ዮሴፍ ሞቃታማውን አየር ወደ ውስጥ ሲስብ በውኃ ላይ የሚበቅሉት አበቦች ሽታ አወደው። የግመሎች ቅፍለት የያዙ ሲራራ ነጋዴዎች ዮሴፍን ይዘው የተንጣለለውን የናይል ደለላማ መሬት አቋርጠው እየወረዱ ነው። ነጋዴዎቹ የወንዙን ዳርቻ ተከትለው ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ በመስመር ሲጓዙ እንዲሁም በውኃ ውስጥ የሚንቦራጨቁት ሽመላዎችና ጋጋኖዎች ቅፍለቱን አይተው ደንብረው ሲበርሩ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ዮሴፍ አሁንም በመቶዎች ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘውን መንደሩን እያሰበ ነው፤ በኬብሮን ከፍታ መሬት ላይ የሚገኘው መንደሩ ነፋሻማ አካባቢ ነው፤ አሁን ግን ዮሴፍ ያለው የተለየ ዓለም ውስጥ ነው።

ዝንጀሮዎች በተምርና በበለስ ዛፎች አናት ላይ ሆነው ይንጫጫሉ። በመንገድ ላይ ያሉ ሰዎች የሚያወሩት ነገርም ቢሆን ለዮሴፍ ከዝንጀሮዎቹ ጫጫታ ብዙም የተለየ አልነበረም፤ ምክንያቱም የሚነጋገሩበትን ቋንቋ መረዳት አይችልም። ምናልባትም አንዳንድ ቃላትን ወይም ሐረጎችን ለመረዳት ጥረት አድርጎ ይሆናል። እንዲያውም አንዳንድ ቃላትን ተምሮ ሊሆን ይችላል። ዮሴፍ እንደገና የትውልድ አገሩን የማየት አጋጣሚ እንደማያገኝ ተሰምቶት ነበር።

ዮሴፍ ገና 17 ወይም 18 ዓመት ቢሆነው ነው፤ ያጋጠሙት ችግሮች ግን እንኳን ለእሱ ለትላልቅ ሰዎችም በጣም የሚከብዱ ናቸው። የገዛ ወንድሞቹ፣ አባታቸው ከእነሱ ይበልጥ ዮሴፍን በመውደዱ በቅናት ስላረሩ ሊገድሉት ፈልገው ነበር። የኋላ ኋላ ግን ለእነዚህ ነጋዴዎች ሸጡት። (ዘፍጥረት 37:2, 5, 18-28) እነዚህ ነጋዴዎች ለሳምንታት ሲጓዙ ከቆዩ በኋላ ወደ ግብፅ ዋና ከተማ እየተቃረቡ ነው፤ ዮሴፍንና ሌሎች ውድ ሸቀጦቻቸውን ሸጠው ስለሚያገኙት ትርፍ በማሰብ በደስታ መፍነክነክ ጀምረዋል። ዮሴፍ ተስፋ ቆርጦ መንፈሱ እንዳይሰበር ማድረግ የቻለው እንዴት ነው? እኛስ በሕይወታችን የሚያጋጥሙን ውጣ ውረዶች እምነታችንን እንዳያጠፉት መከላከል የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ከዮሴፍ የምንማረው ብዙ ነገር አለ።

ይሖዋ “ከዮሴፍ ጋር ነበረ”

“ዮሴፍ ወደ ግብፅ [ተወሰደ]፤ ከፈርዖን ሹማምንት አንዱ የሆነውም የዘበኞች አለቃ፣ ግብፃዊው ጲጥፋራ ወደዚያ ከወሰዱት ከእስማኤላውያን ነጋዴዎች እጅ ገዛው።” (ዘፍጥረት 39:1) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው ይህ አጭር ሐሳብ ይህ ወጣት ለሁለተኛ ጊዜ ለባርነት ሲሸጥ ሊሰማው የሚችለውን የውርደት ስሜት እንድንገምት ይረዳናል። ዮሴፍ የተቆጠረው ልክ እንደ ሸቀጥ ነው! ዮሴፍ የፈርዖን ሹም የነበረውን አዲሱን ጌታውን ተከትሎ በሕዝብ የተጨናነቁትን የከተማ ጎዳናዎች በማቋረጥ ወደ አዲሱ ቤቱ መጓዝ ጀመረ።

