በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ጥቅምት 2014

 መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ሕይወቴ በራሴ ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር

ሕይወቴ በራሴ ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር
  • የትውልድ ዘመን፦ 1951

  • የትውልድ አገር፦ ጀርመን

  • የኋላ ታሪክ፦ ኩሩና በራስ የመመራት ዝንባሌ የተጠናወተው

የቀድሞ ሕይወቴ፦

የልጅነቴን የተወሰኑ ዓመታት ያሳለፍኩት ምሥራቅ ጀርመን ውስጥ በቼኮስሎቫኪያና በፖላንድ ድንበሮች አቅራቢያ በምትገኘው በላይፕሲግ አካባቢ ነበር። ስድስት ዓመት ሲሆነኝ በአባቴ ሥራ ምክንያት በመጀመሪያ ወደ ብራዚል ከዚያም ወደ ኢኳዶር ሄድን።

አሥራ አራት ዓመት ሲሆነኝ ወላጆቼ ጀርመን ወደሚገኝ አዳሪ ትምህርት ቤት ላኩኝ። ወላጆቼ የሚኖሩት በደቡብ አሜሪካ ስለነበር ያለእነሱ እርዳታ ራሴን መምራት ነበረብኝ። ይህም በራሴ የምመራ ሰው እንድሆን አደረገኝ። የማደርጋቸው ነገሮች በሌሎች ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ አያሳስበኝም ነበር።

አሥራ ሰባት ዓመት ሲሆነኝ ወላጆቼ ወደ ጀርመን ተመለሱ። መጀመሪያ ላይ ከእነሱ ጋር አብሬ መኖር ጀምሬ ነበር። ይሁን እንጂ በራሴ የምመራ ሰው ስለነበርኩ ከእነሱ ጋር ተስማምቶ መኖር ከባድ ሆነብኝ። በመሆኑም በ18 ዓመቴ ቤት ለቅቄ ወጣሁ።

የሕይወትን ዓላማ ለማወቅ ያልሞከርኩት ነገር አልነበረም። የተለያዩ የአኗኗር ዘይቤዎችን እንዲሁም ቡድኖችን ከተመለከትኩ በኋላ በሕይወቴ ላደርግ የምችለው ከሁሉ የተሻለው ነገር ሰዎች ይህችን ውብ ፕላኔት ሳያጠፏት በፊት እየተዘዋወርኩ ማየት እንደሆነ ተሰማኝ።

አንድ ሞተር ብስክሌት ገዛሁና ጀርመንን ለቅቄ ወደ አፍሪካ አመራሁ። ብዙም ሳይቆይ ግን ሞተር ብስክሌቴን ለማስጠገን ወደ አውሮፓ መመለስ አስፈለገኝ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ፖርቱጋል ውስጥ ወደሚገኝ አንድ የባሕር ዳርቻ ሄድኩ። ሞተር ብስክሌቴን ትቼ በውኃ ላይ ለመጓዝ የሚያስችለኝ ጀልባ ማግኘት እንዳለብኝ የተሰማኝ በዚህ ቦታ እያለሁ ነበር።

በዚህ ጊዜ አትላንቲክ ውቅያኖስን በጀልባ ለማቋረጥ እየተዘጋጀ ከነበረ አንድ የወጣቶች ቡድን ጋር ተገናኘሁ። ከጊዜ በኋላ ባለቤቴ የሆነችው ሎሪም ከእነሱ መካከል ነበረች። መጀመሪያ ወደ ካሪቢያን ደሴቶች ተጓዝን። ከዚያም በፖርቶ ሪኮ ትንሽ ቆይታ ካደረግን በኋላ ወደ አውሮፓ ተመለስን። ለመኖሪያም የሚሆን በሞተር የሚንቀሳቀስ ጀልባ ለማግኘት ተስፋ አድርገን ነበር። ይሁን እንጂ ለሦስት ወር ያህል ስናፈላልግ ከቆየን በኋላ እቅዳችን በድንገት ተቋረጠ። ምክንያቱም በጀርመን የጦር ኃይል ውስጥ እንዳገለግል ተመለመልኩ።

በጀርመን የባሕር ኃይል ውስጥ ለ15 ወር አገለገልኩ። በዚህ ጊዜ ውስጥ እኔና ሎሪ ተጋባን፤ ከዚያም ዓለምን የማሰስ እቅዳችንን ለመቀጠል ዝግጅት  ማድረግ ጀመርን። ወታደራዊ አገልግሎት ከመጀመሬ ጥቂት ቀደም ብሎ የአንድ ጀልባ ቀፎ ገዝተን ነበር። በጦር ኃይል ውስጥ እያገለገልኩ ሳለሁ የገዛነውን የጀልባ ቀፎ በሸራ የሚነዳ አነስተኛ ጀልባ አድርገን ሠራነው። ኑሯችንን ጀልባው ውስጥ አድርገን ውቧን ፕላኔታችንን እየተዘዋወርን ለማየት አቅደን ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝተን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመርነው በዚህ ወቅት ነው፤ በወቅቱ ወታደራዊ አገልግሎቴን ጨርሼ ጀልባውን ሠርተን እያጠናቀቅን ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

መጀመሪያ ላይ በሕይወቴ ውስጥ ያን ያህል ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልገኝ አልተሰማኝም ነበር። ምክንያቱም የምኖረው በሕጋዊ መንገድ ካገባኋት ሴት ጋር ነው፤ በዚያ ላይ ደግሞ ማጨስ አቁሜያለሁ። (ኤፌሶን 5:5) ዓለምን ለማሰስ የነበረን እቅድም የአምላክን ድንቅ የፍጥረት ሥራዎች እንድንቃኝ ስለሚያስችለን ጥሩ የሕይወት አቅጣጫ እንደሆነ አስብ ነበር።

እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ለውጥ ማድረግ ያስፈልገኝ ነበር፤ በተለይ ደግሞ በባሕሪዬ ረገድ። ኩሩና ከልክ በላይ በራሴ የምመራ ሰው ስለነበርኩ ትኩረቴ ሁሉ ያረፈው በችሎታዎቼና ባከናወንኳቸው ነገሮች ላይ ነበር። ሕይወቴ በራሴ ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር።

አንድ ቀን ኢየሱስ በተራራ ላይ የሰጠውን ዝነኛ ስብከት አነበብኩ። (ማቴዎስ ምዕራፍ 5-7) መጀመሪያ ላይ ኢየሱስ ደስተኛ መሆን ስለሚቻልባቸው መንገዶች የተናገረው ሐሳብ ግራ አጋብቶኝ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የሚራቡና የሚጠሙ ደስተኛ እንደሆኑ ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:6) ችግረኛ መሆን አንድን ሰው እንዴት ደስተኛ ሊያደርገው እንደሚችል አልገባኝም። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴን ስቀጥል ግን ሁላችንም መንፈሳዊ ፍላጎት እንዳለን ተገነዘብኩ፤ እንዲሁም እንዲህ ያለ ፍላጎት እንዳለን በትሕትና መቀበልና እሱን ለማርካት ጥረት ማድረግ እንዳለብን ተረዳሁ። ነገሩ ኢየሱስ እንዳለው ነው፦ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው።”—ማቴዎስ 5:3

እኔና ሎሪ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመርነው በጀርመን እያለን ሲሆን ከዚያ በኋላ ወደ ፈረንሳይ ከዚያም ወደ ጣሊያን ሄደናል። በሄድንበት ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችን እናገኝ ነበር። በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለው እውነተኛ ፍቅርና አንድነት በእጅጉ ያስደንቀኝ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ አንድነት ያላቸው ሕዝቦች እንደሆኑ ተገነዘብኩ። (ዮሐንስ 13:34, 35) ከጊዜ በኋላ እኔና ሎሪ ተጠምቀን የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን።

ከተጠመቅሁ በኋላም በባሕሪዬ ላይ ለውጥ ማድረግ ነበረብኝ። እኔና ሎሪ በአፍሪካ የጠረፍ አካባቢዎች አድርገን አትላንቲክ ውቅያኖስን በማቋረጥ በጀልባችን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመሄድ ወሰንን። ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች በሚሸፍነው የተንጣለለ ውቅያኖስ ላይ እኔና ሎሪ ብቻችንን በትንሿ ጀልባችን ላይ በምንጓዝበት ወቅት ዕፁብ ድንቅ ከሆነው ፈጣሪያችን ጋር ስንወዳደር ምን ያህል ኢምንት እንደሆንን ተገነዘብኩ። ውቅያኖስ ላይ ሆኖ ብዙ የሚሠራ ሥራ ስለሌለ ጊዜያችንን የሚሻማ ነገር አልነበረም፤ በመሆኑም አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፈው መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ነበር። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይበልጥ የነካኝ ኢየሱስ በምድር ላይ ስላሳለፈው ሕይወት የሚገልጸው ታሪክ ናቸው። እኔ ልገምት ከምችለው በላይ ከፍተኛ ችሎታዎች ያሉት ፍጹም ሰው የነበረ ቢሆንም ወደ ራሱ ትኩረት ለመሳብ ሞክሮ አያውቅም። ሕይወቱ ያተኮረው በራሱ ላይ ሳይሆን በሰማይ ባለው አባቱ ላይ ነው።

የአምላክን መንግሥት ማስቀደም እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ

በኢየሱስ ታሪክ ላይ ሳሰላስል ትኩረቴን በምፈልጋቸው ነገሮች ላይ ብቻ ከማድረግ ይልቅ የአምላክን መንግሥት ማስቀደም እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ። (ማቴዎስ 6:33) እኔና ሎሪ ዩናይትድ ስቴትስ ስንደርስ እዚያው ለመኖርና ትኩረታችንን በአምልኳችን ላይ ለማድረግ ወሰንን።

ያገኘሁት ጥቅም፦

ሕይወቴ በራሴ ላይ ብቻ ያተኮረ በነበረበት ወቅት አብዛኛውን ጊዜ ስለማደርጋቸው ውሳኔዎች እርግጠኛ አልነበርኩም። አሁን ግን ልመራበት የምችል ምንጊዜም ትክክለኛ የሆነ ጥበብ የሚገኘው የት እንደሆነ አውቄያለሁ። (ኢሳይያስ 48:17, 18) በተጨማሪም ከዚህ በፊት እፈልግ የነበረውን የሕይወት ዓላማ አግኝቻለሁ፤ ይኸውም አምላክን ማምለክና ስለ እሱ እንዲማሩ ሰዎችን መርዳት ነው።

እኔና ሎሪ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረጋችን ትዳራችንን በእጅጉ አጠናክሮልናል። በተጨማሪም ይሖዋን የምታውቅና የምትወድ አንዲት ልጅ ስላለችን ተባርከናል።

ሕይወታችን ሁልጊዜ አልጋ በአልጋ አልነበረም ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ ስለሚረዳን እሱን ማገልገላችንና በእሱ መታመናችንን ፈጽሞ አናቆምም።—ምሳሌ 3:5, 6