ረዓብ፣ ጎሕ ሲቀድ በመስኮቷ ዘልቃ በኢያሪኮ ዙሪያ ያለውን ሜዳ ቃኘች። ወራሪው የእስራኤል ሠራዊት ሜዳው ላይ ፈስሷል። እነዚህ እስራኤላውያን፣ ከዚያ በፊት ባሉት ቀናት እንዳደረጉት ሁሉ የጆሮ ታምቡር የሚበሳ የመለከት ድምፅ እያሰሙና በእግራቸው አቧራውን እያቦነኑ ከተማዋን መዞር ጀመሩ።

ረዓብ የምትኖረው በኢያሪኮ ነው፤ በመሆኑም የከተማዋን ጎዳናዎችና መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ሕዝብ የሚርመሰመስባቸውን ገበያዎችና ሱቆች አሳምራ ታውቃቸዋለች። ነዋሪዎቹንም ቢሆን በደንብ ታውቃቸዋለች። ባለፉት ተከታታይ ቀናት እስራኤላውያን፣ ከተማዋን በቀን አንድ ጊዜ በመዞር እንግዳ የሆነ ነገር እያደረጉ ነው፤ በዚህ ሁኔታ ቀናት ሲያልፉ የሕዝቡ ልብ በፍርሃት እየቀለጠ እንደሄደ ረዓብ ማስተዋሏ አልቀረም። ይሁንና የእስራኤላውያን መለከት በኢያሪኮ ጎዳናዎችና አደባባዮች ላይ ሲያስተጋባ ረዓብ እንደ ሌላው የኢያሪኮ ሕዝብ በፍርሃትና በተስፋ መቁረጥ አልተዋጠችም።

ረዓብ፣ ዛሬም ገና ጎህ ከመቅደዱ የእስራኤል ሠራዊት ኢያሪኮን መዞር ሲጀምር ተመለከተች፤ ይህ ሰባተኛው ቀን መሆኑ ነው። መለከቶችን የሚነፉትንና አምላካቸው ይሖዋ በመካከላቸው መገኘቱን የሚያመለክተውን ቅዱስ ታቦት የተሸከሙትን ካህናት በወታደሮቹ መሃል አየች። ረዓብ በግዙፉ የኢያሪኮ ቅጥር ላይ በሚገኘው መስኮቷ ላይ ያንጠለጠለችውን ቀይ ፈትል እየነካካች በሐሳብ ስትዋጥ በዓይነ ሕሊናችን ልናያት እንችላለን። ይህን ፈትል ስትመለከት፣ እሷና ቤተሰቧ በከተማይቱ ላይ ከሚመጣው ጥፋት እንደሚድኑ የተሰጣትን ተስፋ ማስታወሷ አይቀርም። ረዓብ ሕዝቧን አሳልፋ የሰጠች ከሃዲ ልትባል ትችላለች? ይሖዋ ከዳተኛ እንደሆነች አድርጎ አልተመለከታትም፤ እንዲያውም አስደናቂ እምነት እንዳላት ሴት አድርጎ ቆጥሯታል። እስቲ የረዓብን ታሪክ ከመጀመሪያው አንስተን እንመልከት፤ ይህን ስናደርግ ከእሷ ምን ትምህርት እንደምናገኝ ማስተዋል እንችላለን።

