በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ግንቦት 2014

 መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት

የይሖዋ ምሥክሮች በኢየሱስ ያምናሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች በኢየሱስ ያምናሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች ከሰዎች ጋር ምን ዓይነት ውይይት እንደሚያደርጉ የሚያሳይ ምሳሌ ከዚህ በታች ቀርቧል። ኤልያስ የሚባል አንድ የይሖዋ ምሥክር ቶማስ የሚባልን ሰው ቤቱ ሄዶ እያወያየው እንዳለ አድርገን እናስብ።

በኢየሱስ ማመን አስፈላጊ ነው

ኤልያስ፦ ታዲያስ፣ ቶማስ። በድጋሚ ስላገኘሁህ ደስ ብሎኛል።

ቶማስ፦ እኔም ደስ ብሎኛል።

ኤልያስ፦ አዲስ የወጡ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን አምጥቼልሃለሁ። በእነዚህ መጽሔቶች ውስጥ ያሉትን ርዕሶች በጣም እንደምትወዳቸው ይሰማኛል።

ቶማስ፦ አመሰግናለሁ። እንዲያውም ልጠይቅህ የምፈልገው ነገር ስላለ ዛሬ በመምጣትህ ደስ ብሎኛል።

ኤልያስ፦ እሺ፤ ጥያቄህ ምንድን ነው?

ቶማስ፦ ባለፈው ከአንድ የሥራ ባልደረባዬ ጋር እያወራሁ ነበር። የሰጠኸኝን መጽሔቶች እንደወደድኳቸው ነገርኩት። እሱ ግን የይሖዋ ምሥክሮች በኢየሱስ ስለማያምኑ ጽሑፎቻቸውን ማንበብ እንደሌለብኝ ነገረኝ። ይህ እውነት ነው? ከአንተ ጋር ስንገናኝ ይህን ጥያቄ እንደምጠይቅህ ለሥራ ባልደረባዬ ነግሬዋለሁ።

ኤልያስ፦ ጥያቄውን ስላነሳህልኝ ደስ ብሎኛል። ከሌላ ሰው ከመስማት ይልቅ በቀጥታ የይሖዋ ምሥክሮችን ለመጠየቅ መምረጥህ ብልህነት ነው። ደግሞም አንድ ሰው የሚያምነውን ነገር ለማወቅ ግለሰቡን ራሱን ከመጠየቅ የተሻለ ምን አማራጭ ይኖራል?

ቶማስ፦ እኔም አንተን የጠየቅኩት ለዚህ ነው።

ኤልያስ፦ የሚገርመው፣ ሰዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ከሚያስቡት በተቃራኒ በኢየሱስ እናምናለን። እንዲያውም ለመዳን በኢየሱስ ማመን ወሳኝ ነገር እንደሆነ እንገነዘባለን።

ቶማስ፦ እኔም እንደምታምኑ ይሰማኝ ነበር፤ ግን የሥራ ባልደረባዬ በኢየሱስ እንደማታምኑ ሲነግረኝ አጠራጠረኝ። ምናልባት ከዚህ በፊት ስለዚህ ጉዳይ አውርተን ስለማናውቅ ሊሆን ይችላል።

ኤልያስ፦ በኢየሱስ ማመን አስፈላጊ እንደሆነ የሚያሳዩ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ባሳይህ ደስ ይለኛል። እነዚህ ጥቅሶች የይሖዋ ምሥክሮች ለሰዎች ሲሰብኩ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሙባቸው ጥቅሶች ናቸው።

ቶማስ፡ እሺ አሳየኝ።

ኤልያስ፦ ለውይይታችን ጥሩ መነሻ እንዲሆነን ኢየሱስ የተናገረውን አንድ ሐሳብ እንመልከት፤ ዮሐንስ 14:6ን ላንብብልህ። ኢየሱስ ይህን ሐሳብ የተናገረው ከሐዋርያቱ መካከል ከአንዱ ጋር ሲወያይ ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ ‘እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ። በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።’” በዚህ ጥቅስ መሠረት ወደ አብ መቅረብ የምንችለው በማን በኩል ብቻ ነው?

