በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

በመካከለኛው ዘመን በስፔን የአምላክን ቃል ማሳወቅ

በመካከለኛው ዘመን በስፔን የአምላክን ቃል ማሳወቅ

“ወደ ስፔን በምጓዝበት ጊዜ እንደምጎበኛችሁና እናንተ ጋር ለጥቂት ጊዜ ቆይቼ ናፍቆቴን ከተወጣሁ በኋላ የተወሰነ መንገድ እንደምትሸኙኝ ተስፋ አደርጋለሁ።”—ሮም 15:24

ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህን ቃላት በሮም ለነበሩት የእምነት አጋሮቹ የጻፈላቸው በ56 ዓ.ም. ገደማ ነው። ጳውሎስ በእርግጥ ወደ ስፔን ተጉዞ ይሁን አይሁን መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። ያም ሆነ ይህ ጳውሎስ ወይም ሌሎች ክርስቲያን ሚስዮናውያን ባደረጉት ጥረት የተነሳ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ምሥራች በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ላይ ስፔን ሊደርስ ችሏል።

ብዙም ሳይቆይ በስፔን ውስጥ የክርስትና እምነት ተከታዮች መብዛት ጀመሩ። በዚህም የተነሳ በዚያ ለነበሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ላቲን መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ። ይህም የሆነበት ምክንያት ስፔን በሮም አገዛዝ ሥር እስከ ሁለተኛው መቶ ዘመን ድረስ በቆየችበት ረጅም ጊዜ ውስጥ በሌሎች የሮም ግዛቶች እንደነበረው ሁሉ በስፔንም ላቲን የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ሆኖ ስለነበር ነው።

የላቲን መጽሐፍ ቅዱሶች ክፍተቱን ደፈኑ

የጥንቶቹ የስፔን ክርስቲያኖች በርካታ የላቲን ትርጉሞችን ያዘጋጁ ሲሆን እነዚህ ትርጉሞች በጥቅሉ ዌተስ ላቲና ሂስፓና በመባል ይጠራሉ። ጀሮም ላቲን ቩልጌት የተባለውን ታዋቂ ትርጉሙን በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. መባቻ ላይ ከማጠናቀቁ በፊት በነበሩት ብዙ ዓመታት ውስጥ በስፔን ይሰራጩ የነበሩት እነዚህ የላቲን መጽሐፍ ቅዱሶች ነበሩ።

ጀሮም በፓለስቲና ምድር በምትገኘው በቤተልሔም ሆኖ ያጠናቀቀው ትርጉም በፍጥነት ስፔን ደረሰ። ሉሲኒየስ የተባለ አንድ ሀብታም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ጀሮም የላቲን መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እያዘጋጀ መሆኑን ሲሰማ የዚህን ትርጉም አንድ ቅጂ በተቻለ መጠን ቶሎ ማግኘት ፈለገ። ስለዚህ ጽሑፉን ገልብጠው ወደ ስፔን እንዲያመጡለት ስድስት ጸሐፍትን ወደ ቤተልሔም ላከ። በቀጣዮቹ መቶ ዘመናት ቩልጌት ቀስ በቀስ በዌተስ ላቲና ሂስፓና ቦታ ተተካ። እነዚህ የላቲን ትርጉሞች የስፔን ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ መልእክቱን እንዲረዳ አስችለውት ነበር። ይሁን እንጂ የሮም አገዛዝ ወደ ፍጻሜው ሲመጣ መጽሐፍ ቅዱስን በሌላ ቋንቋ መተርጎም አስፈላጊ ሆነ።

