በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

በ16ኛው መቶ ዘመን የነበሩ ሦስት እውነት ፈላጊዎች—ምን አገኙ?

በ16ኛው መቶ ዘመን የነበሩ ሦስት እውነት ፈላጊዎች—ምን አገኙ?

“እውነት ምንድን ነው?” በመጀመሪያው መቶ ዘመን የይሁዳ አገረ ገዢ የነበረው ሮማዊው ጳንጥዮስ ጲላጦስ በፊቱ ለፍርድ ቀርቦ ለነበረው ለኢየሱስ ይህን ጥያቄ አቅርቦ ነበር። (ዮሐንስ 18:38) እርግጥ ነው፣ ጲላጦስ ይህን ጥያቄ ያቀረበው እውነትን ለማወቅ ፈልጎ አልነበረም። እንዲህ ያለ የምጸት ጥያቄ ማንሳቱ ተጠራጣሪነቱን የሚጠቁም ነው። ጲላጦስ፣ እውነት ሲባል አንድ ሰው ለማመን የመረጠውን ወይም የተማረውን ማንኛውንም ነገር እንደሚያመለክትና እውነትን ማወቅ የሚቻልበት መንገድ እንደሌለ ያስብ የነበረ ይመስላል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎችም እንዲህ ይሰማቸዋል።

በ16ኛው መቶ ዘመን በአውሮፓ የነበሩ ምእመናን እውነተኛው ነገር የቱ እንደሆነ ግራ ተጋብተው ነበር። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሁሉም የበላይ እንደሆኑ የሚገልጸውንና ሌሎቹን የቤተ ክርስቲያኗን ትምህርቶች ከልጅነታቸው ጀምሮ የተማሩ ሰዎች፣ በወቅቱ አውሮፓን ያጥለቀለቃት የተሐድሶ ንቅናቄ ያመጣቸው አዳዲስ ሐሳቦች ተጋረጡባቸው። ታዲያ ማመን ያለባቸው የትኛውን ነው? እውነት የሆነውን መለየት የሚችሉትስ እንዴት ነው?

በዚያን ጊዜ፣ እውነቱን ፈልገው ለማግኘት ቆርጠው የተነሱ በርካታ ሰዎች ነበሩ፤ ከእነዚህ መካከል ሦስቱን እንመለከታለን። * እነዚህ ሰዎች እውነት የሆነውን ከሐሰቱ መለየት የቻሉት እንዴት ነበር? ደግሞስ ምን አገኙ? መልሱን እያየን እንሄዳለን።

“መጽሐፍ ቅዱስ . . . ምንጊዜም የበላይነት ይኑረው”

ቮልፍጋንግ ካፒቶ አጥባቂ ሃይማኖተኛ የሆነ ወጣት ነበር። ሕክምና፣ ሕግ እና መንፈሳዊ ትምህርት ያጠናው ካፒቶ በ1512 የደብር ቄስ ሆነ፤ ከዚያም የማይንዝ ሊቀ ጳጳሳት ረዳት ሆነ።

መጀመሪያ ላይ ካፒቶ፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርቶች የሚቃወም መልእክት ይሰብኩ የነበሩትን የተሐድሶ አራማጆች ቅንዓት ለማለዘብ ይሞክር ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ካፒቶ ራሱ የተሐድሶውን እንቅስቃሴ መደገፍ ጀመረ። ታዲያ ምን አድርጎ ይሆን? የታሪክ ምሁር የሆኑት ጄምስ ማቲው ኪተልሰን እንደጻፉት ካፒቶ ከተለያዩ ትምህርቶች ጋር በተያያዘ ጥያቄ ሲሰነዘርበት “[ስብከቱ] ትክክል መሆኑ የሚመዘንበት ከሁሉ የተሻለው መለኪያ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ” ገልጿል፤ ይህን ያለው “ትክክል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው” የሚል እምነት ስለነበረው እንደሆነ ኪተልሰን ተናግረዋል። በመሆኑም ካፒቶ ስለ ምስጢረ ቁርባንና ለቅዱሳን አምልኮ አከል ክብር ስለመስጠት የሚገልጹት የቤተ ክርስቲያኗ ትምህርቶች ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የላቸውም የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሰ። (“ ነገሩ ትክክል መሆኑን ማረጋገጥ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በ1523 ካፒቶ በሊቀ ጳጳሳቱ ዘንድ የነበረውን ትልቅ ቦታ ትቶ በወቅቱ የሃይማኖታዊ ተሐድሶ ማዕከል በነበረችው በስትራዝቡርግ ከተማ መኖር ጀመረ።

