“ሃይማኖት አንድ ያደርገናል ወይስ ይከፋፍለናል?” ይህ ዘ ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ በተሰኘው ጋዜጣ ላይ ለአንባቢያን ቀርቦ የነበረ ጥያቄ ነው። ምላሽ ከሰጡት መካከል በጣም ብዙዎቹ ማለትም 89 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ሃይማኖት ከፋፋይ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል።

ሃይማኖትን በመቀላቀል የሚያምኑ ሰዎች ግን ለዚህ ጉዳይ ያላቸው አመለካከት የተለየ ነው። “ስለ ርኅራኄ የማይገደው . . . ፣ ስለ አካባቢ ደኅንነት የማይቆረቆር . . . ፣ ስለ እንግዳ ተቀባይነት ደንታ የሌለው ሃይማኖት ካለ ንገሩኝ” በማለት የወጣቶች የሃይማኖቶች ጥምረት መሥራች የሆኑት ኤቡ ፓቴል ጠይቀዋል።

በእርግጥም ቡዲስቶች፣ ካቶሊኮች፣ ፕሮቴስታንቶች፣ ሂንዱዎች፣ ሙስሊሞችና ሌሎችም ብዙ ሃይማኖቶች ድህነትን ለመዋጋት፣ ለሰብዓዊ መብት ለመታገል፣ ፈንጂ መቅበር እንዲታገድ ወይም ለአካባቢያዊ ችግሮች ትኩረት እንዲሰጥ ለማድረግ ኃይላቸውን ያስተባበሩባቸው ጊዜያት አሉ። በሃይማኖቶች መካከል የጋራ መግባባትና መቻቻል እንዲኖር ለማድረግ ሲባል ብዙ እምነቶች የተሳተፉባቸው የውይይት መድረኮች ተዘጋጅተዋል። እንዲሁም በልዩነታቸው እንደሚደሰቱ ለማሳየት ሻማ የማብራት ሥነ ሥርዓቶችን፣ ፌስቲቫሎችን፣ የሙዚቃና የጸሎት ዝግጅቶችን ጨምሮ በርካታ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋሉ።

ለመሆኑ የሃይማኖቶች ጥምረት በተለያዩ እምነቶች መካከል ያለውን ግጭት ለማስወገድ ያስችላል? ደግሞስ ሃይማኖትን መቀላቀል አምላክ የተሻለ ዓለም ለማምጣት የሚጠቀምበት መንገድ ነው?

አንድነትን ማምጣት ምን ዋጋ ያስከፍላል?

ሃይማኖትን ለመቀላቀል ተብለው ከተቋቋሙ ትላልቅ ድርጅቶች አንዱ፣ ስላገኘው ስኬት ሲናገር ከ200 የሚበልጡ የተለያዩ እምነቶችን የሚወክሉ አባላት እንዳሉትና በ76 አገሮች እየተንቀሳቀሰ እንዳለ ገልጿል። ይህ ድርጅት ዓላማው “ዘላቂ የሃይማኖቶች ትብብር እንዲኖር በየዕለቱ መሥራት” መሆኑን ተናግሯል። ጉዳዩ ግን የመናገሩን ያህል ቀላል ሆኖ አልተገኘም። ለምሳሌ ያህል፣ መሥራቾቹ እንደሚገልጹት ከሆነ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የፈረሙትን ብዙ ሃይማኖቶች ላለማስከፋት ሰነዱ ላይ የሰፈረውን ሐሳብ በጥንቃቄ መጻፍ አስፈልጓቸዋል። ለምን? አንዱ ምክንያት በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ አምላክ ሊካተት ይገባዋል ወይስ አይገባውም በሚለው ጉዳይ ላይ ባለመግባባታቸው ነው። በመጨረሻም አምላክ የሚለው ቃልም ሆነ ሐሳቡ በሰነዱ ውስጥ እንዳይገባ ተደርጓል።

አምላክን ከነአካቴው ካወጡት ታዲያ ሃይማኖት ምን የሚጫወተው ሚና ይኖራል? እንዲህ ያለው ሃይማኖትን የመቀላቀል ንቅናቄ፣ ሃይማኖታዊ ካልሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅት የሚለየውስ በምንድን ነው? ከላይ የተጠቀሰው ድርጅት ራሱን የሚገልጸው እንደ ሃይማኖታዊ ተቋም ሳይሆን የትብብር መንፈስ እንዲኖር ለማድረግ ተብሎ እንደተቋቋመ ድርጅት የሆነው በዚህ ምክንያት ነው።

በጎ ዓላማን ማራመድ ብቻውን በቂ ነው?