በመጨረሻ ቤት ደረሱ! ቤቱ ዮሴፍ ከሚያውቀው ቤት በእጅጉ የተለየ ነበር። ዮሴፍ ያደገው በግ አርቢ በሆነ ዘላን ቤተሰብ ውስጥ ነው፤ ቤተሰቦቹ የሚኖሩት በድንኳን ውስጥ ሲሆን ብዙ ጊዜ ጓዛቸውን ነቅለው ከቦታ ወደ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ። እዚህ ግብፅ ውስጥ ደግሞ እንደ ጲጥፋራ ያሉ ባለጸጋ ግብፃውያን የሚኖሩት በሚያማምሩና ደማቅ ቀለም በተቀቡ ቤቶች ውስጥ ነው። የጥንቶቹ ግብፃውያን ደንገልና ሌሎች የውኃ ተክሎች የሚበቅሉባቸው ኩሬዎች እንዲሁም የጥላ ዛፎች ያሏቸው መናፈሻዎችን ይወዱ እንደነበር የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች ዘግበዋል። አንዳንዶቹ ቤቶች ዙሪያቸውን መናፈሻ ቦታ ያላቸው ሲሆን ነፋስ ለመቀበል የሚያስችል በረንዳ፣ አየር እንደ ልብ የሚያስገቡ ከፍ ብለው የተሠሩ መስኮቶች እንዲሁም ትልቅ የመመገቢያ አዳራሽና ለአገልጋዮች የተዘጋጁ ክፍሎችን ጨምሮ ብዙ ክፍሎች ያሏቸው ናቸው።

ዮሴፍ እንዲህ ባለው የቅንጦት ሕይወት ከልክ በላይ ተማርኮ ይሆን? እንደዚያ ማለት ይከብዳል። ዮሴፍን በወቅቱ ያሳሰበው ብቸኝነቱ ሳይሆን አይቀርም። የግብፃውያን ቋንቋ፣ አለባበስና የፀጉር አያያዛቸው ለእሱ እንግዳ ነበር፤ በተለይ ደግሞ  ሃይማኖታቸው ከእሱ በጣም የተለየ ነበር። ግብፃውያን ብዙ አማልክት ያሏቸው፣ ጥንቆላና አስማት የሚፈጽሙ እንዲሁም ሞትና ከሞት በኋላ ያለው ሕይወት ከልክ በላይ የሚያሳስባቸው ሕዝቦች ነበሩ። ይሁንና ዮሴፍ በብቸኝነት ስሜት እንዳይደቆስ የረዳው አንድ ነገር ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ይሖዋ “ከዮሴፍ ጋር ነበረ።” (ዘፍጥረት 39:2) ዮሴፍ የልቡን አውጥቶ ለአምላክ እንደጸለየ ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ . . . ቅርብ ነው” ይላል። (መዝሙር 145:18) ዮሴፍ ወደ አምላኩ እንዲቀርብ የረዳው ሌላው ነገርስ ምንድን ነው?

ይህ ወጣት ተስፋ አልቆረጠም፤ ከዚህ ይልቅ ሥራውን በጥሩ ሁኔታ ማከናወኑን ቀጠለ። ይሖዋም ይህን ተመልክቶ የባረከው ሲሆን ዮሴፍ ብዙም ሳይቆይ በጌታው ፊት ሞገስ ማግኘት ቻለ። ጲጥፋራ የዮሴፍ ቤተሰቦች የሚያመልኩት ይሖዋ የተባለው አምላክ ይህን ወጣት እየባረከው እንደሆነ አስተዋለ፤ ለዮሴፍ የመጣው በረከት ደግሞ ለእሱም እንደተረፈ ጥርጥር የለውም። ዮሴፍ ቀስ በቀስ የጌታውን አክብሮት እያተረፈ ሄደ፤ እንዲያውም ጲጥፋራ በዚህ ጎበዝ ወጣት ላይ ከፍተኛ እምነት ስለጣለ ባለው ነገር ሁሉ ላይ ሾመው።—ዘፍጥረት 39:3-6