መጽሐፍ ቅዱስ በሰሌዳ ላይ

በአምስተኛው መቶ ዘመን ቪሲጎቶችና ሌሎች የጀርመን ጎሣዎች ስፔንን ሲወርሩ ጎቲክ የተባለ አዲስ ቋንቋ በአገሪቱ መነገር ጀመረ። ወራሪዎቹ የሥላሴን መሠረተ ትምህርት የማይቀበል አሪያኒዝም የሚባል የክርስትና እምነት ተከታዮች ነበሩ። በተጨማሪም አልፊላስ ጎቲክ የሚባል የራሳቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አምጥተው ነበር። ሬካሬድ የሚባለው የቪሲጎቶች ንጉሥ አሪያኒዝምን በመተው የካቶሊክን ሃይማኖት እስከተቀበለበት እስከ ስድስተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ድረስ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በስፔን በሰፊው ይነበብ ነበር። በኋላም ሬካሬድ የአልፊላስ መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ የአሪያንን መጻሕፍት በሙሉ ሰብስቦ አቃጠላቸው። በዚህም የተነሳ ሁሉም የጎቶች ጽሑፎች ከስፔን ውስጥ ድራሻቸው ጠፋ።

በላቲን ቀበሌኛ የተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ያሉበት ሰሌዳ፣ ስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም.

ያም ሆኖ በዚህ ወቅትም የአምላክ ቃል በስፔን ውስጥ መስፋፋቱን ቀጥሎ ነበር። ከጎቲክ ቋንቋ በተጨማሪ በስፔን ውስጥ በሰፊው የሚነገር አንድ የላቲን ቀበሌኛ ቋንቋ ነበረ፤ ይህ ቋንቋ ከጊዜ በኋላ በኢቤሪያ ባሕረ ገብ መሬት የሚነገሩትን የላቲን ቋንቋዎች ወለደ። * በዚህ የላቲን ቀበሌኛ ከተጻፉ ጽሑፎች እጅግ ጥንታዊ የሆኑት፣ የቪሲጎቶች ሰሌዳዎች በመባል ይጠራሉ፤ ይህን ስያሜ ያገኙት ጽሑፎቹ የተዘጋጁት በሰሌዳዎች ላይ በመሆኑ ነው። የተጻፉት በስድስተኛውና በሰባተኛው መቶ ዘመን ሲሆን አንዳንዶቹ ከመዝሙር መጽሐፍና ከወንጌሎች ላይ የተወሰዱ  ጽሑፎችን ይዘዋል። አንደኛው ሰሌዳ 16ኛውን መዝሙር በሙሉ ይዟል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ሰሌዳዎች ላይ መገኘታቸው በዚያ ዘመን ተራው ሕዝብ የአምላክን ቃል ያነብና ይገለብጥ እንደነበረ ያሳያል። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው መምህራን እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች፣ ማንበብና መጻፍ ለሚማሩ ተማሪዎቻቸው መልመጃ ለመስጠት ይጠቀሙባቸው የነበረ ይመስላል። ሰሌዳዎቹ፣ በመካከለኛው ዘመን በገዳማት ውስጥ በሥዕል የተደገፈ መጽሐፍ ቅዱስ ለማዘጋጀት ይውል ከነበረው ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ብራና ጋር ሲነጻጸሩ በርካሽ ዋጋ የሚገኙ ነበሩ።

በሥዕል ካሸበረቀው በሌዎን ከሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተወሰደ። ይሁን እንጂ እነዚህ ልዩ መጽሐፍ ቅዱሶች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን መልእክት ለሕዝቡ ለማዳረስ እምብዛም አልረዱም

አንድ እጅግ ውድ የሆነ በሥዕል የተደገፈ መጽሐፍ ቅዱስ ስፔን ውስጥ በሌዎን ባለው በሳን ኢሲዶሮ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይገኛል። በ960 ዓ.ም. የተዘጋጀው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ 47 በ34 ሴንቲ ሜትር ስፋት ያላቸው 516 ቅጠሎች ያሉት ሲሆን ክብደቱ 18 ኪሎ ግራም ነው። አሁን በቫቲካን ቤተ መጻሕፍት የሚገኘው ሌላው ትርጉም ደግሞ በ1020 ዓ.ም. ገደማ የተዘጋጀው የሪፖል መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ይህ ትርጉም በመካከለኛው መቶ ዘመን ከነበሩት በሥዕሎች ያሸበረቁ መጽሐፍ ቅዱሶች አንዱ ነው። አንድ መነኩሴ እንዲህ ዓይነት የሥነ ጥበብ ሥራ ሲያዘጋጅ፣ ጎላ ተደርገው ከሚጻፉ የመጀመሪያ ፊደላት መካከል አንዷን ለመጻፍ አንድ ሙሉ ቀን ወይም ርዕሱ የሚጻፍበትን ገጽ ለማዘጋጀት አንድ ሙሉ ሳምንት ፈጅቶበት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እነዚህ ልዩ መጽሐፍ ቅዱሶች የአምላክን ቃል ለሕዝቡ ለማዳረስ እምብዛም አልረዱም።