ጋለሞታዪቱ ረዓብ

ረዓብ ጋለሞታ ነበረች። ቀደም ባሉት ዘመናት የነበሩ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች፣ ይህን ሐሳብ መቀበል ስለከበዳቸው ረዓብ የማደሪያ ክፍሎችን የምታከራይ ሴት እንደሆነች ገልጸዋል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሐቁን ሳይሸፋፍን በግልጽ አስቀምጦታል። (ኢያሱ 2:1፤ ዕብራውያን 11:31፤ ያዕቆብ 2:25) በከነዓናውያን ማኅበረሰብ ውስጥ ዝሙት አዳሪነት ተቀባይነት ያለው ሥራ ሳይሆን አይቀርም። ያም ቢሆን ይሖዋ ትክክል ወይም ስህተት የሆኑ ነገሮችን እንዲጠቁመን ለሁላችንም ሕሊና ሰጥቶናል፤ በመሆኑም አንድ ነገር በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ መሆኑ ከሕሊና ወቀሳ አያድነንም። (ሮም 2:14, 15) ረዓብም አኗኗሯ አሳፋሪ እንደሆነ ሳይሰማት አይቀርም። ምናልባትም በዛሬው ጊዜ እንዲህ ባለው ሕይወት ውስጥ እንደሚገኙት እንደ ብዙዎቹ ሰዎች ሁሉ እሷም ለቤተሰቧ የሚያስፈልገውን ማቅረብ ከፈለገች ሌላ አማራጭ እንደሌላትና ከዚህ ሕይወት ማምለጥ እንደማትችል ይሰማት ይሆናል።

ረዓብ የተሻለ ሕይወት ቢኖራት እንደምትመኝ ጥርጥር የለውም። በትውልድ አገሯ፣ በሥጋ ዘመዳሞች መካከልና ከእንስሳት ጋር የሚፈጸም ሩካቤ ሥጋን ጨምሮ ወራዳ ምግባርና ዓመፅ ተስፋፍቶ ነበር። (ዘሌዋውያን 18:3, 6, 21-24) እንዲህ ዓይነት ክፉ ነገሮች እንዲበዙ ሃይማኖት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። በቤተ መቅደሶቹ ውስጥ የሚከናወኑት የአምልኮ ሥርዓቶች የፆታ ብልግና መፈጸምን ያካትቱ ነበር፤ እንዲሁም እንደ በዓልና ሞሎክ ላሉት አጋንንታዊ አማልክት የሚቀርበው አምልኮ ሕፃናትን በሕይወት እያሉ በእሳት መሥዋዕት ማድረግን ይጨምራል።

በከነዓን የሚፈጸመው ነገር ከይሖዋ ዓይን የተሰወረ አልነበረም። እንዲያውም ከነዓናውያን ይፈጽሟቸው በነበሩት ብዙ ክፉ ተግባሮች ምክንያት ይሖዋ “ምድሪቱም ሳትቀር ረከሰች፤ እኔም ስለ ኀጢአቷ ቀጣኋት፤ ስለዚህ የሚኖሩባትን ሰዎች ተፋቻቸው”  በማለት ተናግሯል። (ዘሌዋውያን 18:25) ምድሪቱ ‘ስለ ኃጢአቷ የተቀጣችው’ እንዴት ነበር? “አምላክህ እግዚአብሔር እነዚህን ሕዝቦች ጥቂት በጥቂት ከፊትህ ያስወጣቸዋል” ተብሎ ለእስራኤላውያን ተነግሯቸው ነበር። (ዘዳግም 7:22) በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ይሖዋ ምድሪቱን ለአብርሃም ቤተሰብ እንደሚሰጥ ቃል ገብቶ ነበር፤ አምላክ ደግሞ ‘ሊዋሽ አይችልም።’—ቲቶ 1:2፤ ዘፍጥረት 12:7