ዮሴፍ በዛሬው ጊዜ አምላክን ለሚያገለግሉ ወጣቶች ግሩም ምሳሌ ትቷል። ለምሳሌ ያህል፣ እነዚህ ወጣቶች በትምህርት ቤት በሚሆኑበት ወቅት ካሉበት አካባቢ የተለዩ እንደሆኑ የሚሰማቸው ጊዜ ሊኖር ይችላል፤ ምክንያቱም በትምህርት ቤት የሚያገኟቸው ሰዎች በመናፍስታዊ ድርጊቶች የሚደሰቱ እንዲሁም ስለ ሕይወት ብሩሕ የሆነ አመለካከት የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። አንተ ያለህበት ሁኔታም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ከሆነ ይሖዋ አሁንም እንዳልተለወጠ አስታውስ። (ያዕቆብ 1:17) አሁንም ቢሆን ይሖዋ ለእሱ ምንጊዜም ታማኝ ከሚሆኑና እሱን ለማስደሰት የሚችሉትን ያህል ጥረት ከሚያደርጉ ሁሉ ጋር ይሆናል። ይሖዋ እንዲህ ያሉትን ሰዎች አብዝቶ ይባርካቸዋል፤ ለአንተም እንዲሁ ያደርግልሃል።

ዘገባው በመቀጠል ዮሴፍ እያደገ እንደሄደ ይናገራል። ይህ ወጣት አድጎ “ጥሩ ቁመና ያለውና መልከ መልካም” ሰው ሆነ። እነዚህ ቃላት ዮሴፍ አደጋ ሊያጠላበት እንደሚችል ይጠቁማሉ፤ ምክንያቱም አካላዊ ውበት ብዙውን ጊዜ ተገቢ ያልሆነ ትኩረት ሊስብ ይችላል።

የጲጥፋራ ሚስት ታማኝ በሆነው በዮሴፍ ላይ ዓይኗን ጣለችበት

‘ዮሴፍ አልሰማትም’

ዮሴፍ ታማኝነትን ከፍ አድርጎ ይመለከታል፤ የጲጥፋራ ሚስት ግን እንዲህ አይደለችም። መጽሐፍ ቅዱስ “የጌታው ሚስት ዐይኗን ጣለችበት፤ አፍ አውጥታም፣ ‘አብረኸኝ ተኛ’ አለችው” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 39:7) ዮሴፍ ይህች አምላክን የማታመልክ ሴት ያቀረበችለት ዓይን ያወጣ ጥያቄ ይፈትነው ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዮሴፍ በእሱ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች ካላቸው የፆታ ስሜት ነፃ እንደሆነ አይናገርም፤ በቅንጦት የምትኖረው የጲጥፋራ ሚስትም ብትሆን ቆንጆ ሴት አይደለችም ብለን እንድናስብ የሚያደርግ ምንም ምክንያት የለም። ታዲያ ዮሴፍ ከዚህች ሴት ጋር ቢተኛ ጌታው ፈጽሞ ሊያውቅ እንደማይችል ያስብ ይሆን? ከጲጥፋራ ሚስት ጋር እንዲህ ዓይነት ቅርርብ መፍጠሩ ሊያስገኝለት የሚችለው ቁሳዊ ጥቅም ያማልለው ይሆን?

 እውነቱን ለመናገር በዮሴፍ አእምሮ ውስጥ የተመላለሰውን ሐሳብ በሙሉ ማወቅ አንችልም። በልቡ ውስጥ ምን እንደነበረ ግን በእርግጠኝነት ማወቅ እንችላለን። ለጲጥፋራ ሚስት የሰጠው መልስ ይህን በግልጽ ያሳያል፦ “ጌታዬ ያለውን ሁሉ በኀላፊነት ስለ ሰጠኝ፣ በቤቱ ውስጥ ስላለው ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። በዚህ ቤት ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት ያለው ማንም የለም፤ እርሱ ያልሰጠኝ ነገር ቢኖር፣ አንቺን ብቻ ነው፤ ያውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው፤ ታዲያ፣ እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?” (ዘፍጥረት 39:8, 9) ይህ ወጣት እነዚህን ቃላት በቆራጥነት መንፈስ ሲናገር ይታይህ። የጲጥፋራ ሚስት ከእሱ ጋር ለመፈጸም የፈለገችውን ነገር ማሰብ እንኳ ዘግንኖታል። ለምን?

