በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 የሕይወት ታሪክ

አምላክን በማገልገል ያሳለፍኩት አስደሳች ሕይወት

አምላክን በማገልገል ያሳለፍኩት አስደሳች ሕይወት

ከልጅነቴ ጀምሮ ይደርስብኝ የነበረው የዘር መድልዎ እንዲሁም ባይሳካልኝስ የሚለው ፍርሃት በጣም ያስጨንቀኝ ነበር፤ ከዚህም ሌላ በተፈጥሮዬ በጣም ዓይናፋር ነበርኩ። ከመጽሐፍ ቅዱስ መጽናኛ ማግኘት እንደምችል ተስፋ በማድረግ በአካባቢያችን ወዳለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሄጄ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስተምሩኝ ጠየቅኩ። እዚያም የፈለግኩትን ማግኘት ባለመቻሌ ትኩረቴን ወደ ስፖርቱ ዓለም አዞርኩ።

ብዙም ሳይቆይ ጂምናስቲክና የጡንቻ ስፖርቶች መሥራት ጀመርኩ። ውሎ አድሮም በሳን ሊያንድሮ፣ ካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዕከል ከፈትኩ፤ በዚያም የአሜሪካ የሰውነት ቅርጽ ውድድር አሸናፊ የነበረን አንድ ሰው ጨምሮ በዚህ ስፖርት ላይ ከተሰማሩ ሌሎች ሰዎች ጋር እሠራ ነበር። የተስተካከለና ፈርጣማ ሰውነት እንዲኖረኝ ማድረግ ብችልም በውስጤ የሚሰማኝን ባዶነት ማስወገድ አልቻልኩም።

ያደረግኩት ፍለጋ ተሳካ

በከፈትኩት የስፖርት ማዕከል ውስጥ የሚሠራ አንድ ጓደኛዬ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ያለኝን ፍላጎት ስለተረዳ እሱ ከሚያውቀው አንድ ሰው ጋር ሊያስተዋውቀኝ እንደሚፈልግ ነገረኝ። በማግስቱ ጠዋት አንድ የይሖዋ ምሥክር ወደ ቤቴ መጣ። ለአራት ሰዓት ያህል፣ ላቀረብኩለት ጥያቄዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መልስ ሰጠኝ። ከዚያም፣ በዚያኑ ዕለት ምሽት ተመልሶ እንዲመጣ ጠየቅሁት፤ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ተወያየን። በተማርኩት ነገር በጣም ስለተደሰትኩ በቀጣዩ ቀን አብሬው በመሄድ የሚሰብክበትን መንገድ ማየት እችል እንደሆነ ጠየቅሁት። ሰዎች ለሚያቀርቡለት ጥያቄ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መልስ የሚሰጥበት መንገድ አስደነቀኝ። ‘እኔም ማድረግ የምፈልገው ይህንን ነው’ ብዬ አሰብኩ!

በመሆኑም ሥራዬን በመተው ከዚህ አቅኚ ጋር (የይሖዋ ምሥክር የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሚጠራበት ስያሜ ነው) በአገልግሎት ማሳለፍ ጀመርኩ። ግንቦት 1948 ሳን ፍራንሲስኮ፣ ካሊፎርኒያ ውስጥ ካው ፓላስ በሚባል የስፖርት ማዕከል በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተጠመቅሁ። በዚያው ዓመት አቅኚ ሆንኩ።

የይሖዋ ምሥክሮች እናቴን ሄደው እንዲያነጋግሩልኝ ጠየቅኋቸው። እናቴም ጥሩ ምላሽ የሰጠች ሲሆን ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። የቤተሰብ ተቃውሞ ቢያጋጥማትም ሕይወቷ እስኪያልፍ ድረስ ለበርካታ ዓመታት አምላክን በታማኝነት አገልግላለች። ከእሷ በቀር ከቤተሰባችን የይሖዋ ምሥክር የሆነ ሌላ ሰው የለም።