በሌላ በኩል ግን ይሖዋ፣ በምድሪቱ ላይ የሚኖሩት አንዳንድ ሕዝቦች ሙሉ በሙሉ እንዲጠፉ ወስኖ ነበር። (ዘዳግም 7:1, 2) ይሖዋ ጻድቅ የሆነ “የምድር ሁሉ ዳኛ” እንደመሆኑ መጠን የእያንዳንዱን ሰው ልብ በማንበብ እነዚህ ሕዝቦች ክፋትና ወራዳ ምግባር የተሞላበት አካሄዳቸውን ፈጽሞ እንደማይቀይሩ አውቋል። (ዘፍጥረት 18:25፤ 1 ዜና መዋዕል 28:9) ረዓብ፣ ጥፋት በተፈረደባት በዚህች ከተማ ውስጥ ስትኖር ምን ተሰምቷት ይሆን? ስለ እስራኤላውያን የሚወራው ነገር ጆሮዋ ሲደርስ ምን ተሰምቷት ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት ማወቅ አንችልም። የእስራኤል አምላክ፣ በባርነት ቀንበር ሥር የነበረውን ሕዝቡን እየመራ በወቅቱ በዓለም ላይ ኃያል በነበረው የግብፅ ሠራዊት ላይ ድል እንደተጎናጸፈ ሰምታለች። አሁን ደግሞ እስራኤላውያን በኢያሪኮ ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ ተዘጋጅተዋል! እንደዚያም ሆኖ የኢያሪኮ ነዋሪዎች ከክፋት ድርጊታቸው አልተመለሱም። ከዚህ አንጻር መጽሐፍ ቅዱስ፣ የረዓብ ወገኖች ስለሆኑት ከነዓናውያን ሲናገር ‘ታዛዥ ሳይሆኑ የቀሩት’ የሚለው ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም።—ዕብራውያን 11:31

ረዓብ ግን ከአገሯ ሰዎች የተለየች ነች። ስለ እስራኤላውያንና ይሖዋ ስለሚባለው አምላካቸው ባለፉት ዓመታት በሰማችው ነገር ላይ አሰላስላበት መሆን አለበት። ይሖዋ ከከነዓናውያን አማልክት ምንኛ የተለየ ነው! ይሖዋ፣ ሕዝቡን ከመጨቆን ይልቅ የተዋጋላቸው እንዲሁም አምላኪዎቹ እንዲረክሱ ከማድረግ ይልቅ የላቀ የሥነ ምግባር አቋም እንዲኖራቸው የሚፈልግ አምላክ ነው። ይህ አምላክ፣ ሴቶች የወንዶችን የፆታ ፍላጎት ለማርካት የተፈጠሩና ለዚህ ዓላማ እንደ ሸቀጥ ሊለወጡ የሚችሉ እንዲሁም ጸያፍ በሆኑ የአምልኮ ሥርዓቶች ላይ ወራዳ በሆነ ድርጊት ከመካፈል ሌላ ሚና የሌላቸው እንደሆኑ አድርጎ አይመለከታቸውም፤ ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ሴቶችን የሚይዘው በክብር ነው። ረዓብ፣ እስራኤላውያን ከዮርዳኖስ ማዶ መስፈራቸውንና በኢያሪኮ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር መዘጋጀታቸውን ስትሰማ በሕዝቧ ላይ የሚመጣውን ጥፋት በማሰብ አዝና መሆን አለበት። ይሖዋ የረዓብን ሁኔታ አስተውሎ እንዲሁም በልቧ ያለውን መልካም ነገር ተመልክቶት ይሆን?

በዛሬው ጊዜ፣ እንደ ረዓብ ያሉ ብዙ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎችም ክብርን ዝቅ ከሚያደርግና ደስታን ከሚያሳጣ ሕይወታቸው ማምለጥ እንደማይችሉ ያስባሉ፤ ማንም በቁም ነገር እንደማያያቸውና ዋጋ ቢስ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። የረዓብ ታሪክ ይሖዋ፣ ማንኛችንንም ቢሆን የእሱን ትኩረት ለማግኘት እንደማንበቃ አድርጎ እንደማይመለከተን ያስታውሰናል፤ ይህ በጣም የሚያጽናና ነው። የቱንም ያህል ራሳችንን ዝቅ አድርገን ብንመለከት ይሖዋ “ከእያንዳንዳችን የራቀ . . . አይደለም።” (የሐዋርያት ሥራ 17:27) እሱ ለእኛ ቅርብ ነው፤ እንዲሁም በእሱ ላይ እምነት ለሚያሳድሩ ሁሉ ምንጊዜም ተስፋ የሚሰጥ አምላክ ነው። ታዲያ ረዓብ በእሱ ላይ እምነት ነበራት?