በስትራዝቡርግ ባለው የካፒቶ ቤት፣ በሃይማኖት ረገድ የተለየ  አመለካከት ያላቸው ሰዎች ይገናኙ እንዲሁም በብዙ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች ላይ ይወያዩ ነበር። አንዳንድ የተሐድሶ አራማጆች የሥላሴን መሠረተ ትምህርት ይቀበሉ የነበረ ቢሆንም ዘ ራዲካል ሪፎርሜሽን የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚገልጸው ከሆነ ካፒቶ “በሥላሴ መሠረተ ትምህርት ረገድ ዝምታን” እንደመረጠ ከጽሑፎቹ ማየት ይቻላል። ለምን? ካፒቶ፣ የስፔን ሃይማኖታዊ ምሁር የነበረው ማይክል ሰርቪተስ የሥላሴ ትምህርት ሐሰት መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ተጠቅሞ ያስረዳበት መንገድ ትኩረቱን ስቦት ነበር። *

ሥላሴን መካድ፣ ሞት ሊያስከትል የሚችል ነገር በመሆኑ ካፒቶ አመለካከቱን በግልጽ አውጥቶ ለመናገር አልደፈረም። ይሁን እንጂ ከማይክል ሰርቪተስ ጋር ከመገናኘቱ በፊትም የሥላሴ መሠረት ትምህርት ትክክል መሆኑን ይጠራጠር እንደነበር ከጽሑፎቹ መመልከት ይቻላል። ካፒቶና ተባባሪዎቹ “በግላቸው በሃይማኖት ጥልቅ ሚስጥሮች ላይ መወያየት የጀመሩ ሲሆን የቤተ ክርስቲያኗን ባለሥልጣናት በይፋ ባይቃወሙም እጅግ ቅዱስ የሆነውን ሥላሴን እንደካዱ” ከጊዜ በኋላ አንድ የካቶሊክ ቄስ ጽፏል። ካፒቶ ከኖረበት ዘመን ከአንድ መቶ ዓመት በኋላ፣ ሥላሴን በመቃወም ከጻፉ ታዋቂ ጸሐፊዎች ስም ዝርዝር ውስጥ የካፒቶ ስም በአንደኛ ደረጃ ሰፍሯል።

ቮልፍጋንግ ካፒቶ የቤተ ክርስቲያን ዋና ድክመት ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን ችላ ማለቷ’ እንደሆነ ያምን ነበር

ካፒቶ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የእውነት ምንጭ እንደሆነ ያምን ነበር። “በመንፈሳዊ ትምህርት ረገድ መጽሐፍ ቅዱስና የክርስቶስ ሕግ ምንጊዜም የበላይነት ይኑራቸው” በማለት ተናግሯል። ዶክተር ኪተልሰን እንደተናገሩት ካፒቶ “የመንፈሳዊ ትምህርት ምሁራን፣ ዋና ድክመት ቅዱሳን መጻሕፍትን ችላ ማለታቸው እንደሆነ አበክሮ ገልጿል።”

በ1526 በካፒቶ ቤት አርፎ የነበረው ማርቲን ሴላሪዎስ (ማርቲን ቦርሃዎስ ተብሎም ይጠራል) የሚባል አንድ ወጣትም ልክ እንደ ካፒቶ እውነትን ከአምላክ ቃል የመማር ልባዊ ፍላጎት ነበረው።