መጽሐፍ ቅዱስ በአረብኛ

በስምንተኛው መቶ ዘመን ላይ የእስልምና እምነት ተከታዮች አገሪቱን ሲወርሩ በስፔን ውስጥ አንድ ሌላ ቋንቋ መነገር ተጀመረ። ሙስሊሞች ቅኝ ግዛት ባደረጓቸው አካባቢዎች ከላቲን የበለጠ ይነገር የነበረው አረብኛ ስለሆነ መጽሐፍ ቅዱስን በዚህ ቋንቋ መተርጎም አስፈላጊ ሆነ።

ከአምስተኛው እስከ ስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በላቲንና በአረብኛ የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሶች የስፔን ሕዝብ የአምላክን ቃል እንዲያነብብ አስችለዋል

በአረብኛ ቋንቋ የተዘጋጁ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በተለይም ወንጌሎች በመካከለኛው ዘመን በስፔን እንደተሰራጩ ጥርጥር የለውም። በስምንተኛው መቶ ዘመን ጆን የተባሉ የሴቪል ሊቀ ጳጳስ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አረብኛ ሳይተረጉሙት አልቀሩም። የሚያሳዝነው ግን ከእነዚህ የአረብኛ ትርጉሞች መካከል አብዛኞቹ ጠፍተዋል። በአሥረኛው መቶ ዘመን አጋማሽ የተዘጋጀ ወንጌሎችን የያዘ አንድ የአረብኛ ትርጉም በስፔን፣ ሌዎን በሚገኘው ካቴድራል ተጠብቆ ይገኛል።

የወንጌሎች ትርጉም በአረብኛ፣ አሥረኛው መቶ ዘመን ዓ.ም.

 ስፓንኛ ትርጉሞች ብቅ አሉ

በመካከለኛው ዘመን ማለቂያ ላይ ካስቲሊያን ወይም ስፓንኛ በኢቤሪያ ባሕረ ገብ መሬት ብቅ ማለት ጀመረ። ይህ አዲስ ቋንቋ የአምላክን ቃል ለማሰራጨት ጠቃሚ መሣሪያ ሆኖ ነበር። * በስፓንኛ ቋንቋ ከተዘጋጀው ጥንታዊ ትርጉም ላይ የተወሰደ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላ ፋሲዬንዳ ዴ ኡልትራ ማር (ከባሕር ማዶ የተፈጸሙ ክንውኖች) በተሰኘ በ13ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በተዘጋጀ መጽሐፍ ላይ ሰፍሮ ተገኝቷል። ይህ ጽሑፍ ወደ እስራኤል የተደረገን ጉዞ የሚተርክ ሲሆን ከአምስቱ የኦሪት መጻሕፍት፣ ከሌሎች የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት፣ እንዲሁም ከወንጌሎችና ከመልእክቶች ላይ የተወሰዱ ጥቅሶችን አካትቷል።

ንጉሥ አልፎንሶ 10ኛ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ስፓንኛ እንዲተረጎም ድጋፍ ሰጠ

የቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣናት በዚህ ትርጉም አልተደሰቱም ነበር። በዚህም ምክንያት በ1234 ዓ.ም. በተካሄደው የታራጎና ጉባኤ ላይ ሕዝቡ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የተዘጋጁትን ሁሉንም መጽሐፍ ቅዱሶች በአካባቢው ለሚገኙ ቀሳውስት እንዲያስረክቡና መጻሕፍቱ እንዲቃጠሉ ድንጋጌ ወጣ። ደግነቱ ይህ ድንጋጌ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዳይዘጋጅ ማስቆም አልቻለም። ስፓንኛ የጽሑፍ ቋንቋ እንዲሆን በማድረጉ የሚታወቀው ንጉሥ አልፎንሶ 10ኛ (1252-1284) ቅዱሳን መጻሕፍት በአዲሱ ቋንቋ እንዲተረጎሙ ፍላጎት የነበረው ከመሆኑም ሌላ ለሥራው ድጋፍ ሰጠ። በዚህ ዘመን ከተዘጋጁት የስፓንኛ ትርጉሞች መካከል፣ ፕሪአልፎንሳይን የተባለው መጽሐፍ ቅዱስና በዘመኑ ከነበሩት የስፓንኛ የትርጉም ሥራዎች ሁሉ ትልቁ የሆነውና ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የተዘጋጀው የአልፎንሶ መጽሐፍ ቅዱስ ይገኙበታል።

በ13ኛው መቶ ዘመን ከተዘጋጁት የፕሪአልፎንሳይን (በስተ ግራ) እና የአልፎንሶ መጽሐፍ ቅዱስ (በስተ ቀኝ) ላይ የተወሰዱ ገጾች

እነዚህ ሁለቱም ትርጉሞች አዲሱ ስፓንኛ ቋንቋ ተቀባይነት እንዲያገኝና እንዲዳብር ረድተዋል። ቶማስ ሞንትጎሜሪ የተባሉት ምሁር ፕሪአልፎንሳይን የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስ አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፦ “የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ ትክክለኛና ውበት ያለው ቋንቋን በመጠቀም ረገድ የሚደነቅ ሥራ አከናውኗል። . . . ይህ የስፓንኛ ትርጉም ቀላልና ግልጽ ነበር፤ ላቲን ያልተማረው ሕዝብም የሚያስፈልገው እንዲህ ዓይነት ትርጉም ነበር።”

ይሁን እንጂ እነዚህ ጥንታዊ የስፓንኛ መጽሐፍ ቅዱሶች የተተረጎሙት መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈባቸው የመጀመሪያ ቋንቋዎች ሳይሆን ከላቲን ቩልጌት ነው። ከ14ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ አይሁዳውያን ምሁራን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በቀጥታ ከዕብራይስጥ ወደ ስፓንኛ በመተርጎም ብዙ የስፓንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን አዘጋጁ። በወቅቱ በአውሮፓ ውስጥ ትልቁ የአይሁድ ማኅበረሰብ የሚገኘው በስፔን ነበር፤ የአይሁድ ተርጓሚዎች ደግሞ ትርጉሞቻቸውን ለማዘጋጀት በእጅ የተጻፉ ጥሩ የዕብራይስጥ ጽሑፎችን በቀላሉ ማግኘት ይችሉ ነበር። *

ከእነዚህ ትርጉሞች ጉልህ ምሳሌ የሚሆነን በ15ኛው መቶ ዘመን የተጠናቀቀው አልባ የተሰኘው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ሉዊስ ዴ ጉዝማን የሚባል አንድ ስፔናዊ ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ ሞይስስ አራኬል የተባለው ረቢ መጽሐፍ ቅዱስን ካስቲዞ (ንጹሕ) ወደሚባለው ስፓንኛ እንዲተረጉምለት ጠየቀው። ባለሥልጣኑ ይህን አዲስ ትርጉም የፈለገበትን ሁለት ምክንያቶች አቅርቧል። አንደኛው፣ “በዛሬው ጊዜ በላቲን ቋንቋ የሚገኙት መጽሐፍ ቅዱሶች ትርጉማቸው ትክክል ስላልሆነ” ሁለተኛ፣ “እንደ እኛ ያሉ ሰዎች አስቸጋሪ የሆኑ ጥቅሶችን ለመረዳት የኅዳግ ማስታወሻዎች በጣም ስለሚያስፈልጓቸው [ነው]” ብሏል። ይህ ሰው ያቀረባቸው ምክንያቶች በእሱ ዘመን የነበሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለመረዳት ከፍተኛ ጉጉት እንደነበራቸው ያሳያል። በተጨማሪም በሕዝቡ የአፍ መፍቻ ቋንቋ የተተረጎሙ ቅዱሳን መጻሕፍት ከዚያ በፊትም በስፔን በጣም ሰፊ ስርጭት እንደነበራቸው ያመለክታል።

