የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ የምንጸልየው ለምንድን ነው?

ስለ አምላክ መንግሥትና ወደፊት ስለሚያከናውናቸው ነገሮች የበለጠ ለማወቅ ትፈልጋለህ?

የአምላክ መንግሥት በሰማይ የተቋቋመ መስተዳድር ነው። ይህ መንግሥት በምድር ላይ ጽድቅና ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል፤ ኢየሱስ መንግሥቱ እንዲመጣ እንዲጸልዩ ተከታዮቹን ያስተማራቸው ለዚህ ነው። ዓመፅን፣ ግፍን ወይም በሽታን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ የሚችል የሰው መንግሥት የለም፤ ይህን ማድረግ የሚችለው እንዲሁም የሚያደርገው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው። አምላክ ልጁን ኢየሱስን የዚህ መንግሥት ንጉሥ እንዲሆን መርጦታል። በተጨማሪም ይሖዋ ከኢየሱስ ተከታዮች መካከል ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚገዙ ሰዎችን መርጧል።—ሉቃስ 11:2ን እና ሉቃስ 22:28-30ን አንብብ።

በቅርቡ የአምላክ መንግሥት የአምላክን አገዛዝ በሚቃወሙ ሁሉ ላይ እርምጃ ይወስዳል። በመሆኑም የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ ስንጸልይ አምላክ ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ አጥፍቶ በምትኩ የእሱ መንግሥት እንዲያስተዳድረን መለመናችን ነው።—ዳንኤል 7:13, 14ን እና ራእይ 11:15, 18ን አንብብ።

የአምላክ መንግሥት ለሰዎች ጥቅም ያስገኛል የምንለው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ርኅሩኅ ስለሆነ ከሁሉ የተሻለ ንጉሥ ነው። በተጨማሪም የአምላክ ልጅ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ኃይል አለው፤ በመሆኑም አምላክ እንዲረዳቸው የሚለምኑትን ሁሉ ሊረዳቸው ይችላል።—መዝሙር 72:8, 12-14ን አንብብ።

የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ ከልብ የሚጸልዩና ሕይወታቸውን ከአምላክ ፈቃድ ጋር አስማምተው የሚኖሩ ሁሉ ይህ መንግሥት ከሚያስገኘው ጥቅም ተቋዳሽ ይሆናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን መማር ፈጽሞ የማያስቆጭ ነው።—ሉቃስ 18:16, 17ን እና ዮሐንስ 4:23ን አንብብ።