላሉት ቅን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ትልቅ ትርጉም ያለው መልእክት ይዟል። ሃይማኖተኛ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ዓይነት የትሕትና መንፈስ ቢያሳዩ ኖሮ እንዴት ጥሩ ነበር! የአምላክ ቃል ያለውን ትክክለኛ ትርጉም ለማወቅ ከፈለግን የኩራት አስተሳሰብን ማስወገድና በአምላክ ላይ መታመን ይኖርብናል።—1 ተሰሎንቄ 2:13፤ ያዕቆብ 4:6

የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ በቅድሚያ ሕልሙን ተናገረ። በሕልሙ ሦስት ቀንበጦች ያሉት አንድ የወይን ተክል እንዳየና በቀንበጦቹ ላይም የወይን ዘለላዎች እንደነበሩ ለዮሴፍ ነገረው። ከዚያም የበሰሉትን የወይን ፍሬዎች ወስዶ በፈርዖን ጽዋ ውስጥ እንደጨመቃቸው ገለጸለት። ለይሖዋ ምስጋና ይግባውና ዮሴፍ የሕልሙን ትርጉም ወዲያውኑ አወቀ። ዮሴፍ ለመጠጥ አሳላፊው ሦስቱ የወይን ቀንበጦች ሦስት ቀናትን እንደሚያመለክቱና በሦስት ቀናት ውስጥ ፈርዖን የመጠጥ አሳላፊውን ወደ ቀድሞ ሥልጣኑ እንደሚመልሰው ነገረው። በዚህ ጊዜ በመጠጥ አሳላፊው ፊት ላይ የእፎይታ ስሜት ተነበበ፤ ዮሴፍም “ቸርነት አድርግልኝ፤ ስለ እኔም ለፈርዖን ንገርልኝ” አለው። ከዚያም ከአገሩ የወጣው በአፈና እንደሆነና ወደ ወኅኒ የተጣለውም ያለአንዳች ጥፋት እንደሆነ ገለጸለት።—ዘፍጥረት 40:9-15

የዳቦ ጋጋሪዎቹ አለቃ፣ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ሕልም ፍቺ መልካም መሆኑን ሲያይ እሱም ሕልሙን ለመናገር ተነሳሳ፤ ከዚያም በሕልሙ ሦስት የዳቦ መሶቦችን ተሸክሞ እንደነበረና ወፎች በራሱ ላይ ከተሸከመው መሶብ ሲበሉ እንዳየ ለዮሴፍ ነገረው። አሁንም አምላክ፣ የዚህን ሕልም ትርጉም ለዮሴፍ ገለጠለት። ይሁን እንጂ ሕልሙ ለዳቦ ጋጋሪዎቹ አለቃ መልካም ዜና የያዘ አልነበረም። ዮሴፍ እንዲህ አለው፦ “የሕልሙ ፍቺ ይህ ነው፤ ሦስቱ መሶብ ሦስት ቀን ነው፤ በሦስት ቀን ውስጥ  ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፤ በዕንጨትም ላይ ይሰቅልሃል፤ ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል።” (ዘፍጥረት 40:16-19) የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች መልካም ዜናም ሆነ የፍርድ መልእክት በድፍረት ያውጁ እንደነበረ ሁሉ ዮሴፍም የአምላክን መልእክቶች በድፍረት ተናግሯል።—ኢሳይያስ 61:2

ከሦስት ቀናት በኋላ ዮሴፍ የተናገረው ነገር ተፈጸመ። ፈርዖን የልደት በዓሉን ለማክበር ግብዣ አዘጋጀ፤ እርግጥ ነው በጥንት ዘመን የነበሩ የአምላክ ሕዝቦች እንዲህ ዓይነቱን ልማድ አይከተሉም ነበር። ያም ሆነ ይህ በዚህ ዕለት ፈርዖን በሁለቱ አገልጋዮቹ ላይ ፍርድ አስተላለፈ። ዮሴፍ አስቀድሞ እንደተናገረው ሁሉ የዳቦ ጋጋሪዎቹ አለቃ የተገደለ ሲሆን የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ደግሞ ወደ ቀድሞ ሥልጣኑ ተመለሰ። የሚያሳዝነው ግን ይህ ሰው ዮሴፍን ረሳው።—ዘፍጥረት 40:20-23

“እዚህ ግባ የምባል ሰው አይደለሁም!”