በመካከለኛው ዘመን የነበሩት ተርጓሚዎችና ገልባጮች ምስጋና  ይግባቸውና በስፔን የሚኖሩ የተማሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ያላንዳች እንቅፋት በራሳቸው ቋንቋ ማንበብ ችለው ነበር። በዚህም የተነሳ ታሪክ ጸሐፊው ኽዋን ኦርትስ ጎንዛሌዝ እንደገለጹት “የስፔን ሕዝብ ከሉተር ዘመን በፊት ከኖሩት የጀርመን ወይም የእንግሊዝ ሕዝቦች በላቀ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን ያውቅ ነበር።”

“የስፔን ሕዝብ ከሉተር ዘመን በፊት ከኖሩት የጀርመን ወይም የእንግሊዝ ሕዝቦች በላቀ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን ያውቅ ነበር።”—የታሪክ ምሁር የሆኑት ኽዋን ኦርትስ ጎንዛሌዝ

ይሁን እንጂ በ15ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ ስፓኒሽ ኢንክዊዚሽን በመባል የሚታወቀው የሮም ካቶሊክ ችሎት ቅዱሳን መጻሕፍትን በማንኛውም ቋንቋ መተርጎምም ሆነ እንዲህ ያሉትን ትርጉሞች ይዞ መገኘት በጥብቅ የተከለከለ ነገር እንደሆነ ገለጸ። መጽሐፍ ቅዱስ ለረጅም ዘመናት በስፔን ምድር ታገደ። ይህ እገዳ የተነሳው ሦስት መቶ ዓመታት ካለፉ በኋላ ነው። በዚያ የጨለማ ዘመን ጥቂት ደፋር ተርጓሚዎች በውጭ አገር ሆነው አዳዲስ የስፓንኛ ትርጉሞችን በማዘጋጀት በድብቅ ወደ ስፔን እንዲገቡ አደረጉ። *

መጽሐፍ ቅዱስ በመካከለኛው ዘመን በስፔን ያሳለፈው ታሪክ እንደሚያሳየው ተቃዋሚዎች የአምላክን ቃል ለማፈን በብዙ መንገድ ጥረዋል። ይሁን እንጂ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በቃሉ አማካኝነት እንዳይናገር ዝም ማሰኘት አልቻሉም።—መዝሙር 83:1፤ 94:20

ብዙ ምሁራን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሠሩት ሥራ መጽሐፍ ቅዱስ በመካከለኛው ዘመን በስፔን ውስጥ እንዲታወቅና በስፋት እንዲሰራጭ አስችሏል። ዘመናዊ ተርጓሚዎችም ቅዱሳን መጻሕፍትን ወደ ላቲን፣ ጎቲክ፣ አረብኛ እና ስፓንኛ የተረጎሙትን የቀድሞዎቹን ፈር ቀዳጅ ተርጓሚዎች ፈለግ ተከትለዋል። በዚህም የተነሳ በዛሬው ጊዜ ያሉ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ስፓንኛ ተናጋሪ ሕዝቦች የአምላክን ቃል ልባቸውን በሚነካው በራሳቸው ቋንቋ ማንበብ ችለዋል።

^ አን.10 ከእነዚህ ቋንቋዎች መካከል ካስቲሊያን፣ ካታላን፣ ጋሊሺያንና ፖርቱጋልኛ ይገኙበታል።

^ አን.17 በዛሬው ጊዜ ስፓንኛ 540 ሚሊዮን ለሚያህሉ ሰዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋ ነው።

^ አን.20 በዚህ መጽሔት የታኅሣሥ 1, 2011 እትም ላይ “መለኮታዊው ስም እና አልፎንሶ ዴ ዘሞራ ትክክለኛ ትርጉም ለማዘጋጀት ያደረገው ጥረት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.23 በዚህ መጽሔት የሰኔ 1, 1996 እትም ላይ “ካስዮዶሮ ዴ ሬይና ለስፓኒሽ መጽሐፍ ቅዱስ ያደረገው ተጋድሎ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።