በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  የካቲት 2014

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ዓለምን የቀየረው ጦርነት

ለጦርነትና ለመከራ ዋነኛው ተጠያቂ ማን ነው?

ለጦርነትና ለመከራ ዋነኛው ተጠያቂ ማን ነው?

ኅዳር 11, 1918 አንደኛው የዓለም ጦርነት አበቃ። የሥራ ቦታዎች የተዘጉ ሲሆን ሰዎች በጎዳናዎች ላይ ሲጨፍሩ ይታዩ ነበር። ይሁን እንጂ ደስታቸው ብዙም አልዘለቀም። ዓለምን ያናወጠውን ጦርነት ማብቃት ተከትሎ ከጦር መሣሪያ የከፋ አደገኛ መቅሰፍት ተከሰተ።

ሰኔ 1918 የኅዳር በሽታ (ስፓኒሽ ፍሉ) በመባል የሚታወቅ ገዳይ መቅሰፍት በፈረንሳይ ጦር ሜዳዎች ብቅ አለ። ይህ ቫይረስ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ብዙም ሳይቆይ መታየት ጀመረ። ለምሳሌ ያህል፣ ወረርሽኙ በጥቂት ወራት ውስጥ የገደላቸው በፈረንሳይ የነበሩ የአሜሪካ ወታደሮች ቁጥር የጠላት ጥይት ከፈጃቸው ይበልጥ ነበር። በተጨማሪም ጦርነቱ ሲያበቃ ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱት ወታደሮች በሽታውን ይዘውት ስለሄዱ ወረርሽኙ በፍጥነት በመላው ዓለም ተዛመተ።

ከጦርነቱ በኋላ በነበሩት ዓመታት ረሃብና ኢኮኖሚያዊ ችግርም ተስፋፍቶ ነበር። ጦርነቱ በ1918 ሲያበቃ አብዛኞቹ የአውሮፓ አገሮች ረሃብ አጥቅቷቸው ነበር። በ1923 የጀርመን ገንዘብ ጨርሶ ዋጋ አጥቶ ነበር ለማለት ይቻላል። ከስድስት ዓመታት በኋላ የመላው ዓለም ኢኮኖሚ ተንኮታኮተ። በመጨረሻም በ1939፣ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀመረ፤ ይህ ጦርነት በተወሰነ መጠን ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ጋር የተያያዘ ነበር። ተከታትለው የመጡት እነዚህ ችግሮች መንስኤያቸው ምንድን ነው?

የመጨረሻዎቹ ቀኖች ምልክት

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የአንዳንድ ታሪካዊ ክስተቶችን መንስኤ ለመረዳት ያስችለናል፤ በተለይ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጋር በተያያዘ ይህን ማየት ይቻላል። ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ሕዝብ በሕዝብ ላይ የሚነሳበት’ እንዲሁም በመላው ምድር የምግብ እጥረትና ቸነፈር የሚከሰትበት ጊዜ እንደሚመጣ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 24:3, 7፤ ሉቃስ 21:10, 11) ኢየሱስ፣ እንዲህ  ዓይነቶቹ መቅሰፍቶች የመጨረሻዎቹ ቀኖች ምልክት እንደሚሆኑ ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸው ነበር። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በምድር ላይ ያሉት ወዮታዎች በሰማይ ከተደረገ ጦርነት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ተጨማሪ ሐሳቦች ቀርበዋል።— “በምድርና በሰማይ የተካሄደ ጦርነት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ይኸው የራእይ መጽሐፍ ስለ አራት ፈረሰኞች ይናገራል፤ እነዚህ ፈረሰኞች የአፖካሊፕስ አራት ፈረሰኞች እየተባሉም ይጠራሉ። ከእነዚህ ፈረሰኞች ሦስቱ፣ ኢየሱስ ቀደም ብሎ በትንቢት የተናገራቸውን መቅሰፍቶች ማለትም ጦርነትን፣ ረሃብን እና ቸነፈርን የሚያመለክቱ ናቸው። ( “አራቱ ፈረሰኞች በእርግጥ በመጋለብ ላይ ናቸው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አንደኛው የዓለም ጦርነት እስካሁንም ያላባራ የመከራ ዘመን እንዲጀመር አድርጓል። መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ሁሉ መከራ ዋነኛው ተጠያቂ ሰይጣን እንደሆነ ይገልጻል። (1 ዮሐንስ 5:19) ታዲያ እሱን ሊገታው የሚችል ኃይል ይኖር ይሆን?

የራእይ መጽሐፍ ሰይጣን “ጥቂት ጊዜ” ብቻ እንደቀረው የሚናገር መሆኑ የሚያጽናና ነው። (ራእይ 12:12) ሰይጣን በቁጣ የተሞላውና በምድር ላይ ታይቶ የማይታወቅ መከራ እያስነሳ ያለው ለዚህ ነው። ይሁንና የምናያቸው መከራዎች የሰይጣን ጊዜ እያለቀ መሆኑንም ጭምር ያበስራሉ።

 የዲያብሎስን ሥራ ማፍረስ

በእርግጥም አንደኛው የዓለም ጦርነት በታሪክ ውስጥ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። መላውን ዓለም የሚነካ የጦርነት ዘመን ያመጣ ሲሆን አብዮቶች እንዲቀጣጠሉና ሰዎች በሰብዓዊ መሪዎች ላይ እምነት መጣል እንዲያቅታቸው አድርጓል። በተጨማሪም ሰይጣን ከሰማይ መባረሩን የሚያሳይ ጉልህ ማስረጃ ነው። (ራእይ 12:9) ይህ የማይታይ የዓለም ገዥ የሥልጣን ጊዜው እያለቀ መሆኑን ከተገነዘበ ጨካኝ አምባገነን ጋር የሚመሳሰል እርምጃ እየወሰደ ነው። ይህ የዓለም ገዥ የቀሩት ቀኖች ሲያበቁ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ የተከሰተው የመከራ ዘመንም ያበቃል።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አንጻር፣ በሰማይ ያለው ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅርቡ ‘የዲያብሎስን ሥራ እንደሚያፈርስ’ ለማመን የሚያስችል ምክንያት አለህ። (1 ዮሐንስ 3:8) በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ ይጸልያሉ። አንተስ እንዲህ እያደረግህ ነው? ለዚያ መንግሥት ምስጋና ይግባውና ታማኝ ሰዎች በምድር ላይ የሰይጣን ፈቃድ ሳይሆን የአምላክ ፈቃድ ሲፈጸም ያያሉ። (ማቴዎስ 6:9, 10) በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር፣ የዓለም ጦርነት እንደገና ሊነሳ ቀርቶ ጦርነት የሚባል ነገር እስከ ጭራሹ አይኖርም! (መዝሙር 46:9) ስለዚያ መንግሥት እንድትማር እናበረታታሃለን፤ ይህን ካደረግህ በምድር ላይ ሰላም በሚሰፍንበት ጊዜ መኖር ትችላለህ!—ኢሳይያስ 9:6, 7

^ አን.20 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ተመልከት።