የኢየሱስ ሞት የሚጠቅመን እንዴት ነው?

አምላክ ሰዎችን የፈጠረው ሕመምም ሆነ ሞት ሳይደርስባቸው በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ አስቦ ነበር። ይሁን እንጂ የመጀመሪያው ሰው አዳም ፈጣሪን ባለመታዘዙ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚውን አጣ። እኛም የአዳም ዘሮች እንደመሆናችን መጠን ከእሱ ሞትን ወርሰናል። (ሮም 5:8, 12፤ 6:23) እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ግን አዳም ያሳጣንን ነገር መልሰን እንድናገኝ ሲል ልጁን ኢየሱስን እንዲሞት ወደ ምድር ላከው።ዮሐንስ 3:16ን አንብብ።

ኢየሱስ የሞተው የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ለማስቻል ነው። ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም በሚኖሩበት ጊዜ ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ትችላለህ?

የኢየሱስ ሞት የኃጢአት ይቅርታና ፍጻሜ የሌለው ሕይወት እንድናገኝ በር ከፍቷል። መጽሐፍ ቅዱስ እርጅና፣ በሽታና ሞት የሚወገድበት ጊዜ ሲመጣ በምድር ላይ ያለው ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል ፍንጭ ይሰጠናል።ኢሳይያስ 25:8ን፣ ኢሳይያስ 33:24ን እና ራእይ 21:4, 5ን አንብብ።

የኢየሱስን ሞት ማሰብ የሚኖርብን እንዴት ነው?

ኢየሱስ፣ ቀለል ያለ ሥነ ሥርዓት በማዘጋጀት ሞቱን እንዲያስቡ በመጨረሻው ምሽት ላይ ለተከታዮቹ ነግሯቸዋል። የኢየሱስን ሞት በየዓመቱ በዚህ መንገድ ማሰባችን ኢየሱስና ይሖዋ የሰው ልጆችን ምን ያህል እንደሚወዱ ለማሰላሰል ያስችለናል።—ሉቃስ 22:19, 20ን እና 1 ዮሐንስ 4:9, 10ን አንብብ።

በዚህ ዓመት የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ የሚውለው ሰኞ፣ ሚያዝያ 6 ቀን 2006 ዓ.ም. (ሚያዝያ 14, 2014) ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ነው። አንተም በአካባቢህ ከሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ይህን የመታሰቢያ በዓል እንድታከብር ተጋብዘሃል።—ሮም 1:11, 12ን አንብብ።