“ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን ያገኝ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር ችሮታ ነው።” (መክብብ 3:13) አምላክ በሥራችን እንድንደሰት የሚፈልግ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱን ደስታ ማግኘት የምንችልበትን መንገድ ይነግረናል ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ አይደለም? (ኢሳይያስ 48:17) ደስ የሚለው ነገር፣ አምላክ ከሥራችን ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ገልጾልናል። እስቲ ቀጥሎ የተጠቀሱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ተመልከት።

ለሥራ አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ

የምትሠራው ሥራ የአእምሮ ሥራ ወይም የጉልበት ሥራ አሊያም ደግሞ ሁለቱንም የሚያጠቃልል ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና በየትኛውም የሥራ መስክ ቢሆን “ለፍተው የሠሩት ሁሉ ትርፍ [እንደሚያስገኝ]” እወቅ። (ምሳሌ 14:23) ምን ዓይነት ትርፍ? አንደኛ ነገር፣ ጠንክረን መሥራታችን የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች ለማሟላት ያስችለናል። እርግጥ ነው፣ አምላክ እሱን በሙሉ ልብ ለሚያመልኩ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚያሟላ ቃል ገብቷል። (ማቴዎስ 6:31, 32) ይሁን እንጂ እኛም በሐቀኝነት ጠንክረን እንድንሠራ ይጠብቅብናል።—2 ተሰሎንቄ 3:10

በመሆኑም ሥራ ግባችን ላይ እንድንደርስ የሚረዳን መሣሪያ ነው ሊባል ይችላል። ሥራ ኃላፊነታችንን በአግባቡ እንድንወጣ ያስችለናል። የ25 ዓመቱ ጆሹዋ እንዲህ ብሏል፦ “ራስህን መቻል ትልቅ ስኬት ነው። የሚያስፈልግህን ነገር መግዛት ከቻልክ ከሥራ ማግኘት ያለብህን ጥቅም እያገኘህ ነው ሊባል ይችላል።”

ከዚህም በላይ ጠንክሮ መሥራት ለራሳችን አክብሮት እንዲኖረን ይረዳናል። ጠንክሮ መሥራት ድካምና ልፋት እንደሚጠይቅ ግልጽ ነው። ሥራችን አሰልቺ ወይም ከባድ ቢሆንም እንኳ ከራሳችን ጋር ታግለን በትጋት መሥራታችንን የምንቀጥል ከሆነ ግን አምላክ የሚፈልግብንን ነገር እያደረግን እንደሆነ ስለምናውቅ እርካታ እናገኛለን። ስንፍና እንዲያሸንፈን ባለመፍቀዳችን ደስ ይለናል። (ምሳሌ 26:14) ስለሆነም ሥራ ከፍተኛ እርካታ ያስገኝልናል። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው አሮን እንዲህ ብሏል፦ “ቀኑን ሙሉ ስሠራ ከዋልኩ በኋላ ደስ የሚል ስሜት ይሰማኛል። ሰውነቴ ቢዝልም እንዲሁም የሠራሁትን ሥራ ማንም ሰው ልብ ባይለውም እንኳ አንድ ትልቅ ነገር እንዳከናወንኩ አስባለሁ።”

 በሥራህ የተካንክ ሁን

መጽሐፍ ቅዱስ “በሙያው ሥልጡን” ስለሆነ ወንድ እንዲሁም ‘ሥራ የሚወዱ እጆች’ ስላሏት ሴት በአድናቆት ይናገራል። (ምሳሌ 22:29፤ 31:13) እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ምንም ጥረት ሳያደርግ በሥራው የተካነ ሊሆን አይችልም። ደግሞም ብዙ ሰዎች በደንብ የማይችሉትን ሥራ ማከናወን አያስደስታቸውም። ምናልባትም ብዙዎች በሥራቸው የማይደሰቱት በሥራቸው የተካኑ ለመሆን አስፈላጊውን ጥረት ስላላደረጉ ይሆናል።

እንደ እውነቱ ከሆነ አንድ ሰው ለሚሠራው ማንኛውም ሥራ ተገቢ አመለካከት ካለው ማለትም በሥራው የተካነ ለመሆን የሚጥር ከሆነ ከሥራው ደስታ ማግኘት ይችላል። የ24 ዓመቱ ዊልያም እንዲህ ብሏል፦ “አንድን ሥራ አቅምህ በፈቀደው ሁሉ ሠርተህ ውጤቱን ስትመለከት እርካታ ታገኛለህ። አቋራጭ መንገድ የምትፈልግ ወይም የሚጠበቅብህን ብቻ በማድረግ የምትወሰን ከሆነ ግን እንዲህ ዓይነት ስሜት አይኖርህም።”