ሰላዮቹን ተቀብላለች

እስራኤላውያን ኢያሪኮን መዞር ከመጀመራቸው ከተወሰነ ጊዜ በፊት ሁለት እንግዶች ወደ ረዓብ ቤት መጡ። ሁለቱ ሰዎች ማንም ልብ ሳይላቸው ገብተው ለመውጣት አስበው ነበር፤ ይሁን እንጂ ከተማይቱ ስለተሸበረች ብዙ ሰዎች፣ በመካከላቸው የእስራኤል ሰላዮች እንዳይኖሩ በንቃት ይጠባበቁ ነበር። ረዓብም አስተዋይ ስለሆነች የእንግዶቹን ማንነት ሳትጠረጥር አልቀረችም። እርግጥ ነው፣ እንግዶች ወደ ቤቷ መምጣታቸው አዲስ  ነገር አይደለም፤ እነዚህ ሰዎች ግን የፈለጉት ማደሪያ ማግኘት እንጂ ከእሷ ጋር መተኛት አልነበረም።

ሁለቱ ሰዎች ከእስራኤል ሰፈር የመጡ ሰላዮች ናቸው። አዛዣቸው ኢያሱ የላካቸው የኢያሪኮን ጠንካራና ደካማ ጎን አጣርተው እንዲመጡ ነው። ኢያሪኮ፣ የእስራኤል ወረራ ከተደገሰላቸው የከነዓን ከተሞች የመጀመሪያዋና ምናልባትም ከሁሉም ኃያሏ ነች። ኢያሱ፣ እሱና ሕዝቡ ምን እንደሚጠብቃቸው ማወቅ ፈልጎ ነበር። ሰላዮቹ ወደ ረዓብ ቤት የገቡት አስበውበት እንደሆነ ጥርጥር የለውም። እንግዶች፣ ከየትኛውም ስፍራ ይልቅ ወደ ጋለሞታ ቤት ቢገቡ ማንም ልብ አይላቸው ይሆናል። በተጨማሪም ሰላዮቹ፣ እዚያ የሚመጡ ሰዎች ከሚያወሩት ነገር መሃል ጠቃሚ መረጃ ሊያገኙ እንደሚችሉ ተስፋ አድርገው ሊሆን ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ረዓብ “መልእክተኞቹን በጥሩ ሁኔታ ተቀብላ [አስተናገደቻቸው]” በማለት ይናገራል። (ያዕቆብ 2:25) እነማን እንደሆኑና ለምን እንደመጡ ጥርጣሬ አድሮባት ሊሆን ቢችልም ወደ ቤቷ እንዲገቡና በዚያ እንዲያድሩ ፈቅዳላቸዋለች። ምናልባትም ስለ አምላካቸው ስለ ይሖዋ የበለጠ ለማወቅ ተስፋ አድርጋ ይሆናል።

ይሁንና ከኢያሪኮ ንጉሥ የተላኩ መልእክተኞች በድንገት ወደ ቤቷ መጡ! ከእስራኤል የተላኩ ሰላዮች ወደ ረዓብ ቤት እንደገቡ የሚገልጽ ወሬ ተናፍሷል። ታዲያ ረዓብ ምን ታደርግ ይሆን? ሁለቱን እንግዶች ብትደብቃቸው ራሷንም ሆነ መላ ቤተሰቧን ለአደጋ ማጋለጥ አይሆንባትም? እንዲህ ያሉትን ጠላቶች አስጠግታ ብትገኝ የኢያሪኮ ሕዝብ፣ ከነመላው ቤተሰቧ አይፈጃትም? በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሁኔታ መፈጠሩ ረዓብ ስለ እንግዶቹ ማንነት እርግጠኛ እንድትሆን አደረጋት። ይሖዋ ከራሷ አማልክት እጅግ የተሻለ አምላክ እንደሆነ ካወቀች ከእሱ ጎን ለመቆም የሚያስችል ከዚህ የተሻለ አጋጣሚ ይኖራል?

