በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 የሕይወት ታሪክ

ይሖዋን ማገልገል የዕድሜ ልክ ሥራዬ እንዲሆን መረጥኩ

ይሖዋን ማገልገል የዕድሜ ልክ ሥራዬ እንዲሆን መረጥኩ

ጥር 1937 ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተመረቅሁ በኋላ በማዕከላዊ ምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ በምንኖርበት አቅራቢያ ባለው የአይዋ ዩኒቨርሲቲ ተመዘገብኩ። ሕይወቴ በትምህርትና የትምህርቴን ወጪ ለመክፈል በመሥራት የተወጠረ ስለነበር ለሌላ ነገር ጊዜ አልነበረኝም። ከልጅነቴ ጀምሮ ዋነኛ ግቤ ስለ ረጃጅም ሕንፃዎችና ስለ ተንጠልጣይ ድልድዮች ማጥናት ነበር።

በ1942 መጀመሪያ ላይ ማለትም ዩናይትድ ስቴትስ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ ስትገባ የአምስተኛ ዓመት የኮሌጅ ትምህርቴን በመከታተል ላይ የነበርኩ ሲሆን በወቅቱ በሥነ ሕንፃ ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪዬን ለመያዝ የቀረኝ ጥቂት ወራት ብቻ ነበር። የምኖረው ከሁለት ልጆች ጋር አንድ ቤት ውስጥ ነበር። ከልጆቹ አንዱ “ምድር ቤት ያሉትን ልጆች እየመጣ የሚጠይቃቸውን” ሰው እንዳነጋግር ሐሳብ አቀረበልኝ። እዚያ ስሄድ ይሖዋ ምሥክር የሆነውን ጆን ዖቶ (ጆኒ) ብሬመርን አገኘሁት። ለቀረበለት ጥያቄ ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ የሚያገኝበት መንገድ በጣም አስገረመኝ። በጣም ስለተደነቅሁ ከጆኒ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሬ ማጥናትና ውሎ አድሮም ሁኔታዎች በሚፈቅዱልኝ ጊዜ ሁሉ ከእሱ ጋር በስብከቱ ሥራ መካፈል ጀመርኩ።

የጆኒ አባት ዖቶ የይሖዋ ምሥክር የሆነው በዎልነት አይዋ የአንድ ባንክ ፕሬዚዳንት ሳለ ነበር። ዖቶ ሙሉ ጊዜውን አምላክን ለማገልገል ሲል ሥራውን ለቀቀ። የእሱም ሆነ የቤተሰቡ መልካም ምሳሌነት ከጊዜ በኋላ እኔም አንድ ትልቅ ውሳኔ እንዳደርግ አበረታቶኛል።

ውሳኔ የማደርግበት ጊዜ ደረሰ

አንድ ቀን የዩኒቨርሲቲው ዲን፣ ውጤቴ እየቀነሰ መሆኑንና በፊት በነበረኝ ጥሩ ውጤት ብቻ መመረቅ እንደማልችል ነገረኝ። በዚህ ጊዜ ይሖዋ አምላክ መመሪያ እንዲሰጠኝ አጥብቄ ጸለይኩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ምህንድስና የሚያስተምረኝን ፕሮፌሰር እንዳነጋግር ተጠራሁ። እሱም አንድ መሃንዲስ እንዲልክ በቴሌግራም እንደተጠየቀና እኔ ሥራውን እንደምቀበል ተማምኖ እሺ ማለቱን ነገረኝ። እኔም ፕሮፌሰሩን ካመሰገንኩት በኋላ ይሖዋን ማገልገል የዕድሜ ልክ ሥራዬ እንዲሆን የመረጥኩበትን ምክንያት ገለጽኩለት። ሰኔ 17 ቀን 1942 ተጠመቅሁና ወዲያውኑ ማለት ይቻላል አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ፤ አቅኚ የሚለው መጠሪያ ሙሉ ጊዜያቸውን አምላክን ለማገልገል የሚያውሉ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው።

