ያለፉትን ርዕሶች ስታነብብ የይሖዋ ምሥክሮች ለአምላክ መንግሥት ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡ ሳታስተውል አልቀረህም። ምናልባትም ወደፊት እንደምናገኛቸው ከተገለጹት በረከቶች አንዳንዶቹ ትኩረትህን ስበውት ይሆናል። በሌላ በኩል ግን እንዲህ ያሉት ተስፋዎች እንዲሁ የሕልም እንጀራ እንደሆኑ አስበህ ይሆናል።

የሰማኸውን ነገር ሁሉ ለማመን አለመቸኮልህ ብልህነት ነው። (ምሳሌ 14:15) በዚህ ረገድ የምታሳየው ጥንቃቄ በጥንቷ ቤርያ የነበሩት ሰዎች ከወሰዱት እርምጃ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። * የቤርያ ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው ምሥራች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲነገራቸው የሰሙትን ነገር ተቀበሉ፤ ይሁን እንጂ የተቀበሉት እንዲሁ በስሜት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ “የሰሙት ነገር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ” ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥንቃቄ መርምረዋል። (የሐዋርያት ሥራ 17:11) በሌላ አነጋገር፣ የቤርያ ሰዎች የሰሙትን ምሥራች ቅዱሳን መጻሕፍት ከሚናገሩት ነገር ጋር አመሳክረዋል። ከዚያም ምሥራቹ በእርግጥ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አመኑ።

የይሖዋ ምሥክሮች አንተም እንዲሁ እንድታደርግ ይጋብዙሃል። መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ለማስተማር ባደረግነው ዝግጅት አማካኝነት የይሖዋ ምሥክሮች ከአምላክ መንግሥት ጋር በተያያዘ ያላቸው እምነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆን አለመሆኑን እንድትመረምር ልንረዳህ እንችላለን።

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ ስለ አምላክ መንግሥት እንድታውቅ ብቻ ሳይሆን በሰዎች አእምሮ ውስጥ ለሚጉላሉ ጥያቄዎች መልስ እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል።

ከሁሉ በላይ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ ‘ወደ አምላክ እንድትቀርብ’ ይረዳሃል። (ያዕቆብ 4:8) ወደ አምላክ ይበልጥ እየቀረብክ መሄድህ የአምላክ መንግሥት አሁንም ሆነ ለዘላለም ከሚያመጣቸው በረከቶች ተቋዳሽ እንድትሆን ያስችልሃል። ኢየሱስ ራሱ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ እንዲህ ብሏል፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተና ስለላክኸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል አለባቸው።”—ዮሐንስ 17:3

 

^ አን.4 ቤርያ በጥንቷ መቄዶንያ የምትገኝ ከተማ ነበረች።