“በመሠረቱ ሁሉም ዋና ዋና ሃይማኖቶች የሚሰብኩት መልእክት ተመሳሳይ ይኸውም ፍቅርን፣ ርኅራኄንና ይቅር ባይነትን ነው” በማለት ታዋቂው የሃይማኖቶች ጥምረት አራማጅ ዳላይ ላማ ተናግረዋል። አክለውም “ዋናው ነገር እነዚህ ባሕርያት የዕለታዊ ሕይወታችን ክፍል እንዲሆኑ ማድረጉ ነው” ብለዋል።

በእርግጥ እንደ ፍቅር፣ ርኅራኄና ይቅር ባይነት ያሉት ባሕርያት ጠቃሚ መሆናቸውን የሚክድ የለም። ኢየሱስም ወርቃማው ሕግ እየተባለ የሚጠራውን የሚከተለውን ሐሳብ ተናግሯል፦ “እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር  ሁሉ እናንተም እንደዚሁ ልታደርጉላቸው ይገባል።” (ማቴዎስ 7:12) ይሁን እንጂ እውነተኛው ሃይማኖት በጎ ዓላማን በማራመድ ብቻ የተወሰነ ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ የነበሩትን አምላክን እንደሚያገለግሉ የሚናገሩ ብዙ ሰዎችን አስመልክቶ “በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ አይሁን እንጂ ለአምላክ ቅንዓት እንዳላቸው እመሠክርላቸዋለሁ” ብሎ ነበር። ችግራቸው ምን ነበር? እነዚህ ሰዎች “የአምላክን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውን ጽድቅ ለመመሥረት” እንደሚፈልጉ ጳውሎስ ተናግሯል። (ሮም 10:2, 3) እነዚህ ሰዎች አምላክ ከእነሱ ስለሚፈልገው ነገር ትክክለኛ እውቀት ስላልነበራቸው ቅንዓታቸውም ሆነ እምነታቸው ከንቱ ሆኖባቸዋል።—ማቴዎስ 7:21-23

መጽሐፍ ቅዱስ ሃይማኖትን ስለ መቀላቀል ምን ይላል?

“ሰላም ፈጣሪዎች ደስተኞች ናቸው” በማለት ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:9) ኢየሱስ ሰዎች ከዓመፅ እንዲርቁ በማበረታታትና የተለያየ ሃይማኖት ላላቸው ሰዎች የሰላምን መልእክት በማድረስ፣ የሰበከውን ነገር በሕይወቱ ተግባራዊ አድርጓል። (ማቴዎስ 26:52) ኢየሱስ ለሰበከው የሰላም መልእክት ምላሽ የሰጡ ሰዎች በመካከላቸው የማይበጠስ ፍቅርና አንድነት ነበራቸው። (ቆላስይስ 3:14) ይሁን እንጂ የኢየሱስ ዓላማ ከተለያየ እምነት የመጡ ሰዎች ተስማምተው በሰላም መኖር የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ብቻ ነበር? ሌሎች በሚያደርጓቸው ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥስ ተካፍሎ ነበር?

የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያን ሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስን አምርረው ይቃወሙት የነበረ ከመሆኑም ሌላ ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር። ታዲያ ኢየሱስ ሁኔታውን የያዘው እንዴት ነው? ኢየሱስ “ተዉአቸው። እነሱ ዕውር መሪዎች ናቸው” በማለት ደቀ መዛሙርቱን አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 15:14) ኢየሱስ እንዲህ ካሉ ግለሰቦች ጋር መንፈሳዊ የወንድማማችነት ኅብረት ለመፍጠር ፈቃደኛ አልነበረም።

በግሪክ በምትገኘው ቆሮንቶስ ውስጥ ከጊዜ በኋላ አንድ የክርስቲያን ጉባኤ የተቋቋመ ሲሆን በዚህች ከተማ ብዙ ሃይማኖቶች እንዲሁም የተለያየ ባሕልና አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ይገኙ ነበር። ታዲያ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች ምን አቋም ወሰዱ? ሐዋርያው ጳውሎስ “ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ” በማለት ጻፈላቸው። እንዲህ ማድረግ የሌለባቸው ለምንድን ነው? ጳውሎስ ምክንያቱን ሲያስረዳ “በክርስቶስና በቤልሆር መካከል ምን ስምምነት አለ? ወይም የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ድርሻ አለው?” ብሏል። ከዚያም የሚከተለውን ምክር ሰጣቸው፦ “ስለዚህ ከመካከላቸው ውጡና ራሳችሁን ለዩ።”—2 ቆሮንቶስ 6:14, 15, 17

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሃይማኖት መቀላቀልን አይደግፍም። ‘ታዲያ እውነተኛ አንድነት ሊገኝ የሚችለው እንዴት ነው?’ የሚል ጥያቄ ይፈጠርብህ ይሆናል።

እውነተኛ አንድነትን መገንባት

ድንቅ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆነውና ምድርን የሚዞረው ዓለም አቀፉ የሕዋ ምርምር ጣቢያ የተገነባው 15 ገደማ የሚሆኑ አገሮች ኅብረት ፈጥረው ስለሠሩ ነው። የኅብረቱ አባል አገሮች ምን ዓይነት ንድፍ መጠቀም እንዳለባቸው ባይስማሙ ኖሮ ይህ ውጥን ይሳካ ነበር ብለህ ታስባለህ?

በመሠረታዊ ሐሳብ ደረጃ በዘመናችን ባለው ሃይማኖትን የመቀላቀል ንቅናቄ ውስጥም ሊኖር የሚገባው ሁኔታ ይህ ነበር። በእነዚህ ንቅናቄዎች ውስጥ ትብብርና መከባበር አስፈላጊ እንደሆነ በሰፊው ቢነገርም አንድነት ያለው እምነት ለመገንባት የሚረዳ ሁሉም ሃይማኖቶች የተስማሙበት አንድ ንድፍ ግን የለም። በዚህም የተነሳ ከሥነ ምግባርና ከመሠረታዊ ትምህርት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች አሁንም ሃይማኖቶችን እንደከፋፈሉ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ እንደ ንድፍ የሚቆጠሩ የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ይዟል። በመሆኑም ሕይወታችንን መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው ንድፍ ላይ ተመሥርተን መገንባት እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ተግባራዊ የሚያደርጉ ሰዎች የዘርና የሃይማኖት ጥላቻን አሸንፈው በሰላምና በአንድነት አብረው መሥራት ችለዋል። አምላክም ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ በትንቢት ሲገልጽ “ሰዎች ሁሉ የይሖዋን ስም እንዲጠሩና እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲያገለግሉት ቋንቋቸውን ለውጬ ንጹሕ ቋንቋ እሰጣቸዋለሁ” ብሎ ነበር። አንድነት የሚገኘው ‘ንጹሑን ቋንቋ’ በመማር ማለትም አምላክ ያወጣውን መሥፈርት በመከተል ነው።—ሶፎንያስ 3:9 NW፤ ኢሳይያስ 2:2-4

የይሖዋ ምሥክሮች፣ በአቅራቢያህ ወደሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ መጥተህ በመካከላቸው የሚገኘውን አስደናቂ ሰላምና አንድነት በገዛ ዓይንህ እንድትመለከት ሞቅ ያለ ግብዣ ያቀርቡልሃል።—መዝሙር 133:1