ዮሴፍ እንደተናገረው ጌታው እሱን ያምነዋል። ጲጥፋራ ከሚስቱ በቀር በቤቱ ውስጥ ያለውን ነገር በሙሉ ለዮሴፍ ሰጥቶታል። ታዲያ ይህን ያህል የሚያምነውን ጌታውን እንዴት ይከዳዋል? ይህን ማሰብ እንኳ ይዘገንነዋል። ይሁን እንጂ ከዚህ ይበልጥ የሚዘገንነው በአምላኩ በይሖዋ ላይ ኃጢአት የመሥራቱ ሐሳብ ነው። ዮሴፍ፣ አምላክ ስለ ጋብቻና ስለ ታማኝነት ያለውን አመለካከት በተመለከተ ከወላጆቹ ብዙ ነገር ተምሯል። የመጀመሪያውን ጋብቻ ያስፈጸመው ይሖዋ ራሱ ነው፤ እንዲሁም ስለ ጋብቻ ያለውን አመለካከት በግልጽ ተናግሯል። ይሖዋ፣ ባልና ሚስት አንድ ላይ እንዲጣመሩና “አንድ ሥጋ” እንዲሆኑ እንደሚፈልግ ገልጿል። (ዘፍጥረት 2:24) ይህንን ጥምረት ለማፍረስ በመሞከራቸው የአምላክ ቁጣ ሊደርስባቸው የነበሩ ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ የዮሴፍ ቅድመ አያት የነበረውን የአብርሃምን እና የዮሴፍ አያት የነበረውን የይስሐቅን ሚስት ለመውሰድ አስበው የነበሩ ሰዎች ከአምላክ ቁጣ ያመለጡት ለጥቂት ነው። (ዘፍጥረት 20:1-3፤ 26:7-11) ዮሴፍ ከእነዚህ ታሪኮች ትምህርት አግኝቷል፤ በመሆኑም ያገኘውን ትምህርት በሕይወቱ ተግባራዊ ማድረግ ፈልጎ ነበር።

የጲጥፋራ ሚስት ዮሴፍ በሰጣት መልስ አልተደሰተችም። ምክንያቱም ይህ ተራ ባሪያ ጥያቄዋን አለመቀበሉ ሳያንስ ያቀረበችለት ግብዣ “ክፉ ድርጊት” እንደሆነ ተናግሯል! እሷ ግን መወትወቷን ቀጠለች። ምናልባትም ክብሯ እንደተነካ ተሰምቷት ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ ዮሴፍን እሺ ለማሰኘት ቆርጣ ተነሳች። በመሆኑም ኢየሱስን ከፈተነው ከሰይጣን ጋር የሚመሳሰል ነገር አድርጋለች። ሰይጣንም ያደረገው ሙከራ ከሽፎበታል፤ ሆኖም ተስፋ ቆርጦ ከመተው ይልቅ “ሌላ አመቺ ጊዜ እስኪያገኝ ድረስ” ጠብቋል። (ሉቃስ 4:13) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ታማኝ ሰዎች ቆራጥ መሆንና በአቋማቸው መጽናት ያስፈልጋቸዋል። ዮሴፍም እንዲህ ዓይነት ሰው መሆኑን አሳይቷል። የጲጥፋራ ሚስት “በየቀኑ” ብትጎተጉተውም ከአቋሙ ፍንክች አላለም። ዮሴፍ፣ የጲጥፋራን ሚስት ‘እንዳልሰማት’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፍጥረት 39:10) ይሁን እንጂ የጲጥፋራ ሚስት ያሰበችውን ለመፈጸም ቆርጣ ተነስታ ነበር።

አገልጋዮቹ በሙሉ ቤት የማይኖሩበትን ጊዜ መረጠች። ዮሴፍ ሥራውን ለማከናወን ወደ ቤት መግባት እንደሚያስፈልገው ታውቃለች። በመሆኑም ዮሴፍ ወደ ቤት ሲገባ ልታጠምደው ተዘጋጀች። ልብሱን ጨምድዳ በመያዝ “አብረኸኝ ተኛ” በማለት ለመጨረሻ ጊዜ ጥያቄዋን አቀረበች። በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ልብሱን መንጭቆ ለማስለቀቅ ሞከረ። እሷ ግን ጨምድዳ ያዘችው። ስለዚህ ልብሱን እጇ ላይ ትቶላት ሸሽቶ ወጣ!—ዘፍጥረት 39:11, 12

