መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው የትንሣኤ ተስፋ ታምናለህ? * በሞት ካጣናቸው የምንወዳቸው ሰዎች ጋር ዳግም የመገናኘት ተስፋ እንዳለን ማወቁ ብቻ እንኳ ያስደስታል። ይሁንና ይህ ተስፋ እንዲያው የሕልም እንጀራ ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት የተዉትን ምሳሌ መመርመራችን ተገቢ ነው።

ሐዋርያት የሞቱ ሰዎች እንደሚነሱ ጠንካራ እምነት ነበራቸው። ለምን? ቢያንስ ሁለት ምክንያቶች ነበሯቸው። በመጀመሪያ ይህ ተስፋቸው የተመሠረተው በሚከተለው ሐቅ ላይ ነው፦ ኢየሱስ ራሱ ከሞት ተነስቷል። ሐዋርያትና “ከአምስት መቶ የሚበልጡ ወንድሞች” ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን አይተውታል። (1 ቆሮንቶስ 15:6) በተጨማሪም አራቱ የወንጌል ዘገባዎች እንደሚገልጹት ኢየሱስ ከሞት መነሳቱ በሰፊው የሚታወቅና ብዙዎች አምነው የተቀበሉት ሐቅ ነበር።—ማቴዎስ 27:62 እስከ 28:20፤ ማርቆስ 16:1-8፤ ሉቃስ 24:1-53፤ ዮሐንስ 20:1 እስከ 21:25

በሁለተኛ ደረጃ ሐዋርያቱ ኢየሱስ ቢያንስ ሦስት ሰዎችን ከሞት ሲያስነሳ ይኸውም በመጀመሪያ በናይን ከዚያም በቅፍርናሆም በመጨረሻም በቢታንያ ይህን ተአምር ሲፈጽም የዓይን ምሥክሮች ነበሩ። (ሉቃስ 7:11-17፤ 8:49-56፤ ዮሐንስ 11:1-44) በዚህ መጽሔት ላይ ቀደም ሲል እንደተገለጸው ከእነዚህ ተአምራት መካከል የመጨረሻው የተፈጸመው የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ ከሆነ ከአንድ ቤተሰብ ጋር በተያያዘ ነበር። እስቲ በወቅቱ የተከናወነውን ነገር በዝርዝር እንመልከት።

‘ትንሣኤ እኔ ነኝ’

“ወንድምሽ ይነሳል።” ኢየሱስ እነዚህን ቃላት የተናገረው ለማርታ ሲሆን ወንድሟ አልዓዛር ከሞተ አራት ቀናት ሆኖት ነበር። መጀመሪያ ላይ ማርታ ኢየሱስ ምን እያለ እንዳለ አልገባትም ነበር። ስለሆነም ወደፊት የሚፈጸም ነገር እንደሆነ ስላሰበች “እንደሚነሳ አውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” ብሎ ከተናገረ በኋላ ወንድሟን ከሞት ሲያስነሳው ስታይ ምን ያህል በአድናቆት ተውጣ ሊሆን እንደሚችል አስብ።—ዮሐንስ 11:23-25

አልዓዛር ሞቶ በቆየባቸው አራት ቀናት የት ነበር? አልዓዛር በእነዚያ አራት ቀናት በሌላ ቦታ በሕይወት እንደቆየ የሚጠቁም ምንም ነገር አልተናገረም። አልዓዛር ወደ ሰማይ ሄዳ የነበረች የማትሞት ነፍስ አልነበረችውም። ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ሲያስነሳው በሰማይ በአምላክ አጠገብ ሆኖ እንዳይደሰት ወደ ምድር መልሶ አምጥቶታል ማለት አይደለም። ታዲያ አልዓዛር በእነዚያ አራት ቀናት የት ነበር? እንደ እውነቱ ከሆነ መቃብር ውስጥ ተኝቶ ነበር።—መክብብ 9:5, 10