ይህ ከሆነ ድፍን ሁለት ዓመታት አለፉ። (ዘፍጥረት 41:1) ይህ ለዮሴፍ እንዴት ተስፋ አስቆራጭ ሊሆንበት እንደሚችል አስበው! ይሖዋ የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃና የዳቦ ጋጋሪዎቹን አለቃ ሕልም ፍቺ ከገለጠለት በኋላ የዮሴፍ ተስፋ ለምልሞ ሊሆን ይችላል። በእያንዳንዱ ቀን፣ ጎህ ሲቀድ ዮሴፍ ይህ ቀን ከእስር ነፃ የሚወጣበት እንደሆነ በማሰብ ተስፋ አድርጎ ይሆናል፤ ያም ሆኖ አሰልቺ ከሆነው የእስር ቤት ሕይወት ሳይላቀቅ ቀኖቹ ነጎዱ። እነዚህ ሁለት ዓመታት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የዮሴፍ ጽናት የተፈተነባቸው ጊዜያት ሳይሆኑ አይቀሩም። ሆኖም ዮሴፍ ተስፋ ቆርጦ በአምላኩ በይሖዋ መተማመኑን አልተወም። ለችግሩ እጅ ከመስጠት ይልቅ ሁኔታውን በጽናት ለመቋቋም ቆርጦ ነበር፤ እንዲያውም ፈተናው ይበልጥ ጠንካራ እንዲሆን ረድቶታል።—ያዕቆብ 1:4

በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ስንኖር ጽናቱ የማይፈተን ማን አለ? በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ማቆሚያ የሌላቸው የሚመስሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመጋፈጥ አምላክ ብቻ ሊሰጠን የሚችለው ጽናት፣ ትዕግሥትና ውስጣዊ ሰላም ያስፈልገናል። አምላክ ዮሴፍን እንደረዳው ሁሉ ተስፋ እንዳንቆርጥና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩህ ተስፋ እንዲኖረን እኛንም ሊረዳን ይችላል።—ሮም 12:12፤ 15:13

የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ዮሴፍን ቢረሳውም ይሖዋ ግን ፈጽሞ አልረሳውም። አንድ ቀን ይሖዋ ለፈርዖን ሁለት ሕልሞች አሳየው። በመጀመሪያው ሕልም ላይ ንጉሡ ቁመናቸው ያማረ ሰባት የሰቡ ላሞችና ከእነሱ በኋላ ደግሞ አስቀያሚ መልክ ያላቸው ከሲታ የሆኑ ሰባት ላሞች ከአባይ ወንዝ ሲወጡ ተመለከተ። ከሲታዎቹ ላሞች የሰቡትን ላሞች በሏቸው። በኋላም ፈርዖን በሕልሙ ፍሬያቸው የተንዠረገገና ያማሩ ሰባት የእህል ዛላዎች ተመለከተ። ከዚያም የቀጨጩና በነፋስ የተመቱ ሰባት የእህል ዛላዎች ወጡ፤ እነዚህ ዛላዎች ፍሬያቸው የተንዠረገጉና ያማሩ የሆኑትን የእህል ዛላዎች ዋጧቸው። ፈርዖን ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነቃ በሕልሞቹ የተነሳ እጅግ ታወከ፤ በመሆኑም የግብፅን ጠቢባንና አስማተኛ የሆኑትን ካህናት በሙሉ አስጠርቶ ሕልሞቹን እንዲተረጉሙለት ጠየቃቸው። ሆኖም ሕልሞቹን ሊተረጉምለት የቻለ አልነበረም። (ዘፍጥረት 41:1-8) እነዚህ ሰዎች መናገር ተስኗቸው ይሁን አለዚያም እርስ በርስ የሚጋጩ የተለያዩ ሐሳቦችን አቅርበው ሁኔታውን በእርግጠኝነት ማወቅ አንችልም። ያም ሆነ ይህ ፈርዖን ያሰበው ነገር አልተሳካለትም፤ በመሆኑም የሕልሞቹን ፍቺ ለማወቅ ይበልጥ ጓጓ።

በመጨረሻ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ዮሴፍን አስታወሰው! በዚህ ጊዜ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማው፤ ከዚያም ከሁለት ዓመታት በፊት እሱና የዳቦ ጋጋሪዎቹ አለቃ እስር ቤት ሳሉ ሕልማቸውን በትክክል የተረጎመላቸው አንድ ወጣት እንደነበር ለፈርዖን ነገረው። ፈርዖንም ወዲያውኑ ዮሴፍን ከእስር ቤት እንዲያመጡት ሰዎች ላከ።—ዘፍጥረት 41:9-13