ከባለቤቴ ጋር ተዋወቅን

በ1950 ወደ ግራንድ ጃንክሽን፣ ኮሎራዶ ተዛወርኩ፤ በዚያም ከቢሊ ጋር ተዋወቅሁ። ቢሊ የተወለደችው በ1928 ሲሆን በወቅቱ ታላቅ የኢኮኖሚ ድቀት ተከስቶ ነበር። እናቷ ሚኒ በየቀኑ ምሽት ላይ ጭል ጭል በሚል የኩራዝ ብርሃን መጽሐፍ ቅዱስን ታነብላት ነበር። ቢሊ በአራት ዓመቷ ማንበብ የቻለች ሲሆን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችንም ታውቅ ነበር። በ1940ዎቹ መገባደጃ ላይ እናቷ መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስታጠና ሲኦል የመሠቃያ ቦታ ሳይሆን የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር የሚያመለክት ነገር እንደሆነ አወቀች። (መክብብ 9:5, 10) ከዚያም ሚኒና ባሏ የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ።

ቢሊ በ1949 በቦስተን ከሚገኝ አንድ ኮሌጅ ተመርቃ ስትመለስ መጽሐፍ ቅዱስን በቁም ነገር ማጥናት ጀመረች። ከዚያም መምህር ከመሆን ይልቅ ሕይወቷን ለአምላክ ለመወሰን ቁርጥ ውሳኔ አደረገች። የይሖዋ ምሥክሮች በ1950 በኒው ዮርክ፣ ያንኪ ስታዲየም ባደረጉት ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ተጠመቀች። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ከቢሊ ጋር ተዋወቅን፤ በኋላም ተጋብተን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አብረን መሥራት ጀመርን።

 አገልግሎታችንን የጀመርነው በዩጂን፣ ኦሪገን ሲሆን ብዙ የዕድሜ ልክ ወዳጆችን አፍርተናል። በ1953 በግራንትስ ፓስ፣ ኦሪገን የሚገኝ አንድ አነስተኛ ጉባኤ ለመርዳት ወደዚያ ተዛወርን። በዚያው ዓመት ትንሽ ቆይቶ በጊልያድ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የሚስዮናውያን ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት በ23ኛው ክፍል ላይ እንድንካፈል ተጋበዝን፤ ትምህርት ቤቱ የሚገኘው ከኒው ዮርክ ሲቲ በስተ ሰሜን ምዕራብ 400 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ባለው በሳውዝ ላንሲንግ አቅራቢያ ነው።

በብራዚል በሚስዮናዊነት ማገልገል

እኔና ቢሊ ታኅሣሥ 1954 ማለትም ከጊልያድ ትምህርት ቤት ከተመረቅን ከአምስት ወራት በኋላ በአውሮፕላን ተሳፍረን ወደ ብራዚል ለመሄድ ተነሳን። ለአንድ ሰዓት ያህል ከበረርን በኋላ ሞተሩ ተበላሸብን፤ ያም ቢሆን በሰላም ቤርሙዳ ላይ አረፍን። አውሮፕላኑ በደረሰበት እክል የተነሳ በድጋሚ ኩባ ላይ ለማረፍ ተገደድን፤ በሪዮ ዴ ጄኔሮ፣ ብራዚል ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ለመድረስ በአጠቃላይ 36 ሰዓታት ፈጅቶብናል።

በባውሩ የመጀመሪያው የመንግሥት አዳራሽ፣ የጻፍኩት ምልክት በተከራየነው በዚህ አዳራሽ ላይ ተሰቅሎ፣ 1955

እኔና ቢሊ በቅርንጫፍ ቢሮው አጭር ቆይታ ካደረግን በኋላ ከሌሎች ሁለት ሚስዮናውያን ጋር ወደ ባውሩ፣ ሳኦ ፓውሎ ሄደን የሚስዮናዊነት አገልግሎት ጀመርን። የከተማዋ የሕዝብ ብዛት ከ50,000 በላይ ሲሆን በዚያ የመጀመሪያዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች እኛ ነበርን።

ከቤት ወደ ቤት እየሄድን ሰዎችን ማነጋገር ጀመርን፤ ይሁን እንጂ የአካባቢው የካቶሊክ ቄስ ወዲያውኑ ሥራችንን መቃወም ጀመረ። በሄድንበት እየተከተለን የቤቱ ባለቤቶች እንዳይሰሙን ያስጠነቅቅ ነበር። ይሁንና በጥቂት ሳምንታት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ የሆነ አንድ ትልቅ ቤተሰብ አገኘን፤ የዚህ ቤተሰብ አባላት ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ተጠመቁ። ብዙም ሳይቆይ ሌሎች ሰዎችም ማጥናት ጀመሩ።