ኢየሱስ ሞትን ከእንቅልፍ ጋር እንዳመሳሰለውና የሞቱ ሰዎች ከዚህ እንቅልፍ ሊነቁ የሚችሉት በትንሣኤ አማካኝነት እንደሆነ አስታውስ። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “‘ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል፤ እኔም ከእንቅልፍ ልቀሰቅሰው ወደዚያ እሄዳለሁ’ አላቸው።  በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ‘ጌታ ሆይ፣ ተኝቶ ከሆነ ይሻለዋል’ አሉት። እርግጥ ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው ስለመሞቱ ነው። እነሱ ግን ለማረፍ ብሎ እንቅልፍ ስለመተኛቱ የተናገረ መሰላቸው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በግልጽ እንዲህ አላቸው፦ ‘አልዓዛር ሞቷል።’” (ዮሐንስ 11:11-14) ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት በማስነሳት ዳግም ሕያው እንዲሆንና ከቤተሰቡ ጋር እንዲቀላቀል አድርጓል። ኢየሱስ ለዚህ ቤተሰብ ምን ያህል ትልቅ ውለታ እንደዋለ ማሰብ ትችላለህ!

ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ ያከናወነው ትንሣኤ ወደፊት የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በሚገዛበት ጊዜ የሚፈጽመውን ተግባር የሚያሳይ ናሙና ነው። * ኢየሱስ ከሰማይ ሆኖ ምድርን በሚገዛበት ወቅት በመቃብር ውስጥ ተኝተው ያሉትን ሙታን ዳግም ሕያው ያደርጋቸዋል። ‘ትንሣኤ እኔ ነኝ’ ያለው በዚህ የተነሳ ነው። በሞት ያጣሃቸውን የምትወዳቸውን ሰዎች ዳግም ስታገኛቸው ምን ያህል እንደምትደሰት አስብ! ከሞት የሚነሱትም ሰዎች ምን ያህል ሊደሰቱ እንደሚችሉ ልትገምት ትችላለህ!—ሉቃስ 8:56

በሞት ያጣሃቸውን የምትወዳቸውን ሰዎች ዳግም ስታገኛቸው ምን ያህል እንደምትደሰት አስብ!

የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ እምነት

ኢየሱስ ማርታን “በእኔ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ ቢሞት እንኳ እንደገና ሕያው ይሆናል፤ በሕይወት ያለና በእኔ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ ደግሞ ፈጽሞ አይሞትም” ብሏት ነበር። (ዮሐንስ 11:25, 26) ኢየሱስ በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት ከሞት የሚያስነሳቸው ሰዎች በእሱ ማመናቸውን እስከቀጠሉ ድረስ ለዘላለም በሕይወት የመኖር አጋጣሚ ይኖራቸዋል።

“በእኔ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ ቢሞት እንኳ እንደገና ሕያው ይሆናል።”—ዮሐንስ 11:25

ኢየሱስ ስለ ትንሣኤ የሚገልጸውን ይህን አስደናቂ ነገር ከተናገረ በኋላ ማርታን “ይህን ታምኛለሽ?” በማለት ራሷን እንድትመረምር የሚያነሳሳ ጥያቄ አቀረበላት። እሷም “አዎ፣ ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው የአምላክ ልጅ ክርስቶስ መሆንህን አምናለሁ” አለችው። (ዮሐንስ 11:26, 27) አንተስ? ማርታ ስለ ትንሣኤ የነበራት ዓይነት እምነት ማዳበር ትፈልጋለህ? ይህን ለማድረግ የሚያስችልህ የመጀመሪያው እርምጃ አምላክ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ እውቀት መቅሰም ነው። (ዮሐንስ 17:3፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:4) እንዲህ ያለው እውቀት እምነት እንድታዳብር ሊረዳህ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ርዕሰ ጉዳይ አስመልክቶ ምን እንደሚያስተምር ማወቅ ትፈልጋለህ? ታዲያ ለምን የይሖዋ ምሥክሮችን አትጠይቃቸውም? አስደናቂ ስለሆነው ስለትንሣኤ ተስፋ ከአንተ ጋር ለመወያየት ደስተኞች ናቸው።

^ አን.2 በዚህ እትም ገጽ 6 ላይ የሚገኘውን “ሞት የሁሉ ነገር ፍጻሜ አይደለም!” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.9 መጽሐፍ ቅዱስ የትንሣኤን ተስፋ አስመልክቶ ስለሚሰጠው ተስፋ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 7 ተመልከት።