ፈርዖን የላካቸው ሰዎች ወደ እስር ቤቱ ሲመጡ ዮሴፍ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ሞክር። ዮሴፍ በፍጥነት ልብሶቹን ለወጠ እንዲሁም ፀጉሩን ተላጨ፤ ምናልባትም በዘመኑ በነበረው የግብፃውያን ልማድ መሠረት የራስ ፀጉሩን ሙሉ በሙሉ ተላጭቶ ሊሆን ይችላል። ከፈርዖን ጋር በሚነጋገርበት ወቅት የይሖዋ በረከት እንዳይለየው አጥብቆ ጸልዮ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም! ብዙም ሳይቆይ ሰዎቹ ወደተንቆጠቆጠው ንጉሣዊ ቤተ መንግሥት ወስደው ፈርዖን ፊት አቆሙት። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ከዚያም ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ ‘ሕልም አይቼ ነበር፤ የሚፈታልኝ ሰው ግን አልተገኘም። አንተ ሕልም ሰምተህ መፍታት እንደምትችል ሰማሁ።’” በዚህ ጊዜም ቢሆን ዮሴፍ የሰጠው ምላሽ ትሑት እንደሆነና በአምላኩ እንደሚታመን የሚያሳይ ነበር፤ ዮሴፍ “ኧረ እኔ እዚህ ግባ የምባል ሰው አይደለሁም! ለፈርዖን መልካም የሆነውን ነገር የሚያሳውቀው አምላክ ነው” አለ።—ዘፍጥረት 41:14-16 NW

ትሑት የሆነው ዮሴፍ ፈርዖንን “እዚህ ግባ የምባል ሰው አይደለሁም!” ብሎታል

ይሖዋ ትሑትና ታማኝ የሆኑ ሰዎችን ይወዳል፤ ስለሆነም ከጥበበኞቹና ከካህናቱ የተሰወረውን የሕልሙን ፍቺ ለዮሴፍ መግለጡ አያስደንቅም። ዮሴፍ፣ ፈርዖን ያያቸው ሁለት ሕልሞች ተመሳሳይ ትርጉም እንዳላቸው ገለጸ። ይሖዋ፣ ነገሩ ሁለት ጊዜ እንዲታይ ማድረጉ ጉዳዩ “የተቆረጠ” መሆኑንና መፈጸሙ እንደማይቀር የሚያመለክት ነበር። የሰቡት ላሞችና ያማሩት የእህል ዛላዎች በግብፅ የተትረፈረፈ ምርት የሚኖርባቸውን ሰባት ዓመታት የሚያመለክቱ ሲሆኑ ከሲታዎቹ ላሞችና የቀጨጩት  የእህል ዛላዎች ደግሞ የጥጋብ ዓመታቱን ተከትለው የሚመጡ ሰባት የረሃብ ዓመታትን የሚያመለክቱ ነበሩ። ዮሴፍ፣ ረሃቡ አገሪቱን እጅግ እንደሚጎዳት ገለጸ።—ዘፍጥረት 41:25-32

ፈርዖን፣ ዮሴፍ ሕልሞቹን በትክክል እንደፈታለት ተገነዘበ። ይሁን እንጂ ፈርዖን ምን ማድረግ ይኖርበታል? ዮሴፍ አንድ እርምጃ እንዲወሰድ ሐሳብ አቀረበ። እህል በሚትረፈረፍባቸው ሰባት ዓመታት በግብፅ ምድር የሚገኘውን ምርት የሚያከማችለትና በረሃቡ ዓመታት ደግሞ የተከማቸውን እህል የሚያከፋፍልለት “ብልኀና አስተዋይ ሰው” እንዲፈልግ ለፈርዖን ነገረው። (ዘፍጥረት 41:33-36) ከበቂ በላይ ተሞክሮና ችሎታ የነበረው ቢሆንም ዮሴፍ እሱ እንዲሾም ሐሳብ አላቀረበም። ዮሴፍ ትሑት በመሆኑ እንዲህ ያለውን የትዕቢት ድርጊት የመፈጸም ሐሳብ ሊኖረው እንደማይችል የታወቀ ነው፤ በተጨማሪም የእምነት ሰው ስለነበር እንዲህ ማድረግ አያስፈልገውም። በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት ካለን ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ ወይም አንቱ ለመባል አንጣጣርም። ያሳሰበንን ጉዳይ ሁሉን ነገር ማድረግ ለሚችለው ለይሖዋ መተዋችን ውስጣዊ ሰላም ያስገኝልናል!