ቶማስ፦ በኢየሱስ በኩል።

ኤልያስ፦ ልክ ነው። የይሖዋ ምሥክሮችም ይህን አጥብቀው ያምናሉ። እስቲ አንድ ነገር ልጠይቅህ፦ አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማ ከፈለግን በማን ስም ነው መጸለይ ያለብን?

ቶማስ፦ በኢየሱስ ስም።

ኤልያስ፦ እኔም በዚህ እስማማለሁ። ሁልጊዜ በኢየሱስ ስም ጸሎት የማቀርበው ለዚህ ነው። ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮችም የሚጸልዩት በኢየሱስ ስም ነው።

ቶማስ፦ ኧረ? ጥሩ ነው።

ኤልያስ፦ ሌላ ጥቅስ ደግሞ እንመልከት፤ እስቲ ዮሐንስ 3:16ን እናንብብ። ይህ ጥቅስ በጣም ትልቅ ትርጉም ያለው ከመሆኑ የተነሳ አንዳንዶች የወንጌልን ሐሳብ ጨምቆ እንደያዘ ይሰማቸዋል። በሌላ አባባል ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈውን ሕይወትና አገልግሎቱን በተለመከተ የተጻፈው ነገር ሁሉ ተጨምቆ በዚህ ጥቅስ ሊጠቃለል ይችላል ማለት ነው። ለምን ጥቅሱን አታነበውም?

 ቶማስ፦ እሺ። “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”

ኤልያስ፦ አመሰግናለሁ። ይህን ጥቅስ ታውቀዋለህ?

ቶማስ፦ አዎ፣ ብዙ ጊዜ በቤተ ክርስቲያናችን ሲነበብ ሰምቻለሁ።

ኤልያስ፦ እውነትህን ነው፣ በጣም የታወቀ ጥቅስ ነው። ጥቅሱ ላይ ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ ግን አስተዋልከው? አምላክ የሰው ልጆችን ስለሚወድ የዘላለም ሕይወት እንዳዘጋጀላቸው ኢየሱስ ተናግሯል፤ ግን የዘላለም ሕይወት የምናገኘው ምን ካለን ብቻ ነው?

ቶማስ፦ እምነት ካለን ነው።

ኤልያስ፦ ልክ ነህ። በተለይ ደግሞ ይህ ጥቅስ የሚናገረው፣ የአምላክ አንድያ ልጅ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ማመን ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የዘላለም ሕይወት ለማግኘት በኢየሱስ ማመን አስፈላጊ እንደሆነ ይቀበላሉ፤ ያመጣሁልህ መጽሔት ላይ ይህን የሚጠቁም ሐሳብ ተገልጿል። ገጽ 2 ላይ መጠበቂያ ግንብ የሚታተምበትን ዓላማ አስመልክቶ ሲናገር “እኛ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ሲል በሞተውና በአሁኑ ጊዜ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ በሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት እንዲኖረን ያበረታታል” ይላል።

ቶማስ፦ ይገርማል። በኢየሱስ እንደምታምኑ መጽሔታችሁ ላይ ራሱ በግልጽ ተቀምጦ የለም እንዴ?

ኤልያስ፦ በትክክል።

ቶማስ፦ ታዲያ ሰዎች በኢየሱስ አታምኑም የሚሏችሁ ለምንድን ነው?

ኤልያስ፦ ሰዎች ይህን የሚሉበት በርካታ ምክንያቶች ሊኖሯቸው ይችላል። አንዳንድ ሰዎች እንዲህ የሚሉት ሌሎች ሲያወሩ ሰምተው ነው። ወይም ደግሞ በቤተ ክርስቲያናቸው ስለ እኛ የተሳሳተ ነገር ተነግሯቸው ሊሆን ይችላል።

ቶማስ፦ እንዲያውም አንድ ሐሳብ መጣልኝ፤ ሰዎች በኢየሱስ አያምኑም የሚሏችሁ ራሳችሁን፣ የይሖዋ ምሥክሮች ብላችሁ እንጂ የኢየሱስ ምሥክሮች ብላችሁ ስለማትጠሩ ይሆን?