ረዓብ ለማሰብ ጊዜ ባይኖራትም ዘዴኛ በመሆኗ አፋጣኝ እርምጃ ወሰደች። በቤቷ ሰገነት ላይ አውጥታ በረበረበችው የተልባ እግር ውስጥ ሰላዮቹን ደበቀቻቸው። ከዚያም ለንጉሡ መልእክተኞች እንደሚከተለው በማለት ተናገረች፦ “በእርግጥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጥተዋል፤ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጡ አላውቅም። ጨልሞ የቅጥሩ በር ከመዘጋቱ በፊት ወጥተው ሄደዋል፤ በየት በኩል እንደሄዱ ግን እኔ አላውቅም፤ ልትደርሱባቸው ትችላላችሁና ፈጥናችሁ ተከታተሏቸው።” (ኢያሱ 2:4, 5) ረዓብ፣ ለንጉሡ መልእክተኞች ይህን ስትናገር ዓይን ዓይናቸውን እያየች ሊሆን እንደሚችል ማሰብ እንችላለን። በድንጋጤ የሚደልቀው ልቧ እውነቱን እንዳያሳብቅባት ሰግታ ይሆን?

ረዓብ፣ ከረበረበችው የተልባ እግር ሥር ሁለቱን የይሖዋ አገልጋዮች ደበቀቻቸው፤ ይህን ያደረገችው ሕይወቷን አደጋ ላይ ጥላ ነው

ደግነቱ፣ ብልሃቷ ሠራ! የንጉሡ መልእክተኞች፣ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መሻገሪያ የሚወስደውን መንገድ ይዘው እየተቻኮሉ ሄዱ። (ኢያሱ 2:7) በዚህ ጊዜ ረዓብ እፎይ ብላ መሆን አለበት። ቀላል ዘዴ በመጠቀም፣ እውነቱን ማወቅ የማይገባቸውን እነዚህን ነፍሰ ገዳዮች በተሳሳተ አቅጣጫ የመራቻቸው ሲሆን የይሖዋን አገልጋዮች ሕይወት አትርፋለች።

ረዓብ በፍጥነት ወደ ሰገነቱ ተመልሳ በመሄድ ያደረገችውን ሁሉ ለሁለቱ ሰላዮች ነገረቻቸው። በተጨማሪም አንድ ጠቃሚ መረጃ ሰጠቻቸው፤ የኢያሪኮ ሕዝብ ልቡ እንደቀለጠና ወራሪዎቹን እስራኤላውያን ፈርቶ እንደተሸበረ ገለጸችላቸው። ይህ ዜና  ሰላዮቹን አስደስቷቸው መሆን አለበት። እነዚያ ክፉ ከነዓናውያን የእስራኤል አምላክ የሆነውን ኃያሉን ይሖዋን ፈርተው ተብረክርከዋል! ረዓብ ቀጥሎ የተናገረችው ሐሳብ ደግሞ ይበልጥ ትኩረታችንን የሚስብ ነው። “እግዚአብሔር አምላካችሁ በላይም በሰማይ፣ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነው” አለች። (ኢያሱ 2:11) ስለ ይሖዋ የሰማችው ነገር፣ የእስራኤል አምላክ እምነቷን ልትጥልበት የምትችል አምላክ እንደሆነ እንድትተማመን የሚያደርግ ነው። በመሆኑም በይሖዋ ላይ እምነት ጥላለች።