ዮሴፍ ያደረገው ነገር ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት “ከዝሙት ሽሹ” በማለት የሰጠውን ማሳሰቢያ ያስታውሰን ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) ዮሴፍ ለሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቷል! የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ለአምላክ የሥነ ምግባር ሕጎች ምንም ደንታ ከሌላቸው ሰዎች ጋር ያገናኘን ይሆናል፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ለሚያሳድሩብን ተጽዕኖ እጅ መስጠት የለብንም። የሚያስከፍለን ዋጋ ምንም ይሁን ምን አስፈላጊ ከሆነ መሸሽ አለብን።

እርግጥ ነው፣ ዮሴፍ እንዲህ ዓይነት እርምጃ መውሰዱ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎታል። የጲጥፋራ ሚስት ልትበቀለው ፈለገች። በመሆኑም ወዲያውኑ እየጮኸች አገልጋዮቹን መጣራት ጀመረች። ዮሴፍ ሊደፍራት እንደሞከረና እሷ ስትጮኽ ሸሽቶ እንዳመለጠ ነገረቻቸው። ዮሴፍን ለመወንጀል ባሏ እስኪመለስ ድረስ ልብሱን ይዛ ቆየች። ጲጥፋራ ወደ ቤት ተመልሶ ሲመጣ ያንኑ ውሸት ደግማ ተናገረች፤ ጲጥፋራ ይህን ባዕድ ሰው ወደ ቤት በማምጣቱ ለደረሰባት ነገር ተጠያቂው እሱ እንደሆነ በተዘዋዋሪ ገለጸች። የጲጥፋራ ምላሽ ምን ነበር? ታሪኩ በጣም ‘እንደተቆጣ’ ይናገራል። ከዚያም ዮሴፍን ወደ እስር ቤት አስገባው።—ዘፍጥረት 39:13-20

“እግሮቹ በእግር ብረት ተላላጡ”

በዚያ ዘመን ስለነበሩት የግብፃውያን እስር ቤቶች ብዙ የምናውቀው ነገር የለም። የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች የግብፃውያን እስር ቤቶችን ፍርስራሽ አግኝተዋል፤ እነዚህ እስር ቤቶች ከመሬት በታች ተቆፍረው የተሠሩ ጨለማ ክፍሎችና ሌሎች ጠባብ ክፍሎች ያሏቸው እንደ ምሽግ ያሉ ቦታዎች ነበሩ። ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ የታሰረበትን ቦታ ለመግለጽ ቃል በቃል ሲተረጎም “ጉድጓድ” የሚል ፍቺ ያለው ቃል ተጠቅሟል፤ ይህም እስር ቤቱ ብርሃን የሌለውና በቀላሉ መውጣት የማይቻልበት ስፍራ እንደሆነ ይጠቁማል። (ዘፍጥረት 40:15 NW፣ የግርጌ  ማስታወሻ) በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው “እግሮቹ በእግር ብረት ተላላጡ፤ በዐንገቱም የብረት ማነቆ ገባ” የሚለው ዘገባ ዮሴፍ ተጨማሪ ሥቃይ ደርሶበት እንደነበረ ያሳያል። (መዝሙር 105:17, 18) ግብፃውያን አንዳንድ ጊዜ የእስረኞችን እጅ በብረት የፊጥኝ ያስሩ ነበር፤ ሌሎቹን ደግሞ አንገታቸው ላይ የብረት ማነቆ ያስገቡባቸው ነበር። ዮሴፍ የደረሰበት እንግልት በጣም አሠቃይቶት መሆን አለበት፤ ይህ ሁሉ የደረሰበት ግን ምንም ጥፋት ሳይሠራ ነው።

ከዚህም በላይ ዮሴፍ እንዲህ ካለው መከራ ወዲያውኑ አልተገላገለም። ዘገባው “ዮሴፍም እዚያው እስር ቤት ውስጥ ቆየ” (NW) በማለት ይናገራል። ዮሴፍ በዚያ መጥፎ ሥፍራ ለዓመታት ቆይቷል! * ደግሞም ከእስር ቤት ይውጣ አይውጣ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ዮሴፍ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ቀን ቀንን እየተካ ሳምንታት ብሎም ወራት ተቆጠሩ፤ ይሁን እንጂ ዮሴፍ ተስፋ አልቆረጠም፤ ለዚህ የረዳው ምንድን ነው?