“እንደዚህ ያለ ሰው ማንን ልናገኝ እንችላለን?”

ፈርዖንና አገልጋዮቹ ዮሴፍ ያቀረበው ሐሳብ ጥሩ እንደሆነ ተገነዘቡ። በተጨማሪም ፈርዖን፣ ዮሴፍ እንዲህ ያለ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ሐሳብ ያቀረበው በአምላኩ እርዳታ እንደሆነ ገለጸ። እንዲሁም በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ለነበሩት አገልጋዮቹ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት እንደዚህ ያለ ሰው ማንን ልናገኝ እንችላለን?” አላቸው። ከዚያም ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ስለ ገለጠልህ፣ እንዳንተ ያለ አስተዋይና ብልኀ ሰው የለም። አንተ በቤተ መንግሥቴ የበላይ ትሆናለህ፤ ሕዝቤም ሁሉ ለሥልጣንህ ይገዛል፤ እኔ ከአንተ የምበልጠው በዙፋኔ ብቻ ይሆናል።”—ዘፍጥረት 41:38-41

ፈርዖን የተናገረውን ቃል የሚፈጽም ሰው ነበር። በመሆኑም ዮሴፍን ከጥሩ የተልባ እግር የተሠራ ልብስ አለበሰው። በአንገቱ ላይ የወርቅ ሐብል አጠለቀለት፤ የማኅተም ቀለበቱን ሰጠው፤ እንዲሁም በክብር ሠረገላው ላይ አስቀመጠው፤ ከዚያም በአገሪቱ በሙሉ በመዘዋወር ዕቅዱን እንዲያስፈጽም ሙሉ ሥልጣን ሰጠው። (ዘፍጥረት 41:42-44) እንግዲህ ዮሴፍ በአንድ ጀምበር ከወኅኒ ቤት ወጥቶ ቤተ መንግሥት ገባ። ያን ዕለት ጠዋት ተራ እስረኛ የነበረው ሰው ማታ ላይ ከፈርዖን ቀጥሎ ሁለተኛ ገዢ ሆነ። ዮሴፍ በይሖዋ መታመኑ በእርግጥም ትክክል ነበር! ይሖዋ በእነዚህ ዓመታት ሁሉ በአገልጋዩ ላይ የደረሰውን በደል ተመልክቷል። እንዲሁም በትክክለኛው ጊዜና በትክክለኛው መንገድ ሁኔታው እንዲስተካከል አድርጓል። ይሖዋ ይህን ያደረገው ዮሴፍን ከሚደርስበት ግፍ ነፃ ለማውጣት ብቻ ሳይሆን ወደፊት የሚቋቋመውን የእስራኤል ብሔር ለመታደግ በማሰብ ነበር። ይህ የሆነው እንዴት እንደሆነ ወደፊት በዚህ ዓምድ ሥር በሚወጣ ርዕስ ላይ ይብራራል።

አንተም ማቆሚያ የሌለው የሚመስል ችግር ገጥሞህ ምናልባትም ለዓመታት በደል ሲፈጸምብህ ቆይቶ ሊሆን ይችላል፤ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ዮሴፍን አስታውስ። ዮሴፍ ደግ፣ ትሑት፣ ጽኑ እና የእምነት ሰው ሆኖ በመቀጠሉ በመጨረሻ የይሖዋን በረከት አግኝቷል።

^ አን.4 በነሐሴ 1 እና በኅዳር 1, 2014 የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ “በእምነታቸው ምሰሏቸው” በሚለው ዓምድ ሥር የወጡትን ርዕሶች ተመልከት።

^ አን.10 የጥንቶቹ ግብፃውያን ከ90 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የዳቦና የኬክ ዓይነቶችን ይጋግሩ ነበር። በመሆኑም የፈርዖን የዳቦ ጋጋሪዎች አለቃ ከፍተኛ ሥልጣን ያለው ሰው ነበር። የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃም ለፈርዖን የሚቀርበው ወይን ጠጅና እንደ ቢራ ያለ ሌላ መጠጥ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆንና መርዝ እንዳይጨመርበት የመከታተል ኃላፊነት ነበረበት፤ ምክንያቱም በዚያ ዘመን በነገሥታት ላይ ሴራ መጠንሰስና የግድያ ሙከራ ማድረግ የተለመዱ ነገሮች ነበሩ። በመሆኑም የመጠጥ አሳላፊ ተደርጎ የሚሾመው ሰው አብዛኛውን ጊዜ የንጉሡ የቅርብ አማካሪ ነበር።