በኢየሱስ ዘመን ለቤተ መቅደሱ መዋጮ የሚደረገው እንዴት ነበር?

የቤተ መቅደሱ መዋጮ የሚከተትባቸው ዕቃዎች ይገኙ የነበረው በሴቶች አደባባይ ውስጥ ነበር። ዘ ቴምፕል—ኢትስ ሚኒስትሪ ኤንድ ሰርቪስስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ዙሪያውን ዓምዶች ያሉት በረንዳ አለ፤ በረንዳው ውስጥ ደግሞ ግድግዳው አጠገብ መዋጮ የሚከተትባቸው አሥራ ሦስት የመዋጮ ዕቃዎች ወይም ‘መለከቶች’ ይገኛሉ።”

እነዚህ የመዋጮ ዕቃዎች መለከት ተብለው የሚጠሩት ከላይ ጠባብ ከታች ግን ሰፊ ስለነበሩ ነው። እያንዳንዱ የመዋጮ ዕቃ ለየትኛው ዓይነት መባ የሚውል መዋጮ እንደሚጨመርበት የሚገልጽ ጽሑፍ ያለው ሲሆን የሚሰበሰበው መዋጮም ለዚያው ዓላማ ይውላል። ኢየሱስ ድሃዋን መበለት ጨምሮ በርካታ ሰዎች መዋጮ ሲያደርጉ ይመለከት የነበረው ሴቶች አደባባይ ውስጥ ሆኖ ነበር።—ሉቃስ 21:1, 2

የቤተ መቅደስ ግብር ለመሰብሰብ የሚያገለግሉ ሁለት የመዋጮ ዕቃዎች የነበሩ ሲሆን አንዱ የዚያን ዓመት ሌላው ደግሞ ያለፈው ዓመት መዋጮ ይከተትባቸው ነበር። ከ3 እስከ 7 ያሉት የመዋጮ ዕቃዎች ደግሞ እንደየቅደም ተከተላቸው ለዋኖሶች፣ ለርግቦች፣ ለእንጨት፣ ለዕጣንና ለወርቅ ዕቃዎች የተተመነው ዋጋ የሚጨመርባቸው ነበሩ። መባ የሚያቀርበው ሰው ለአንድ መባ ከተተመነው ዋጋ በላይ መዋጮ ለማድረግ ከፈለገ የተረፈውን ገንዘብ ከተቀሩት የመዋጮ ዕቃዎች በአንዱ ውስጥ ይጨምረዋል። ስምንተኛው የመዋጮ ዕቃ ከኃጢአት መባ የተረፈው ገንዘብ ይከተትበታል። ከ9 እስከ 12 ያሉት የመዋጮ ዕቃዎች ደግሞ ከበደል መባ፣ ከወፎች መሥዋዕት፣ ናዝራውያን ከሚያቀርቡት መባና በሥጋ ደዌ የተያዙ ሰዎች ከሚያቀርቡት መባ የተረፈው ይጨመርባቸዋል። አሥራ ሦስተኛው የመዋጮ ዕቃ ደግሞ የፈቃደኝነት መዋጮ ይከተትበታል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ ትክክለኛ ታሪክ ጸሐፊ ነው?

ሉቃስ በስሙ የተሰየመውን ወንጌልና የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን ጽፏል። ሉቃስ “ሁሉንም ነገር ከመጀመሪያው አንስቶ በጥንቃቄ” እንደመረመረ ገልጿል፤ አንዳንድ ምሁራን ግን ያሰፈረውን ዘገባ ትክክለኝነት በተመለከተ ጥያቄ ያነሳሉ። (ሉቃስ 1:3) ታዲያ ሉቃስ ያሰፈረው ዘገባ ምን ያህል ትክክለኛ ነው?

ሉቃስ በማስረጃ ሊረጋገጡ የሚችሉ የታሪክ እውነታዎችን ዘግቧል። ለምሳሌ ያህል ሮማውያን ባለሥልጣናትን ለመግለጽ የተለያዩ የማዕረግ ስሞችን ተጠቅሟል፤ በፊልጵስዩስ የነበሩትን ባለሥልጣናት ፕራቶርስ ወይም የሕዝብ አስተዳዳሪዎች፣ በተሰሎንቄ ያሉትን ፖሊትአርክስ ወይም የከተማዋ ገዥዎች፣ በኤፌሶን ያሉትን ደግሞ አይሲአርክስ ወይም የማኅበረሰቡ መሪዎች ሲል ጠርቷቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 16:20፤ 17:6፤ 19:31) ሉቃስ፣ ሄሮድስ አንቲጳስን ቴትራርክ ወይም የአውራጃ ገዢ፣ ሰርግዮስ ጳውሎስን ደግሞ የቆጵሮስ አገረ ገዢ ሲል ጠርቷቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 13:1, 7

ሉቃስ ትክክለኛ የማዕረግ ስሞችን መጠቀሙ ትኩረት የሚስብ ነው፤ ምክንያቱም አንድ የሮም ግዛት የሚተዳደርበት ሁኔታ ሲቀየር የአስተዳዳሪዎቹ የማዕረግ ስምም ይቀየር ነበር። ያም ሆኖ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ብሩስ ሚትስገር “በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የተጠቀሱት የማዕረግ ስሞች ከቦታውና ከጊዜው አንጻር ሲታዩ ምንም ስህተት አይገኝባቸውም” ሲሉ ተናግረዋል። ዊልያም ራምሴ የተባሉት ምሁር ሉቃስን “የተዋጣለት ታሪክ ጸሐፊ” ሲሉ ጠርተውታል።