በኋላም በዚሁ ዓመት ለወታደራዊ አገልግሎት እንደተመለመልኩ የሚገልጽ ጥሪ ደረሰኝ፤ ከዚያም በጦርነት ለመካፈል ሕሊናዬ የማይፈቅድልኝ ለምን እንደሆነ ለማስረዳት በምልመላ ቦርዱ ፊት ቀረብኩ። መልካም ባሕርይ ብሎም በምህንድስና ልዩ ችሎታ እንዳለኝ የኮሌጅ ፕሮፌሰሮቼ የጻፉልኝን ደብዳቤ አቀረብኩ። እንዲህ ያለ ጥሩ ማስረጃ ባቀርብም 10,000 የአሜሪካ ዶላር መቀጮ እንድከፍልና በሌቨንወርዝ፣ ካንሳስ በሚገኝ የዩናይትድ ስቴትስ ወህኒ ቤት ለአምስት ዓመታት እንድታሰር ተፈረደብኝ።

በወህኒ ቤት ያሳለፍኩት ሕይወት

ሌቨንወርዝ ፌዴራል ማረሚያ ቤት በዛሬው ጊዜ፤ 230 የምንሆን የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ማረሚያ ቤት ታስረን ነበር

ከ230 በላይ የሆኑ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች በሌቨንወርዝ ፌዴራል ማረሚያ ቤት ሥር በሚገኘው የእርሻ ሥራ በሚካሄድበት ወህኒ ቤት ውስጥ ታስረው ነበር። በዚያም በበርካታ ዘቦች እየተጠበቅን በእርሻው ላይ እንሠራ ነበር። አንዳንዶቹ ዘቦች ስለ  ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማችን ስለሚያውቁ ለእኛ ጥሩ አመለካከት ነበራቸው።

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስብሰባዎቻችንን በወህኒ ቤቱም ለመቀጠል ባደረግነው ጥረት የተወሰኑ ዘቦች ተባብረውናል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ እስር ቤቱ ስናስገባ ይረዱን ነበር። እንዲያውም የወህኒ ቤቱ ኃላፊ መጽናናት (አሁን ንቁ! ይባላል) መጽሔት ኮንትራት ገብቶ ነበር።

ከእስር ተፈትቶ ወደ ሚስዮናዊ አገልግሎት መግባት

የተፈረደብኝ አምስት ዓመት ቢሆንም ሦስቱን ዓመት እንዳጠናቀቅኩ ይኸውም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከጥቂት ወራት በኋላ የካቲት 16 ቀን 1946 ተፈታሁ። ወዲያውኑም አቅኚ በመሆን የሙሉ ጊዜ አገልግሎቴን ቀጠልኩ። ወደ ካንሳስ ተመልሼ በመሄድ በሌቨንወርዝ ከተማ እንዳገለግል ተመደብኩ። በዚያ ሕዝቡ ለይሖዋ ምሥክሮች ያለው ጭፍን ጥላቻ ከፍተኛ ስለነበረ እዚያ መመደቤ አስፈርቶኝ ነበር። ራሴን ለመደጎም የሚያስችል ሥራ ማግኘትም አስቸጋሪ ነበር፤ ከሁሉ የባሰው ግን መኖሪያ ቤት ማግኘት ነው።

ትዝ ይለኛል አንድ ቀን፣ ከቤት ወደ ቤት ሳገለግል ከዚህ በፊት የማውቀው አንድ የእስር ቤት ዘብ አጋጠመኝ፤ እሱም “ሂድ ከዚህ ጥፋ!” ብሎ ጮኸብኝ። የቤዝቦል ዱላ በእጁ ይዞ ስለነበር በድንጋጤ በርሬ ጠፋሁ። ሌላ ቤት ያገኘኋት ሴት ደግሞ “ቆይ አንዴ ጠብቀኝ” አለችኝና ገብታ በሩን ዘጋችው። እኔም መጠበቅ ጀመርኩ፤ ከዚያም በድንገት የፎቁ መስኮት ተከፈተና እጣቢ ውኃ አለበሰችኝ። ያም ሆኖ በአገልግሎቴ በረከቶችን አግኝቼ ነበር። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ሰጥቻቸው የነበሩ አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ከጊዜ በኋላ ሰማሁ።

