በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ወደ አምላክ መቅረብ ትችላለህ

ከአምላክ ጋር ትነጋገራለህ?

ከአምላክ ጋር ትነጋገራለህ?

የቅርብ ጓደኛሞች በአካል ተገናኝተው፣ በስልክ፣ በኢ-ሜይል፣ በቪዲዮም ይሁን በደብዳቤ አማካኝነት አዘውትረው ለመነጋገር ጥረት ያደርጋሉ። ወደ አምላክ ለመቅረብም ከእሱ ጋር አዘውትረን መነጋገር ያስፈልገናል። ይሁንና ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

ሐሳባችንን ለይሖዋ መንገር የምንችለው በጸሎት አማካኝነት ነው። ይሁን እንጂ አምላክን የምናነጋግረው እኩያችንን በምናነጋግርበት መንገድ አይደለም። በምንጸልይበት ጊዜ እያናገርን ያለነው የአጽናፈ ዓለም ልዑል የሆነውን ፈጣሪ እንደሆነ መገንዘብ አለብን። ይህም ጸሎታችንን ጥልቅ አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ እንድናቀርብ ሊያነሳሳን ይገባል። አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማልን ከፈለግን ልናሟላቸው የሚገቡ አንዳንድ መሥፈርቶችም አሉ። ከእነዚህ መሥፈርቶች መካከል ሦስቱን እንመልከት።

አንደኛ፣ ጸሎት መቅረብ ያለበት ለይሖዋ ብቻ ነው፤ ለኢየሱስ፣ ቅዱሳን ተብለው ለሚጠሩ አካላት ወይም ለምስሎች ጸሎት ማቅረብ የለብንም። (ዘፀአት 20:4, 5) መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ፊልጵስዩስ 4:6) ሁለተኛ፣ ጸሎታችን መቅረብ ያለበት የአምላክ ልጅ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። ኢየሱስ ራሱ “በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት ገልጿል። (ዮሐንስ 14:6) ሦስተኛ፣ ጸሎታችን ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ መሆን አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ “የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል” የሚል ሐሳብ ይዟል። *1 ዮሐንስ 5:14

የሚቀራረቡ ጓደኛሞች በተቻለ መጠን አዘውትረው እርስ በርስ ይነጋገራሉ

እርግጥ ነው፣ ሁልጊዜ ሐሳቡን የሚገልጸው አንደኛው ወገን ብቻ ከሆነ ወዳጅነቱ ዘላቂ ሊሆን አይችልም። ጓደኛሞች እርስ በርስ መነጋገር እንዳለባቸው ሁሉ እኛም አምላክ እንዲያነጋግረን መፍቀድና እሱ ሲናገር ማዳመጥ ይኖርብናል። አምላክ ለእኛ የሚናገረው እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ?

በዛሬው ጊዜ ይሖዋ አምላክ ለእኛ “የሚናገረው” በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ከቅርብ ጓደኛህ የተላከ አንድ ደብዳቤ ደረሰህ እንበል። ደብዳቤውን ካነበብክ በኋላ “ጓደኛዬ እኮ እንዲህ አለኝ!” ብለህ በደስታ ለሌሎች ትናገር ይሆናል። ሆኖም ጓደኛህ የነገረህ በአፉ ሳይሆን በጽሑፍ ነው። በተመሳሳይም አንተም መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ይሖዋ እንዲያናግርህ እየፈቀድክለት ነው ማለት ነው። በመሆኑም በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ጂና “አምላክ ወዳጁ አድርጎ እንዲመለከተኝ ከፈለግሁ ለእኛ የላከልንን ‘ደብዳቤ’ ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንዳለብኝ ይሰማኛል” ብላለች። አክላም “መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበቤ ወደ አምላክ ይበልጥ እንድቀርብ አድርጎኛል” በማለት ተናግራለች። ታዲያ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማንበብ ይሖዋ እንዲያናግርህ ትፈቅድለታለህ? እንዲህ ማድረግህ የአምላክ ወዳጅ እንደሆንክ እንዲሰማህ ያደርጋል።

^ አን.5 በጸሎት አማካኝነት ወደ አምላክ መቅረብ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 17 ተመልከት።