የተጠመቁት ቤተሰብ፣ የአንድ ታዋቂ ክበብ ፕሬዚዳንት የሆነ ዘመድ ነበራቸው። እኔም ይህ ክበብ በሚጠቀምበት አዳራሽ ውስጥ ትልቅ ስብሰባ ለማድረግ አሰብኩ። የአካባቢው ቄስ ኮንትራቱ እንዲሰረዝ ጥረት ሲያደርግ ፕሬዚዳንቱ የክበቡን አባላት “ውሉን የምትሰርዙት ከሆነ እኔ ሥራ እለቃለሁ!” አላቸው። በመሆኑም በዚያ ቦታ ስብሰባውን ማካሄድ ቻልን።

በቀጣዩ ዓመት ማለትም በ1956 በሳንቶስ፣ ሳኦ ፓውሎ በተደረገው አውራጃ ስብሰባ ላይ እንድንገኝ ተጋበዝን። ከጉባኤያችን 40 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች በባቡር ወደዚያ ሄደው ነበር። ወደ ባውሩ ስንመለስ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎችን እንድጎበኝ መመደቤን የሚገልጽ ደብዳቤ አገኘሁ። በዚህ የሥራ ምድብ ወደ 25 ለሚጠጉ ዓመታት ያገለገልኩ ሲሆን በዚያ ሰፊ አገር በሚገኙ አብዛኞቹ አካባቢዎች እየተዘዋወርን አገልግለናል።

በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ በባውሩ ያፈራናቸው በርካታ ቀናተኛ የመንግሥቱ ሰባኪዎች

አገልግሎቱ ምን ይመስል ነበር?

በዚያ ወቅት ጉዞ ማድረግ አስቸጋሪ ነበር። በአውቶብስ፣ በባቡር፣ በጋሪ፣ በብስክሌት እንዲሁም በእግራችን በመጓዝ አገሩን በሙሉ አካልለናል ማለት ይቻላል። መጀመሪያ ከሄድንባቸው ከተሞች አንዷ በሳኦ ፓውሎ የምትገኘው ጃው ነበረች። እዚያም አንድ ቄስ ተቃወመን።

ቄሱ “‘ለበጎቼ’ መስበክ አትችሉም” በማለት ተናገረ።

እኛም “ያንተ በጎች አይደሉም። የአምላክ ናቸው” በማለት መልስ ሰጠነው።

ዘ ኒው ዎርልድ ሶሳይቲ ኢን አክሽን በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን ስለ ዓለም አቀፉ የስብከት ሥራችን የሚገልጽ ፊልም ለማሳየት ዝግጅት አደረግን፤ በዚህ ጊዜ ቄሱ በእኛ ላይ ረብሻ ለማስነሳት ሰዎችን ሰበሰበ። እኛም ወዲያውኑ ሁኔታውን ለፖሊስ አሳወቅን። ቄሱና ረብሻ ለመፍጠር የተባበሩት የቤተ ክርስቲያኑ አባላት ፊልም ወደምናሳይበት ቦታ ሲደርሱ ፖሊሶች ጠመንጃቸውን ደግነው ስለጠበቋቸው ምንም ማድረግ አልቻሉም። ፊልሙን ለማየት የተሰበሰበው ብዙ ሕዝብ በፊልሙ በጣም ተደስቷል።

በዚያ ጊዜ፣ ልናገለግል በምንሄድባቸው በአብዛኞቹ አካባቢዎች ከሃይማኖት ሰዎች ጥላቻና ተቃውሞ ያጋጥመን ነበር። ለምሳሌ ያህል በብሉሜናው፣ ሳንታ ካታሪና አቅራቢያ በምትገኘው  በብሩስኪ ከሁለት አቅኚዎች ጋር ተገናኝተን ነበር፤ እነዚህ አቅኚዎች የሚደርስባቸውን ኃይለኛ ተቃውሞ ተቋቁመው ያገለግሉ ነበር። ይሁን እንጂ ጽናታቸው በእጅጉ ክሷቸዋል። ይህ ከሆነ 50 ዓመታት ያለፈ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በዚህ ክልል ከ60 በላይ ጉባኤዎች ይገኛሉ፤ በተጨማሪም በዚህች ከተማ አቅራቢያ በምትገኝ ኢታዣዪ በተባለች ከተማ አንድ የሚያምር የትላልቅ ስብሰባ አዳራሽ ተገንብቷል!