ኤልያስ፦ ይህም አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ቶማስ፦ ለመሆኑ ከሰዎች ጋር ስትነጋገሩ ይሖዋ ላይ ብዙ ትኩረት የምታደርጉት ለምንድን ነው?

“ስምህን ለእነሱ አሳውቄአለሁ”

ኤልያስ፦ አንደኛ ነገር፣ ይሖዋ የሚለውን የአምላክ የግል ስም መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ ስለምናምን ነው፤ ልጁ ኢየሱስም ቢሆን ያደረገው ይህንኑ ነው። ኢየሱስ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ የተናገረውን እንመልከት። ጥቅሱ የሚገኘው በዮሐንስ 17:26 ላይ ነው። እባክህ ይህን ጥቅስ ታነበው?

ቶማስ፦ እሺ። “እኔን የወደድክበትን ፍቅር እነሱም እንዲያንጸባርቁ እንዲሁም እኔ ከእነሱ ጋር አንድነት እንዲኖረኝ ስምህን ለእነሱ አሳውቄአለሁ፤ ደግሞም አሳውቃለሁ።”

ኤልያስ፦ አመሰግናለሁ። ኢየሱስ የአምላክን ስም እንዳሳወቀ መናገሩን አስተዋልክ? ይህን ያደረገው ለምን ይመስልሃል?

ቶማስ፦ እም . . . እኔ እንጃ።

መዳን ለማግኘት በኢየሱስ ማመን አስፈላጊ ነው

ኤልያስ፦ እስቲ ይህን ጉዳይ ግልጽ የሚያደርግልን አንድ ሌላ ጥቅስ እንመልከት። የሐዋርያት ሥራ 2:21ን ላንብብልህ። “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ይላል። እስቲ አስበው፤ የይሖዋን ስም መጥራት ለመዳን ከሚያስፈልጉት መሥፈርቶች አንዱ ከሆነ ኢየሱስ ይህን መሥፈርት ያውቀዋል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው፤ አይደል?

ቶማስ፦ አዎ፣ ትክክል ነህ።

ኤልያስ፦ ስለዚህ ኢየሱስ ተከታዮቹ የአምላክን ስም እንዲያውቁና እንዲጠቀሙበት የፈለገበት አንዱ ምክንያት ተከታዮቹ እንዲድኑ ነው። እኛም ስለ ይሖዋ ብዙ የምንናገርበት አንዱ ትልቅ ምክንያት ይህ ነው። የአምላክን የግል ስም ማሳወቃችን እንዲሁም ሰዎች ይህን ስም እንዲጠሩት መርዳታችን አስፈላጊ እንደሆነ እናምናለን።

ቶማስ፦ ነገር ግን ሰዎች የአምላክን ስም ባያውቁትም ወይም ባይጠቀሙበትም እንኳ፣ እግዚአብሔር ሲሉ ለማመልከት የፈለጉት እሱን እንደሆነ የታወቀ ነው።

ኤልያስ፦ በእርግጥ፣ ይህ እውነት ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን አምላክ ስሙን ለእኛ በመንገር ወደ እሱ መቅረብ ቀላል እንዲሆንልን አድርጓል።

ቶማስ፦ ምን ማለትህ ነው?

 ኤልያስ፦ እስቲ አስበው፦ የሙሴን ስም የግድ ማወቅ አያስፈልገንም ነበር። ቀይ ባሕርን የከፈለው ወይም አሥርቱን ትእዛዛት የተቀበለው ሰው በሚል ብቻ ልናውቀው እንችል ነበር። የኖኅን ስምስ የግድ ማወቅ ያስፈልገን ነበር? መርከብ ሠርቶ ቤተሰቡንና እንስሳትን ያዳነው ሰው ተብሎ ሊጠቀስ ይችል ነበር። ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ ክርስቶስም እንኳ ከሰማይ መጥቶ ለኃጢአታችን የሞተ ሰው ተብሎ ሊታወቅ ይችል ነበር፤ አይመስልህም?