በ1943 በሰሜናዊው የኒው ዮርክ ክፍል ለሚስዮናውያን አንድ አዲስ ትምህርት ቤት ተቋቁሞ ነበር። እኔም እዚያ እንድገባ የተጋበዝኩ ሲሆን የካቲት 8 ቀን 1948 ከትምህርት ቤቱ አሥረኛ ክፍል ተመረቅሁ። ይህ ትምህርት ቤት የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተብሎ ይጠራል። ከተመረቅሁ በኋላ ጎልድ ኮስት ትባል በነበረችው በአሁኗ ጋና ተመደብኩ።

ጎልድ ኮስት ስደርስ ለመንግሥት ባለሥልጣናትና ለአውሮፓውያን እንድሰብክ ተመደብኩ። ቅዳሜና እሁድ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ አገለግል የነበረ ሲሆን የጉባኤውን አባላት ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት አግዛቸው ነበር። በተጨማሪም በገለልተኛ ስፍራ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ያሉበት ቦታ ድረስ እየሄድኩ እጠይቃቸውና ለአገልግሎት አሠለጥናቸው ነበር። እንዲሁም በአቅራቢያው በምትገኘው አይቮሪ ኮስት ትባል በነበረችው በአሁኗ ኮት ዲቩዋር በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት አገልግያለሁ።

በእነዚያ አካባቢዎች ሳገለግል እንደ አፍሪካውያኑ መኖርን ማለትም ከጭቃ በተሠራ ጎጆ ቤት ውስጥ ማደርን፣ በእጅ መብላትንና እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ ያደርጉት እንደነበረው ሜዳ ላይ መጸዳዳትን ተማርኩ። (ዘዳግም 23:12-14) እንዲህ ማድረግ እኔም ሆንኩ አብረውኝ የሚያገለግሉት ሚስዮናውያን በሌሎች ዘንድ መልካም ስም እንድናተርፍ ረድቶናል። በአካባቢው ያሉ አንዳንድ የባለሥልጣናት ሚስቶች ከእኛ  ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረው ነበር። በመሆኑም ተቃዋሚዎች ሲያስቸግሩንና ቪዛችንን እንድንነጠቅ የሚያዝዝ ፈቃድ ሲያገኙ የባለሥልጣናቱ ሚስቶች ባሎቻቸውን በማግባባት ውሳኔዎቹ እንዲሻሩልን ያደርጉ ነበር።

በአፍሪካ የሚያገለግሉ ብዙ ሚስዮናውያን እንደሚያጋጥማቸው እኔም በወባ በሽታ ተያዝኩ። በጣም ያንቀጠቅጠኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ ኃይለኛ ትኩሳት ስለነበረኝ መቃዠት ጀመርኩ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ መንጋጭላዬ እንዳይንገጫገጭ በእጄ እይዘው ነበር። ይሁን እንጂ ከአገልግሎቴ ደስታና እርካታ አግኝቼ ነበር።

በአፍሪካ በቆየሁባቸው አራት ዓመታት ውስጥ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ ከመልቀቄ በፊት ከተዋወቅኋት ኢቫ ሃልክዊስት ጋር እጻጻፍ ነበር። እሷም የይሖዋ ምሥክሮች በኒው ዮርክ ያንኪ ስታዲየም በሚያደርጉት ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ከጊልያድ ትምህርት ቤት 21ኛው ክፍል ሐምሌ 19 ቀን 1953 እንደምትመረቅ ተረዳሁ። ከአንድ የመርከብ ካፒቴን ጋር የመጓጓዣዬን ዋጋ ለመቻል በጉዞ ላይ እየሠራሁለት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዲወስደኝ ዝግጅት አደረግሁ።

በጉዞ ላይ ከባድ ማዕበል የሚያጋጥመን ጊዜ ነበር፤ ይሁንና ከ22 ቀናት ጉዞ በኋላ ወደ ወደቡ ደረስን። ከዚያም ኢቫን ለማግኘት ብሩክሊን ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት አመራሁ። እዚያም የኒው ዮርክን ወደብና አድማሱን ማየት በሚቻልበት አንድ ሰገነት ላይ ሆነን የጋብቻ ጥያቄ አቀረብኩላት። ቆየት ብሎም ኢቫ ከእኔ ጋር በጎልድ ኮስት ለማገልገል መጣች።