ሥራህ ለሌሎች ምን ጥቅም እንደሚያስገኝ አስብ

ከሥራህ ስለምታገኘው የገንዘብ መጠን ብቻ ከማሰብ ተቆጠብ። ከዚህ ይልቅ ራስህን እንደሚከተሉት ያሉትን ጥያቄዎች ጠይቅ፦ ‘ይህ ሥራ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሥራው በትክክል ሳይሠራ ቢቀር ወይም ጭራሹኑ ባይሠራ ምን ሊፈጠር ይችላል? ሥራዬ ለሌሎች ጥቅም የሚያስገኘው እንዴት ነው?’

በተለይ በመጨረሻው ጥያቄ ላይ ማሰብ ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም ከሥራችን የበለጠ እርካታ የምናገኘው ሥራው ሌሎችን እንዴት እንደሚጠቅማቸው ስንመለከት ነው። ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ደንበኞቻችንና አሠሪዎቻችን ከእኛ አገልግሎት በቀጥታ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ሥራችን ጥቅም የሚያስገኘው ለእነዚህ ሰዎች ብቻ አይደለም። የቤተሰባችን አባላትና ሌሎች እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎችም እኛ ከምንሠራው ሥራ ጥቅም ያገኛሉ።

የቤተሰባችን አባላት። አንድ አባወራ የቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን ለማቅረብ ጠንክሮ የሚሠራ ከሆነ ቢያንስ በሁለት መንገዶች ይጠቅማቸዋል። አንደኛ፣ ለኑሮ የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች ማለትም ምግብ፣ ልብስና መጠለያ እንዲያገኙ ያደርጋል። ይህን በማድረግም ‘የራሱ ለሆኑት የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲያቀርብ’ አምላክ የሰጠውን ኃላፊነት ይፈጽማል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ሁለተኛ፣ አንድ ታታሪ የቤተሰብ አስተዳዳሪ ጠንክሮ መሥራት ያለውን ጥቅም ለልጆቹ በተግባር ያስተምራል። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ሼን እንዲህ ብሏል፦ “አባቴ ጠንክሮ በመሥራት ረገድ ምሳሌ የሚሆን ሰው ነው። አብዛኛውን ሕይወቱን ያሳለፈው በአናጺነት ሙያ ሲሆን ጠንካራና ሐቀኛ ሠራተኛ ነው። አንድ ሰው የእጅ ሙያ ኖሮት ሰዎችን የሚጠቅሙ ነገሮችን መሥራቱ ምን ያህል እርካታ እንደሚያስገኝለት ከእሱ ተምሬያለሁ።”

እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች ‘ለተቸገረ ሰው ሊሰጡ የሚችሉት ነገር እንዲኖራቸው በእጃቸው መልካም ተግባር እያከናወኑ በትጋት እንዲሠሩ’ መክሯል። (ኤፌሶን 4:28) በእርግጥም ለራሳችንና ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ነገር ለማቅረብ ጠንክረን የምንሠራ ከሆነ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሌሎች ሰዎችም ለመርዳት የሚያስችል አቅም ይኖረናል። (ምሳሌ 3:27) በመሆኑም ጠንካራ ሠራተኛ መሆን መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ እንድናጣጥም ያስችለናል።

 የሚጠበቅብህን ብቻ በማድረግ አትወሰን

ኢየሱስ በብዙዎች ዘንድ በሚታወቀው የተራራ ስብከቱ ላይ “አንድ ባለሥልጣን አንድ ኪሎ ሜትር እንድትሄድ ቢያስገድድህ ሁለት ኪሎ ሜትር አብረኸው ሂድ” ብሏል። (ማቴዎስ 5:41) ከምትሠራው ሥራ ጋር በተያያዘ ይህ ሐሳብ ሊጠቅምህ የሚችለው እንዴት ነው? የሚጠበቅብህን ብቻ በመሥራት ከመወሰን ይልቅ ከሚጠበቅብህ በላይ ማድረግ የምትችልባቸውን መንገዶች ፈልግ። ግብ አውጣ፤ ሥራህን ከበፊቱ በተሻለ ጥራት ወይም ቅልጥፍና ለማከናወን ጥረት አድርግ። ጥቃቅን ነገሮችን ሳይቀር በጥራት ለመሥራት ሞክር።