ከተጓዥነት ሥራችን ውስጥ የማንረሳው አንዱ ገጽታ ትላልቅ ስብሰባዎችን ለማደራጀት ከእምነት አጋሮቻችን ጋር በመሥራት የምናሳልፈው አስደሳች ጊዜ ነው። በ1970ዎቹ ዓመታት ሰፊ በሆነው በሞሩምቢ ስታዲየም በተካሄዱ ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የስብሰባ የበላይ ተመልካች ሆኜ የማገልገል መብት አግኝቼ ነበር። ስብሰባው ከመካሄዱ በፊት በነበረው ምሽት ስታዲየሙን የሚያጸዱ አሥር አሥር ሰዎችን እንዲልኩ በአቅራቢያው ላሉት አንድ መቶ ገደማ ለሚሆኑ ጉባኤዎች ጥሪ ቀርቦላቸው ነበር።

በዚያ ምሽት የእግር ኳስ ተጫዋቾቹ ስታዲየሙን ለቅቀው ሲወጡ ለጽዳት የሚገቡትን የይሖዋ ምሥክሮች ተመልክተው “መጥረጊያና መወልወያ ይዘው የሚገቡትን ሴቶች እዩአቸው፤ አሁን ይህን ስታዲየም ሊያጸዱ ነው?” በማለት አሹፈው ነበር። ሆኖም እኩለ ሌሊት ላይ መላው ስታዲየም ተጸድቶ አለቀ! የስታዲየሙ ኃላፊ “እናንተ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የሠራችሁትን ለማከናወን የእኔ ሠራተኞች አንድ ሳምንት ሙሉ ይፈጅባቸው ነበር!” በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለስን

በ1980 አባቴ የሞተ ሲሆን ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በፍሪሞንት፣ ካሊፎርኒያ የምትኖረውን እናቴን ለመንከባከብ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለስን። እዚህም አቅኚ ሆነን ማገልገላችንን የቀጠልን ሲሆን በአካባቢው ያሉትን የፖርቱጋል ሕዝቦች መርዳት ጀመርን፤ ራሳችንን ለማስተዳደር ደግሞ ማታ ላይ ሕንፃዎችን እናጸዳ ነበር። ቆየት ብሎ በአቅራቢያ ወዳለው ሳን ዎኪን ቫሊ የሚባል አካባቢ ተዛወርን፤ በዚህ አካባቢ ሆነን ከሳክራሜንቶ እስከ ቤከርስፊልድ ባለው ሰፊ ክልል ውስጥ ፖርቱጋልኛ ለሚናገሩ ሕዝቦች ለመስበክ ጥረት አድርገናል። በአሁኑ ጊዜ በካሊፎርኒያ ውስጥ በፖርቱጋልኛ ቋንቋ የሚካሄዱ አሥር የሚያህሉ ጉባኤዎች አሉ።

በ1995 እናቴ ስትሞት የቢሊን አባት ለመንከባከብ ወደ ፍሎሪዳ ሄድን፤ የቢሊ አባት እስከሞተበት ዕለት ድረስ አብረነው ቆይተናል። የቢሊ እናት የሞተችው ቀደም ብሎ ማለትም በ1975 ነበር። በ2000 ደግሞ በደቡብ ምዕራብ ኮሎራዶ ወዳለ ከፍታ ቦታ ላይ ወደሚገኝ በረሃማ አካባቢ ተዛወርን። በዚህ አካባቢ የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች ሆነን ስናገለግል ናቫሆ እና ዩት የተባሉት የአሜሪካ ሕንዶች በሚኖሩበት አካባቢ ሰብከናል። የሚያሳዝነው፣ ቢሊ የካቲት 2014 አረፈች።

ከ65 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት የነበሩኝን ብዙ ጥያቄዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ እያወጣ ከመለሰልኝ አንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር በመገናኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ! በተለይ እሱ ያስተማረኝ ነገር በእርግጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኝ እንደሆነ ለማረጋገጥ ምርምር ማድረጌ በጣም ጠቅሞኛል። ምክንያቱም አምላክን በማገልገል አስደሳች ሕይወት እንዳሳልፍ አስችሎኛል።