‘ስለ እውነተኛው አምላክ የሚገልጽ እውቀት’

ማርቲን ሴላሪዎስ የቤተ ክርስቲያኗን ትምህርቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያነጻጸረበት ኦን ዘ ዎርክስ ኦቭ ጎድ የተባለው መጽሐፍ የመጀመሪያ ገጽ

በ1499 የተወለደው ሴላሪዎስ የመንፈሳዊ ትምህርትና የፍልስፍና ትጉ ተማሪ ነበር። ሴላሪዎስ በዊተንበርግ፣ ጀርመን በመምህርነት ሥራ ላይ ተሰማርቶ ነበር። ዊተንበርግ የተሐድሶው እንቅስቃሴ ዋና ማዕከል ስለነበረች ሴላሪዎስ፣ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ማሻሻል ከሚፈልጉት እንደ ማርቲን ሉተር ያሉ ሰዎች ጋር ብዙም ሳይቆይ ተዋወቀ። ታዲያ ሴላሪዎስ ከሰብዓዊ አስተሳሰብ የመነጩትን ትምህርቶች በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኘው እውነት መለየት የቻለው እንዴት ነበር?

ቲቺንግ ዘ ሪፎርሜሽን የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚገልጸው ሴላሪዎስ እውነተኛ እውቀት የሚገኘው “መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማንበብ፣ ቅዱስ ጽሑፉን ሁልጊዜ እርስ በርሱ በማነጻጸርና ንስሐ በገባ ልብ በሚቀርብ ጸሎት” እንደሆነ ያምን ነበር። ታዲያ ሴላሪዎስ መጽሐፍ ቅዱስን ሲመረምር ምን አገኘ?

ሐምሌ 1527 ሴላሪዎስ የምርምሩን ውጤት ኦን ዘ ዎርክስ ኦቭ ጎድ የሚል ርዕስ ባለው መጽሐፍ ላይ አሳተመ። እንደ ምስጢረ ቁርባን ያሉት የቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት ሥርዓቶች፣ ሙሉ በሙሉ ምሳሌያዊ እንጂ ቃል በቃል የሚወሰዱ ነገሮች እንዳልሆኑ ጽፏል። ከዚህም በተጨማሪ ፕሮፌሰር ሮቢን ባርንዝ እንደሚሉት ከሆነ የሴላሪዎስ መጽሐፍ፣ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን ትንቢቶች ያብራራ ሲሆን ወደፊት ከሚመጣ አጠቃላይ ጥፋት እና መከራ በኋላ ዓለም አቀፋዊ መታደስ እንደሚኖርና በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉ ሁሉ እውነተኛ እርካታ እንደሚያገኙ ገልጿል።—2 ጴጥሮስ 3:10-13

ሴላሪዎስ ኢየሱስ ክርስቶስን አስመልክቶ የሰጠው አጭር አስተያየትም ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም። ሴላሪዎስ ሥላሴን በቀጥታ ባይቃረንም “በሰማይ ያለው አባት” እና “ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ” ያላቸውን ልዩነት ተረድቶ ስለነበረ ኢየሱስ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ልጆች ከሆኑት ብዙ አማልክት መካከል አንዱ እንደሆነ ጽፏል።—ዮሐንስ 10:34, 35

ሮበርት ዋላስ አንቲትሪኒታሪያን ባዮግራፊ (1850) በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ የሴላሪዎስ ጽሑፎች፣ በ16ኛው መቶ ዘመን ብዙዎች ስለ ሥላሴ መሠረተ ትምህርት የነበራቸውን አመለካከት የተከተሉ እንዳልነበሩ ገልጸዋል። * በመሆኑም አያሌ ምሁራን፣ ሴላሪዎስ የሥላሴን ትምህርት አይቀበልም  የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ሴላሪዎስ “ስለ እውነተኛው አምላክና ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን እውቀት በሰዎች አእምሮ ውስጥ ለማስረጽ” አምላክ ከተጠቀመባቸው መሣሪያዎች አንዱ እንደሆነ ተገልጿል።