ዘገባው ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ “ዮሴፍ እዚያ እስር ቤት ባለበት ጊዜ ሁሉ፣ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ቸርነቱንም አበዛለት” ይላል። (ዘፍጥረት 39:21) የትኛውም የእስር ቤት ግድግዳ፣ ሰንሰለት ወይም ጨለማ ክፍል ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ቸርነት እንዳያሳይ ማገድ አይችልም። (ሮም 8:38, 39) ዮሴፍ በሰማይ ላለው ለሚወደው አባቱ ጭንቀቱን በጸሎት ሳይገልጽ አይቀርም፤ በመሆኑም “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ብቻ ሊሰጥ የሚችለውን ሰላምና መረጋጋት አግኝቶ መሆን አለበት። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ይሖዋ ለዮሴፍ ሌላስ ምን ነገር አድርጎለታል? መጽሐፍ ቅዱስ “በወህኒ አዛዡም ዘንድ ሞገስን ሰጠው” ይላል።

እስረኞቹ የሚሠሩት ሥራ ይሰጣቸው እንደነበረ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል፤ ስለዚህ ዮሴፍ አሁንም የይሖዋን በረከት ማግኘት የሚችልበት አጋጣሚ ተከፈተለት። ዮሴፍ የተሰጠውን ማንኛውም ሥራ በትጋት ማከናወን ጀመረ፤ ሌላውን ነገር ግን ለይሖዋ ተወው። ይሖዋ ዮሴፍን ስለባረከው ልክ በጲጥፋራ ቤት እንደነበረው ሁሉ በእስር ቤት ውስጥም የሌሎችን አመኔታና አክብሮት አተረፈ። ታሪኩ እንዲህ ይላል፦ “ስለዚህ የወህኒው አዛዥ ዮሴፍን የእስረኞች ሁሉ አለቃ አደረገው፤ በእስር ቤቱ ላለውም ነገር ሁሉ ኀላፊ ሆነ። እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ሆኖ ሥራውን ሁሉ ያሳካለት ስለ ነበር የወህኒ ቤት አዛዡ በዮሴፍ ኀላፊነት ሥር ስላለው ስለማንኛውም ጕዳይ ሐሳብ አይገባውም ነበር።” (ዘፍጥረት 39:22, 23) ዮሴፍ ይሖዋ እየተንከባከበው መሆኑን ማወቁ ምንኛ አጽናንቶት ይሆን!

ዮሴፍ እስር ቤት ቢሆንም ይሖዋ እንዲባርከው የሚያደርግ ነገር አድርጓል

እኛም በሕይወታችን የተለያዩ ውጣ ውረዶች ሊያጋጥሙን አልፎ ተርፎም ግፍ ሊፈጸምብን ይችላል፤ ይሁን እንጂ ከዮሴፍ እምነት ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ምንጊዜም ወደ ይሖዋ የምንጸልይ፣ ትእዛዛቱን በታማኝነት የምንጠብቅና በእሱ ፊት ትክክል የሆነውን ለማድረግ በትጋት የምንሠራ ከሆነ ይሖዋ እንዲባርከን አጋጣሚ እንከፍትለታለን። ይሖዋ ለዮሴፍ ያዘጋጀለት ሌሎች ታላላቅ በረከቶችም አሉ፤ በዚህ ዓምድ ሥር በሚወጣው ቀጣይ ርዕስ ላይ ስለ እነዚህ በረከቶች እንመለከታለን።

^ አን.23 ዮሴፍ ወደ ጲጥፋራ ቤት ሲመጣ 17 ወይም 18 ዓመት ገደማ እንደሚሆነው እንዲሁም በዚያ እያለ አድጎ ሙሉ ሰው እንደሆነ የሚጠቁም ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እናገኛለን፤ ስለዚህ በጲጥፋራ ቤት ለተወሰኑ ዓመታት ቆይቶ ሊሆን ይችላል። ከእሥር ቤት ሲለቀቅ ደግሞ 30 ዓመት ሆኖት ነበር።—ዘፍጥረት 37:2፤ 39:6 NW፤ ዘፍጥረት 41:46