ቶማስ፦ ይመስለኛል።

ኤልያስ፦ ይሁን እንጂ አምላክ የእነዚህን ግለሰቦች ስም እንድናውቅ አድርጓል። ስማቸውን ማወቃችን ስለ እነሱ የሚገልጸው ታሪክ ይበልጥ እውን እንዲሆንልን አስችሎናል። በመሆኑም ሙሴን፣ ኖኅን፣ ወይም ኢየሱስን አይተናቸው ባናውቅም እንኳ ስማቸውን ማወቃችን ብቻ እውን እንዲሆኑልን ያደርጋል።

ቶማስ፦ ነገሩን እንደዚህ አስቤው አላውቅም ነበር፤ ግን ያልከው ነገር አሳማኝ ነው!

ኤልያስ፦ የይሖዋ ምሥክሮችም የአምላክን ስም ብዙ ጊዜ የሚጠቀሙበት ሌላው ምክንያት ይህ ነው። ሰዎች በይሖዋ አምላክ ላይ እምነት እንዲያዳብሩ ይኸውም እውን እንዲሆንላቸውና ወደ እሱ መቅረብ እንዲችሉ መርዳት እንፈልጋለን። በሌላ በኩል ደግሞ መዳን ለማግኘት በኢየሱስ ማመናችን በጣም አስፈላጊ እንደሆነም እናውቃለን። ምናልባትም ይህን ነጥብ የሚያስረግጥ አንድ ተጨማሪ ጥቅስ ብናነብ ደስ ይለኛል።

ቶማስ፦ እሺ።

ኤልያስ፦ ቅድም ዮሐንስ 14:6ን አንብበን ነበር። እዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ “መንገድ፣ እውነትና ሕይወት” እንደሆነ ተናግሮ ነበር። አሁን ደግሞ ጥቂት ቁጥሮች ወደ ኋላ እንመለስና ዮሐንስ 14:1ን እንመልከት። እባክህ ኢየሱስ በዚህ ጥቅስ ላይ የተናገረውን ሐሳብ ትንሽ ገባ ብለህ ታነበዋለህ?

ቶማስ፦ እሺ። እንዲህ ይላል፦ “በአምላክ እንደምታምኑ በተግባር አሳዩ፤ በእኔም እንደምታምኑ በተግባር አሳዩ።”

ኤልያስ፦ አመሰግናለሁ። ጥቅሱ እውነተኛ እምነት፣ የምርጫ ጉዳይ እንደሆነ ያሳያል? ማለቴ አንድ ሰው ከይሖዋና ከኢየሱስ መርጦ በአንዱ ብቻ ቢያምን በቂ ነው?

ቶማስ፦ አይደለም። ኢየሱስ በሁለቱም ማመን አስፈላጊ እንደሆነ ተናግሯል።

ኤልያስ፦ ትክክል ነህ። ደግሞም በአምላክና በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳለን መናገር ብቻውን በቂ አይደለም ቢባል እንደምትስማማ እርግጠኛ ነኝ። በእርግጥም ከምንናገረው ነገር ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ያስፈልገናል።

ቶማስ፦ በትክክል።

ኤልያስ፦ ይሁን እንጂ አንድ ሰው በአምላክና በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳለው ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው? ይህን ጥያቄ ሌላ ጊዜ ብንወያይበት ምን ይመስልሃል? *

ቶማስ፦ ደስ ይለኛል።

ለመረዳት ያስቸገረህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ አለ? የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያምኑባቸው ነገሮች ወይም ስለ ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው ለማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ስትገናኝ ጥያቄህን ከማቅረብ ወደኋላ አትበል። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከአንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ ናቸው።

^ አን.60 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 12 ተመልከት።