በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው

መላእክት ሊረዱን ይችላሉ?

መላእክት በጥንት ጊዜ የአምላክ ታማኝ አገልጋይ የነበረውን ዳንኤልን እንደረዱት ሁሉ በዛሬው ጊዜም ሰዎች ምሥራቹ እንዲደርሳቸው ይረዳሉ

ይሖዋ አምላክ ሰዎችን ከመፍጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት በሚሊዮን የሚቆጠሩ መላእክትን ፈጥሯል። (ኢዮብ 38:4, 7) እነዚህ መላእክት አምላክን የሚያገለግሉ ኃያል መንፈሳዊ ፍጥረታት ናቸው፤ አንዳንድ ጊዜ አምላክ በምድር ላይ ላሉ አገልጋዮቹ መመሪያ ለመስጠትና ጥበቃ ለማድረግ መላእክትን ይልካል። (መዝሙር 91:10, 11) በዛሬው ጊዜ መላእክት፣ የኢየሱስ ተከታዮች የሚሰብኩት ምሥራች ለሰዎች እንዲደርስ እርዳታ ያደርጋሉ።—ራእይ 14:6, 7ን አንብብ።

መላእክት እንዲረዱን ወደ እነሱ መጸለይ ይኖርብናል? አይኖርብንም። ጸሎት አምልኮ ስለሆነ ሊቀርብ የሚገባው ለአምላክ ብቻ ነው። (ራእይ 19:10) ደግሞም መላእክት የአምላክ አገልጋዮች ስለሆኑ የሚሰሙት አምላክን እንጂ ሰዎችን አይደለም። በመሆኑም ምንጊዜም ጸሎታችንን በኢየሱስ በኩል ወደ አምላክ ብቻ ማቅረብ ይኖርብናል።—መዝሙር 103:20, 21፤ ማቴዎስ 26:53ን አንብብ።

መጥፎ መላእክት አሉ?

እንደ ሰዎች ሁሉ መላእክትም የተፈጠሩት የመምረጥ ነፃነት እንዲኖራቸው ተደርገው ነው፤ በመሆኑም ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር ለማድረግ መምረጥ ይችላሉ። የሚያሳዝነው ነገር፣ ብዙ መላእክት በአምላክ ላይ ዓመፁ። (2 ጴጥሮስ 2:4) መጀመሪያ ያመፀው ሰይጣን ነው፤ ከዚያም ሌሎች መላእክት እንደ እሱ በማመፅ አጋንንት ሆነዋል። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ ተባርረው ወደ ምድር ተጥለዋል።—ራእይ 12:7-9ን አንብብ።

ከ1914 ወዲህ ክፋትና ዓመፅ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ አምላክ በቅርቡ የሰይጣንንና የአጋንንቱን እንቅስቃሴ እንደሚያስቆም ያመለክታል። ከዚያም አምላክ መጀመሪያ ለምድር ያወጣው ዓላማ ይፈጸማል።ራእይ 12:12፤ 21:3, 4ን አንብብ።