የክርስትና ትምህርት እንደሚመለስ ተስፋ ማድረግ

በ1527 አካባቢ፣ በዘመኑ ከነበሩት ታላላቅ ምሁራን አንዱ እንደሆነ የሚቆጠረው ዮሐንስ ካምፓነስ የተባለ መንፈሳዊ ምሁርም በዊተንበርግ ይኖር ነበር። ካምፓነስ ሃይማኖታዊ ተሐድሶ እንደሚያስፈልግ ቢገነዘብም የማርቲን ሉተር ትምህርቶች አላረኩትም። ለምን?

ካምፓነስ በቁርባን ሥርዓት ላይ ቂጣውና ወይኑ ወደ ኢየሱስ ሥጋና ደም እንደሚለወጡ የሚገልጸውን የምስጢረ ቁርባንን ትምህርት ይቃወም ነበር፤ በሌላ በኩል ደግሞ በጌታ ራት ወቅት፣ ቂጣውና ወይኑ ራሱ የኢየሱስ ሥጋና ደም ነው የሚለውን የማርቲን ሉተርን ትምህርትም አልተቀበለውም። ደራሲ ኦንድሬ ሴጌኒ እንደገለጹት ከሆነ ካምፓነስ ‘ቂጣው ምንጊዜም እንደማይቀየር ሆኖም በምሳሌያዊ መንገድ የክርስቶስን ሥጋ እንደሚወክል’ ያምን ነበር። በ1529 በእነዚሁ ጥያቄዎች ላይ ለመነጋገር በማርበርክ ከተማ በተደረገው ውይይት ላይ ካምፓነስ ከቅዱሳን መጻሕፍት ያገኘውን እውቀት እንዲገልጽ አልተፈቀደለትም። ከዚያ በኋላም በዊተንበርግ አብረውት የነበሩት ሌሎቹ የተሐድሶ አራማጆች ሸሹት።

ዮሐንስ ካምፓነስ ሬስቲትዩሽን በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ስለ ሥላሴ መሠረተ ትምህርት ትክክለኛነት ጥያቄ አንስቷል

የተሐድሶ አራማጆቹን ይበልጥ ያበሳጫቸው ካምፓነስ ስለ አብ፣ ስለ ወልድና ስለ መንፈስ ቅዱስ የነበረው አመለካከት ነው። ካምፓነስ በ1532 ባዘጋጀው ሬስቲትዩሽን የተሰኘ መጽሐፉ ውስጥ ኢየሱስና አባቱ ሁለት የተለያዩ አካላት እንደሆኑ ተናግሯል። አብና ወልድ “አንድ” ናቸው የሚባሉት፣ ባልና ሚስት “አንድ ሥጋ” ናቸው እንደሚባለው መሆኑን የገለጸ ሲሆን ሁለቱም አንድነት ቢኖራቸውም ሁለት የተለያዩ አካላት እንደሆኑ ተናግሯል። (ዮሐንስ 10:30፤ ማቴዎስ 19:5) ካምፓነስ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አብ በወልድ ላይ ያለውን ሥልጣን የገለጸው በባልና ሚስት መካከል ካለው ዝምድና ጋር በሚመሳሰል መንገድ እንደሆነ ተናግሯል፤ ጥቅሱ “የሴት ሁሉ ራስ . . . ወንድ፣ የክርስቶስ ራስ ደግሞ አምላክ [ነው]” ይላል።—1 ቆሮንቶስ 11:3

ስለ መንፈስ ቅዱስስ ምን ማለት ይቻላል? ከዚህ ጋር በተያያዘም የካምፓነስ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነው፤ ካምፓነስ “መንፈስ ቅዱስ ሦስተኛው አካል እንደሆነ ማስረጃ የሚሆን ጥቅስ የለም” በማለት ጽፏል። አክሎም የአምላክ መንፈስ፣ በሥራ ላይ ያለው የአምላክ ኃይል እንደሆነና አምላክ ሁሉንም ነገር ለማዘጋጀትና ለማከናወን በመንፈሱ እንደተጠቀመ ገልጿል።—ዘፍጥረት 1:2

