በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እሬት ተብሎ የተጠቀሰው ነገር ምንድን ነው?

እሬት የሚዘጋጀው አጋርውድ ከሚባለው ዛፍ ነበር

በጥንት ዘመን እሬት ለልብስና ለአልጋ ጥሩ መዓዛ ለመስጠት ያገለግል እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (መዝሙር 45:8 የታረመው የ1980 ትርጉም፤ ምሳሌ 7:17 NW፤ ማሕልየ መሓልይ 4:14) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው እሬት የሚዘጋጀው አጋርውድ (አኩዊላሪያ የሚባሉ ዕፅዋት ዝርያ) ከሚባለው ዛፍ ሳይሆን አይቀርም። እንጨቱ ሲበሰብስ ደስ የሚል መዓዛ ያለው ዘይትና ሙጫ ይወጣዋል። እንጨቱ ተፈጭቶ የሚሸጠው ዱቄት “እሬት” ይባል ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እስራኤል ድንኳኖች ሲናገር “በእግዚአብሔር እንደ ተተከሉ ሬቶች” እንደሆኑ ይገልጻል። (ዘኍልቍ 24:5, 6) ይህ አገላለጽ እስከ 30 ሜትር ከፍታ የሚያድገውንና በርካታ ቅርንጫፎች ያሉትን አጋርውድ የተባለውን ዛፍ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። በእርግጥ ይህ ዛፍ በአሁኗ እስራኤል አይገኝም፤ ያም ቢሆን ኤ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል እንደሚገልጸው “ይህ ዛፍና አሁን [በአካባቢው] የማይታወቁ ሌሎች ዛፎች በዚያን ጊዜ ለም በነበረውና ብዙ ሕዝብ በሚኖርበት የዮርዳኖስ ሸለቆ እንዳልነበሩ ለመናገር የሚያስችል ማስረጃ የለም።”

በኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስ ተቀባይነት ያላቸው ምን ዓይነት መሥዋዕቶች ነበሩ?

በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ይሠራበት የነበረው ይህ የሸክላ ማኅተም 2,000 ዓመታት ገደማ ዕድሜ አለው

የአምላክ ሕግ፣ በቤተ መቅደሱ የሚቀርቡት መሥዋዕቶች ሁሉ ምርጥ መሆን እንዳለባቸው ይገልጻል። አምላክ እንከን ያለባቸውን መሥዋዕቶች አይቀበልም። (ዘፀአት 23:19፤ ዘሌዋውያን 22:21-24) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የኖረው አይሁዳዊ ጸሐፊ ፊሎ እንደገለጸው ከሆነ በወቅቱ የነበሩ ካህናት፣ ለመሥዋዕት የሚቀርቡት እንስሳት ሙሉ ጤነኛ መሆናቸውንና “አንዳች እንከን እንደሌለባቸው” ለማረጋገጥ “ከአናታቸው እስከ እግራቸው” ድረስ በጥንቃቄ ይመረምሯቸው ነበር።

ኤድ ፓሪሽ ሳንደርዝ የተባሉ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “[የቤተ መቅደሱ ባለሥልጣናት] እምነት ለሚጥሉባቸው የመሥዋዕት እንስሳት ነጋዴዎች፣ ካህናቱ ቀደም ብለው የመረመሯቸውን እንስሳትና አእዋፍ ብቻ እንዲሸጡ ፈቃድ ይሰጡ የነበረ ይመስላል። እንዲህ ባለው ሁኔታ ደግሞ ሻጩ የሸጠው ነገር ምንም እንከን የሌለበት እንደሆነ የሚገልጽ እንደ ደረሰኝ ያለ ማረጋገጫ ለገዢው ይሰጠዋል ማለት ነው።”

በ2011 የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች እንዲህ ዓይነት ማረጋገጫ ወይም ምልክት በቤተ መቅደሱ አቅራቢያ አግኝተዋል፤ መጠኑ ሳንቲም የሚያህለው ይህ ማረጋገጫ ከሸክላ የተሠራ ማኅተም ሲሆን ከአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. እስከ 70 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ የነበረ እንደሆነ ይገመታል። በላዩ ላይ የተቀረጹት ሁለት የአረማይክ ቃላት “ንጹሕ ለአምላክ” የሚል ትርጉም እንዳላቸው አንዳንድ የአርኪኦሎጂ ባለሞያዎች ተናግረዋል። የቤተ መቅደሱ ባለሥልጣናት እንዲህ ዓይነቶቹን ምልክቶች ለአምልኮ በሚውሉ ነገሮች ወይም ለመሥዋዕት በሚቀርቡ እንስሳት ላይ ያንጠለጥሏቸው እንደነበረ ይታሰባል።