ረዓብ፣ ይሖዋ ሕዝቡን ድል የሚያጎናጽፍ አምላክ ስለ መሆኑ ጨርሶ አልተጠራጠረችም። በመሆኑም እስራኤላውያን፣ ለእሷና ለቤተሰቧ ምሕረት በማድረግ ከጥፋቱ እንዲያተርፏቸው ሰላዮቹን ተማጸነች። ሰላዮቹም ጥያቄዋን ተቀበሉ፤ ሚስጥራቸውን ከጠበቀችና በከተማዋ ቅጥር ላይ በሚገኘው በቤቷ መስኮት ላይ ቀይ ገመድ ካንጠለጠለች ኢያሪኮ በምትጠፋበት ጊዜ እስራኤላውያን ወታደሮች እሷንና ቤተሰቧን እንደሚያድኗቸው ነገሯት።—ኢያሱ 2:12-14, 18

እምነትን በተመለከተ ከረዓብ ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው “እምነት የሚገኘው ቃሉን ከመስማት ነው።” (ሮም 10:17) ረዓብ፣ ስለ ይሖዋ አምላክ ኃይልና ፍትሕ የሰማችው ትክክለኛ ዘገባ በእሱ እንድትተማመን አድርጓታል። በዛሬው ጊዜ ስለ ይሖዋ ብዙ የማወቅ አጋጣሚ አለን። ታዲያ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ፣ ስለ እሱ ለማወቅ እንዲሁም በእሱ ላይ እምነት ለማሳደር ጥረት እናደርጋለን?

አንድ ግዙፍ ቅጥር ፈረሰ

ሁለቱ ሰላዮች የረዓብን ምክር በመከተል በመስኮቷ ላይ በተንጠለጠለ ገመድ አማካኝነት ወደ ታች ወረዱና ወደ ተራሮቹ ሄደው ተሸሸጉ። ከኢያሪኮ በስተ ሰሜን በሚገኙት ተራሮች ላይ ሰላዮቹ ሊደበቁባቸው የሚችሉ ብዙ ዋሻዎች ነበሩ፤ በመሆኑም ሰላዮቹ ሁኔታዎች እስኪረጋጉ ድረስ በእነዚህ ዋሻዎች ውስጥ ለጥቂት ቀናት ከተሸሸጉ በኋላ ከረዓብ ያገኙትን ምሥራች ይዘው ወደ እስራኤላውያን ሰፈር ተመለሱ።

ረዓብ በእስራኤላውያን አምላክ ላይ እምነት እንዳላት አሳይታለች

ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይሖዋ የዮርዳኖስ ወንዝ መፍሰሱን እንዲያቆም በማድረግ እስራኤላውያንን በደረቅ መሬት ላይ አሻገራቸው፤ የኢያሪኮ ሕዝብ ይህን ሲሰማ በፍርሃት እንደራደ ጥርጥር የለውም። (ኢያሱ 3:14-17) ለረዓብ ግን ይህ ዜና፣ በይሖዋ ላይ እምነት መጣሏ ተገቢ መሆኑን የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።

ከዚያም እስራኤላውያን ኢያሪኮን በቀን አንድ ጊዜ መዞር ጀመሩ፤ በዚህ ሁኔታ ከተማዋን ለስድስት ቀናት ዞሯት። በሰባተኛው ቀን ደግሞ ከሌሎቹ ቀናት የተለየ ነገር አደረጉ። በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ እንደተጠቀሰው ገና ጎህ ሲቀድ ከተማዋን መዞር ጀመሩ፤ ሆኖም እንደ ሌሎቹ ቀናት አንድ ጊዜ ዞረው አላበቁም፤ ከተማዋን ደጋግመው መዞራቸውን ቀጠሉ። (ኢያሱ 6:15) እስራኤላውያን ምን እያደረጉ ነው?

