በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ባለሥልጣናት ከሕዝብ ያገኙትን ሥልጣን ለግል ጥቅማቸው ሲያውሉት ይታያል። እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት በጥንት ዘመንም ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ፍርድ ነክ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ሰዎች ጉቦ መቀበል እንደሌለባቸው የሚገልጽ ሕግ ይዟል፤ ይህ፣ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ከ3,500 ዓመታት በፊትም ይፈጸም እንደነበር ይጠቁማል። (ዘፀአት 23:8) እርግጥ ነው፣ ሙስና ሲባል ጉቦ መቀበል ማለት ብቻ አይደለም። ሙሰኛ የሆኑ የሕዝብ ባለሥልጣናት የሌሎችን ንብረት ይወርሳሉ፤ አንዳንድ አገልግሎቶችን ለግል ጥቅማቸው ያውላሉ፤ አልፎ ተርፎም ገንዘብ ይሰርቃሉ። በተጨማሪም ጓደኞቻቸውንና ዘመዶቻቸውን ለመርዳት ሲሉ ሥልጣናቸውን አላግባብ ይጠቀሙበታል።

ሙስና በማንኛውም ሰብዓዊ ድርጅት ውስጥ ሊኖር ቢችልም በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ግን እጅግ ተስፋፍቶ ይገኛል። በመላው ዓለም ያሉ ብዙ ሰዎች እጅግ ሙሰኛ እንደሆኑ አድርገው የሚፈርጇቸው አምስት ተቋማት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ፖሊስ፣ የሕዝብ ባለሥልጣናት፣ ሕግ አውጪዎችና ዳኞች መሆናቸውን ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው ተቋም በ2013 ያወጣው ግሎባል ኮራፕሽን ባሮሜትር የተሰኘው ጽሑፍ ዘግቧል። ችግሩን አጉልተው የሚያሳዩ ጥቂት ዘገባዎችን እስቲ ተመልከት፦

  • አፍሪካ፦ በ2013፣ በደቡብ አፍሪካ 22,000 ያህል የሕዝብ ባለሥልጣናት በሙስና ተከሰው ነበር።

  • ደቡብ አሜሪካ፦ በ2012 በብራዚል 25 ባለሥልጣናት ፖለቲካዊ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ የሕዝብን ገንዘብ አላግባብ ጥቅም ላይ በማዋላቸው ተፈርዶባቸው ነበር። ከተፈረደባቸው ሰዎች መካከል በአገሪቱ ውስጥ ሁለተኛውን ከፍተኛ ሥልጣን የያዙት ግለሰብ ይኸውም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዋና ሹም ይገኙበታል።

  • እስያ፦ በደቡብ ኮሪያ፣ ሶል ከተማ ውስጥ በ1995 አንድ የገበያ አዳራሽ ተደርምሶ 502 ሰዎች ሞተው ነበር። የገበያ አዳራሹን የገነቡት ሕንፃ ተቋራጮች ለከተማዋ ባለሥልጣናት ጉቦ በመስጠት የጥራት ደረጃውን ባልጠበቀ የግንባታ ዕቃ እንደተጠቀሙና አንድ ሕንፃ እንዲያሟላቸው የሚጠበቁ የደኅንነት ደንቦችን እንደተላለፉ ጉዳዩን የያዙት መርማሪዎች ደርሰውበታል።

  • አውሮፓ፦ የአውሮፓ አገራት የውስጥ ጉዳይ ኮሚሽነር የሆኑት ሲሲሊያ ማልምስትሮም እንደገለጹት ከሆነ “[በአውሮፓ የሙስና] ችግር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተስፋፋ መጥቷል።” እኚህ ሴት አክለው “የፖለቲካው ሥርዓት፣ ሙስናን ከሥሩ ነቅሎ ለማስወገድ የሚያስችል ጥንካሬ የጎደለው ይመስላል” በማለት ተናግረዋል።

ሙስና በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ሥር የሰደደ ችግር ነው። ከፀረ ሙስና ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚያጠኑት ፕሮፌሰር ሱዛን ሮዝአከርማን፣ ሙስናን ለማስወገድ “በመንግሥት አሠራር ላይ መሠረታዊ ለውጥ ማድረግ” እንደሚያስፈልግ ጽፈዋል። ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ ይመስል ይሆናል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከዚህም የሚበልጡ ለውጦችን ማድረግ እንደሚቻልና ይህ መሆኑም እንደማይቀር ይገልጻል።