የቤተሰብ ኃላፊነትን መወጣት

ከኢቫ ጋር በአፍሪካ ለተወሰኑ ዓመታት ካገለገልን በኋላ አባቴ ካንሰር እንደያዘውና ሊሞት እንደተቃረበ የሚገልጽ ደብዳቤ ከእናቴ ዘንድ ደረሰኝ። ኢቫ እና እኔ ፈቃድ ወስደን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለስን። የአባቴ ጤንነት በፍጥነት እያሽቆለቆለ በመሄዱ ብዙም ሳይቆይ አረፈ።

ወደ ጋና ተመልሰን ለአራት ዓመታት ገደማ ከቆየን በኋላ እናቴ በጠና እንደታመመች ሰማሁ። አንዳንድ ወዳጆቻችን እናቴን ለመንከባከብ ወደ ቤት እንድንመለስ ሐሳብ አቀረቡልን። ይህ፣ ካደረግናቸው ውሳኔዎች ሁሉ በጣም ከባዱ ነበር። አሥራ አንድ ዓመት ከኢቫ ጋር፣ በአጠቃላይ 15 ዓመታት በሚስዮናዊነት አገልግሎት ካሳለፍኩ በኋላ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለስን።

በጎልድ ኮስት (በአሁኗ ጋና) ከአንድ የአካባቢው ባለሥልጣን ጋር

በቀጣዮቹ ዓመታት ተራ በተራ እናቴን እንንከባከብ የነበረ ሲሆን አቅሟ ሲፈቅድላት ደግሞ ወደ ስብሰባ ይዘናት እንሄድ ነበር። እናቴ ጥር 17 ቀን 1976 በ86 ዓመቷ አረፈች። ይሁን እንጂ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ከዚህም የከበደ ችግር አጋጠመን። ኢቫ ካንሰር እንዳለባት በሐኪም ምርመራ ተረጋገጠ። በሽታውን ለመታገል የቻልነውን ሁሉ ጥረት ብናደርግም በመጨረሻ በትግሉ ተሸነፈችና በ70 ዓመት ዕድሜዋ ሰኔ 4 ቀን 1985 አረፈች።

የምወደውን ሥራ በምሠራበት ወቅት ያጋጠሙኝ ሌሎች ነገሮች

በ1988 የጋናን ቅርንጫፍ ቢሮ ለማስፋፋት የተገነቡት ተጨማሪ ሕንፃዎች ለአምላክ አገልግሎት ሲወሰኑ በዚያ እንድገኝ ተጋብዤ ነበር። እንዴት ያለ የማይረሳ ወቅት ነበር! ከጊልያድ ተመርቄ ወደ ጋና ስሄድ ማለትም 40 ከሚያህሉ ዓመታት በፊት በዚያ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በጥቂት መቶዎች ብቻ የሚቆጠሩ ነበሩ። በ1988 ቁጥራቸው 34,000 ደርሶ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ 114,000 ሊሞላ ተቃርቧል!

ጋናን ከጎበኘሁ ከሁለት ዓመት በኋላ ነሐሴ 6 ቀን 1990 የኢቫ የቅርብ ጓደኛ ከነበረችው ከቤቲ ሚለር ጋር ተጋባን። አንድ ላይ ሆነን ይሖዋን ማገልገል የዕድሜ ልክ ሥራችን እንዲሆን መርጠናል። አያቶቻችንንና ወላጆቻችንን እንዲሁም ኢቫን በገነት ውስጥ እንደገና የምናይበትን ቀን እንናፍቃለን።—የሐዋርያት ሥራ 24:15

ከ70 ለሚበልጡ ዓመታት ይሖዋን የማገልገል ልዩ መብት ማግኘቴን ሳስብ እንባ በዓይኔ ግጥም ይላል። የእሱን አገልግሎት የዕድሜ ልክ ሥራዬ አድርጌ እንድይዘው ስለረዳኝ ይሖዋን ብዙ ጊዜ አመሰግነዋለሁ። ምንም እንኳ አሁን በ90ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምገኝ ብሆንም በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉም የላቀው መሃንዲስ የሆነው ይሖዋ በዚህ ሥራ እንድቀጥል የሚያስፈልገኝን ጥንካሬና ብርታት አሁንም እየሰጠኝ ነው።