ከተማዋን ሰባት ጊዜ ከዞሩ በኋላ በመጨረሻ ቀጥ ብለው ቆሙ። የመለከቱም ድምፅ ጠፋ። አካባቢው ፀጥ ረጭ አለ። የከተማዋ ነዋሪዎች ብርክ ያዛቸው። ከዚያም ኢያሱ ምልክት ሲሰጥ የእስራኤል ሠራዊት ድምፁን ከፍ አድርጎ ታላቅ ጩኸት ጮኸ፤ የኢያሪኮ ሰዎች የሠራዊቱን ድምፅ ሲሰሙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በመሆኑም በግንቡ አናት ላይ ያሉት ዘቦች፣ እስራኤላውያን ጥቃት የሚሰነዝሩት በዚህ እንግዳ የሆነ ዘዴ እንደሆነ ተሰምቷቸው ይሆን? ከሆነ እንደተሳሳቱ ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደባቸውም። ብዙም ሳይቆይ ግዙፉ ግንብ ሲነቃነቅ ተሰማቸው። ግንቡ መናጋትና መሰንጠቅ ጀመረ፤ ከዚያም ግንድስ ብሎ ወደቀ! ፍርስራሹ የፈጠረው አቧራ እየቀለለ ሲሄድ ሳይፈርስ የቀረ የቅጥሩ ክፍል እንዳለ ግልጽ ሆነ። ያልፈረሰው፣ የረዓብ ቤት ብቻ ነበር፤ ይህም፣ ላሳየችው እምነት ምሥክር ነው! ረዓብ፣ ይሖዋ እንዴት ጥበቃ እንዳደረገላት ስትመለከት ምን ተሰምቷት ሊሆን እንደሚችል አስበው! * ቤተሰቧ ከጥፋት ተርፏል!—ኢያሱ 6:10, 16, 20, 21

የይሖዋ ሕዝቦችም በተመሳሳይ ረዓብን ባሳየችው እምነት አክብረዋታል። ከፍርስራሽ ክምሩ መካከል አንድ ቤት እንደ ሐውልት ብቻውን ቆሞ ሲያዩ ይሖዋ ከዚህች ሴት ጋር እንደሆነ አወቁ። እሷና ቤተሰቧ በዚህች ክፉ ከተማ ላይ ከመጣው ጥፋት ተረፉ። ከጦርነቱ በኋላ ረዓብ፣ በእስራኤላውያን ሰፈር አቅራቢያ እንድትኖር ተፈቀደላት። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ከአይሁድ ሕዝብ ጋር ተቀላቀለች። ሰልሞን የሚባል ሰው አገባች። ልጃቸው ቦዔዝ አስደናቂ እምነት ያለው ሰው በመሆኑ ይታወቃል። እሱም ሞዓባዊቷን ሩትን አገባ። * (ሩት 4:13, 22) ንጉሥ ዳዊትና በኋላም መሲሑ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጡት ታላቅ እምነት ካለው ከዚህ ቤተሰብ ነው።—ኢያሱ 6:22-25፤ ማቴዎስ 1:5, 6, 16

የረዓብ ታሪክ፣ ይሖዋ ለሁሉም ሰው ትኩረት እንደሚሰጥ ያሳያል። ሁሉንም ሰው የሚያይ ሲሆን ልባችንንም ያነባል፤ እንዲሁም ልክ እንደ ረዓብ በልባችን ውስጥ ቅንጣት ታክል እምነት እንዳለ ሲመለከት ይደሰታል። የረዓብ እምነት ለተግባር አነሳስቷታል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ‘በሥራ ጻድቅ ተብላ ተጠርታለች።’ (ያዕቆብ 2:25) እሷን በእምነቷ መምሰላችን ምንኛ ጥበብ ነው!

^ አን.27 ይሖዋ፣ ሁለቱ ሰላዮች ከረዓብ ጋር ያደረጉትን ስምምነት ማክበሩ ትኩረት የሚስብ ነው።

^ አን.28 ስለ ሩትና ቦዔዝ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት በሐምሌ 1 እና በጥቅምት 1, 2012 የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ “በእምነታቸው ምሰሏቸው” በሚለው ዓምድ ሥር የወጡትን ርዕሶች ተመልከት።