ከሚጠበቅብህ በላይ ለመሥራት የምትጥር ከሆነ ሥራህ ይበልጥ አስደሳች ይሆንልሃል። ምክንያቱም ሥራህ በአንተ ቁጥጥር ሥር እንደሆነ ይሰማሃል። ተጨማሪ ነገር እያደረግክ ያለኸው ሌላ ሰው ስላስገደደህ ሳይሆን በራስህ ፍላጎት ነው። (ፊልሞና 14) በዚህ ረገድ በምሳሌ 12:24 (NW) ላይ የሚገኘው “የትጉ ሰዎች እጅ ገዢ ትሆናለች፤ ሥራ ፈት እጆች ግን ለባርነት ይዳረጋሉ” የሚለው ሐሳብ ትዝ ይልህ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ሰዎች አሁንም ቃል በቃል በባርነት ሥር ሊሆኑ ይችላሉ፤ ወይም ደግሞ የግዳጅ ሥራ ያከናውኑ ይሆናል። ይሁን እንጂ የሚጠበቅበትን ነገር ብቻ በማድረግ የሚወሰን ሰው ሁልጊዜ የሚያከናውነው ሌሎች የሚነግሩትን ብቻ ስለሆነ በባርነት ሥር እንዳለ ሊሰማው ይችላል። በራሱ ፍላጎት ተነሳስቶ ከሚጠበቅበት በላይ ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ግን ሕይወቱ በራሱ ቁጥጥር ሥር እንደሆነ ይሰማዋል። ይህ ሰው የራሱ ጌታ ይሆናል ማለት ነው።

ለሥራ ከልክ ያለፈ ቦታ እንዳትሰጥ ተጠንቀቅ

ጠንክሮ መሥራት ጥሩ እንደሆነ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ሕይወት ማለት መሥራት ብቻ እንዳልሆነ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ በትጋት መሥራት እንዳለብን ይገልጻል። (ምሳሌ 13:4) ይሁን እንጂ የሥራ ሱሰኛ መሆንን አያበረታታም። መክብብ 4:6 (NW) “ብዙ በመልፋትና ነፋስን በማሳደድ ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ ጥቂት እረፍት በማድረግ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል” ይላል። ይህ ጥቅስ የሚያስተላልፈው ነጥብ ምንድን ነው? አንድ ሰው ሥራው ጊዜውንና ጉልበቱን ሙሉ በሙሉ የሚያሟጥጥበት ከሆነ በሥራው ውጤት የሚደሰትበት ጊዜ አይኖረውም። በመሆኑም ሥራው ‘ነፋስን የማሳደድ’ ያህል ትርጉም የለሽ ይሆንበታል።

መጽሐፍ ቅዱስ ለሥራ ሚዛናዊ አመለካከት እንድናዳብር ይረዳናል። ሥራችንን በትጋት ማከናወን እንዳለብን የሚናገር ቢሆንም ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይተን እንድናውቅ’ ይመክረናል። (ፊልጵስዩስ 1:10) ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው? ከእነዚህ ነገሮች መካከል ከቤተሰብና ከወዳጆች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ይገኝበታል። ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ግን የአምላክን ቃል እንደ ማንበብና ባነበብነው ነገር ላይ እንደ ማሰላሰል ያሉት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ናቸው።

ለሥራ ተገቢውን ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ከሥራቸው ይበልጥ ደስታ ያገኛሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዊልያም እንዲህ ብሏል፦ “ከቀድሞ አሠሪዎቼ አንዱ ለሥራ ተገቢውን ቦታ በመስጠት ረገድ ምሳሌ የሚሆን ሰው ነበር። ጠንካራ ሠራተኛ ከመሆኑም ሌላ ሥራውን በጥራት ስለሚያከናውን ከደንበኞቹ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለው። ይሁን እንጂ ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ የሥራውን ጉዳይ ትቶ ለቤተሰቡና ለአምልኮው ቅድሚያ ይሰጣል። የሚገርመው ደግሞ ከማውቃቸው በጣም ደስተኛ ሰዎች አንዱ እሱ ነው!”