ሉተር፣ ካምፓነስ አምላክን እንደተሳደበና የአምላክ ልጅ ጠላት እንደሆነ ተናግሯል። ሌላ የተሐድሶ አራማጅ ደግሞ ካምፓነስ እንዲገደል ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ሆኖም ካምፓነስ በአቋሙ ጸንቷል። ዘ ራዲካል ሪፎርሜሽን የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ካምፓነስ፣ ለቤተ ክርስቲያን ውድቀት ምክንያት የሆነው ስለ አምላክ ማንነትና በአምላክና በወንድ መካከል ስላለው ግንኙነት የቀድሞዎቹ ሐዋርያትና መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጡትን ሐሳብ ቤተ ክርስቲያን አለመቀበሏ እንደሆነ ያምን ነበር።

የካምፓነስ ዓላማ አንድ ሃይማኖታዊ ቡድን ማደራጀት አልነበረም። ካምፓነስ “በሃይማኖታዊ ቡድኖችና በኑፋቄዎች መካከል” እውነትን ለማግኘት በከንቱ ደክሟል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛውን የክርስትና ትምህርት መልሳ እንደምትቀበል ተስፋ ያደርግ ነበር። ውሎ አድሮ ግን የካቶሊክ ባለሥልጣናት ካምፓነስን ያሰሩት ሲሆን በወህኒ ቤት ከ20 ዓመት በላይ ሳያሳልፍ እንዳልቀረ ይታመናል። የታሪክ ምሁራን ካምፓነስ በ1575 ገደማ እንደሞተ ያምናሉ።

“ሁሉንም ነገር መርምሩ”

ካፒቶ፣ ሴላሪዎስ፣ ካምፓነስና ሌሎችም መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናታቸው እውነቱን ከስህተቱ እንዲለዩ አስችሏቸዋል።  እነዚህ እውነት ፈላጊዎች ከደረሱባቸው መደምደሚያዎች መካከል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማሙት ሁሉም ባይሆኑም እነዚህ ሰዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን በትሕትና መርምረዋል፤ እንዲሁም ያገኙትን እውነት ከፍ አድርገው ተመልክተውታል።

ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት አጋሮቹን “ሁሉንም ነገር መርምሩ፤ መልካም የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ” በማለት መክሯቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:21) የይሖዋ ምሥክሮች እውነትን ለማግኘት በምታደርገው ፍለጋ የሚያግዝህ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የሚል ተስማሚ ርዕስ ያለው መጽሐፍ አዘጋጅተዋል። ይህን መጽሐፍ ያለ ክፍያ ለማግኘት የዚህን መጽሔት ገጽ 16 እንድትመለከት ወይም jw.org/am የተሰኘውን ድረ ገጻችንን እንድትጎበኝ እንጋብዝሃለን።

^ አን.4 የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) በሚለው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ገጽ 44 ላይ የሚገኘውን “እስከ መከር ጊዜ ድረስ አብሮ ይደግ” የሚለውን ሣጥን እንዲሁም የጥር 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 7-8 ከአንቀጽ 14-17ን ተመልከት።

^ አን.8 በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው የግንቦት 2006 ንቁ! ላይ የወጣውን “እውነትን ለማግኘት ብቻውን የደከመው ማይክል ሰርቪተስ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.17 ሴላሪዎስ ክርስቶስን ለማመልከት “አምላክ” የሚለውን ቃል የተጠቀመበትን መንገድ በተመለከተ መጽሐፉ የሚከተለውን ይናገራል፦ “ዴዮስ የሚለውን ቃል ከሁሉ በላይ የሆነውን አምላክ ብቻ ለማመልከት ሲጠቀምበት በትላልቅ ፊደላት (Deus) ያስቀመጠው ሲሆን ወልድን ለማመልከት ግን (deus) በሚል መንገድ አስቀምጦታል።”