ይሖዋ፣ አምላኪዎቹ እሱን ለማስደሰት የሚያደርጉትን ጥረት ያደንቃል? አንዳንዶች እንደሚያደንቅ አይሰማቸውም፤ እነዚህ ሰዎች፣ አምላክ ስለ እኛ ምንም ደንታ እንደሌለው ይናገራሉ። ይሁንና እንዲህ ዓይነት አስተያየት የሚሰነዝሩ ሰዎች ስለ አምላክ ያላቸው አመለካከት በጣም የተሳሳተ ነው። ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ፣ በዚህ ረገድ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። ይሖዋ፣ በእምነት የሚያገለግሉትን ሰዎች ጥረት እንደሚያደንቅ ያረጋግጥልናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን 11:6 ላይ ምን እንዳለ እስቲ እንመልከት።

ይሖዋን ለማስደሰት ምን ማድረግ አለብን? ጳውሎስ “ያለ እምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም” በማለት ጽፏል። ጳውሎስ፣ ‘ያለ እምነት አምላክን ማስደሰት አስቸጋሪ ነው’ እንዳላለ ልብ በል። ከዚህ ይልቅ ሐዋርያው የተናገረው ያለ እምነት አምላክን ማስደሰት እንደማይቻል ነው። በሌላ አነጋገር፣ አምላክን ለማስደሰት እምነት በጣም ወሳኝ ነገር ነው።

ይሖዋን የሚያስደስተው ምን ዓይነት እምነት ነው? በአምላክ ላይ ያለን እምነት ሁለት ነገሮችን ያካተተ መሆን አለበት። አንደኛ፣ ‘እሱ መኖሩን ማመን አለብን።’ አምላክ መኖሩን የምንጠራጠር ከሆነ እሱን እንዴት ልናስደስተው እንችላለን? ይሁን እንጂ አጋንንትም እንኳ ይሖዋ መኖሩን ያምናሉ፤ በመሆኑም ትክክለኛ እምነት ካለን ከዚህ የበለጠ ነገር ይጠበቅብናል። (ያዕቆብ 2:19) አምላክ እውን እንደሆነ ያለን እምነት ለተግባር ሊያንቀሳቅሰን ይኸውም አኗኗራችን እሱን የሚያስደስት እንዲሆን በማድረግ እምነታችንን በተግባር እንድናሳይ ሊያነሳሳን ይገባል።—ያዕቆብ 2:20, 26

ሁለተኛ፣ አምላክ “ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን [ይኖርብናል]።” እውነተኛ እምነት ያለው ሰው፣ አምላክን በሚያስደስት መንገድ ለመኖር የሚያደርገው ጥረት ከንቱ ሆኖ እንደማይቀር ፈጽሞ አይጠራጠርም። (1 ቆሮንቶስ 15:58) ይሖዋ ለእኛ ወሮታ ለመክፈል ችሎታው ወይም ፍላጎቱ ያለው መሆኑን የምንጠራጠር ከሆነ እሱን እንዴት ልናስደስተው እንችላለን? (ያዕቆብ 1:17፤ 1 ጴጥሮስ 5:7) አምላክ ስለ እኛ እንደማያስብ፣ የምናደርገውን ጥረት እንደማያደንቅ እንዲሁም ለጋስ እንዳልሆነ የሚያስብ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን አምላክ አያውቀውም።

ይሖዋ ወሮታ የሚከፍለው ለእነማን ነው? “ከልብ ለሚፈልጉት” እንደሆነ ጳውሎስ ተናግሯል። ለመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የተዘጋጀ አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው “ከልብ ለሚፈልጉት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ስለ አምላክ ለማወቅ ጥረት ማድረግን ብቻ ሳይሆን እሱን ለማምለክ የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድንም ያመለክታል። አንድ ሌላ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ደግሞ ይህ የግሪክኛ ግስ የገባበት መንገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግን እንደሚያመለክት ይገልጻል። አዎን፣ ይሖዋ በእሱ ላይ እምነት ለሚያሳድሩና በዚህም የተነሳ ከልብ በመነጨ ፍቅር እና ቅንዓት ተነሳስተው ለሚያገለግሉት ሰዎች ወሮታ ይከፍላል።—ማቴዎስ 22:37

ይሖዋ ለእኛ ወሮታ ለመክፈል ችሎታው ወይም ፍላጎቱ ያለው መሆኑን የምንጠራጠር ከሆነ እሱን እንዴት ልናስደስተው እንችላለን?

ታዲያ ይሖዋ፣ በእምነት ተነሳስተው ለሚያገለግሉት ሰዎች ወሮታ የሚከፍላቸው እንዴት ነው? ወደፊት፣ በዋጋ ሊተመን የማይችል ውድ የሆነ ሽልማት ይኸውም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ሊሰጣቸው ቃል ገብቷል፤ ይህም ልግስናውና ፍቅሩ ታላቅ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። (ራእይ 21:3, 4) ይሖዋን ከልብ የሚፈልጉ ሰዎች አሁንም እንኳ የተትረፈረፈ በረከት ያገኛሉ። ቅዱስ መንፈሱ የሚሰጣቸው እርዳታ እንዲሁም በቃሉ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ አስደሳችና አርኪ ሕይወት እንዲመሩ ያስችላቸዋል።—መዝሙር 144:15፤ ማቴዎስ 5:3

በእርግጥም ይሖዋ፣ አምላኪዎቹ በእምነት ተነሳስተው ለሚያቀርቡት አገልግሎት ከፍ ያለ ዋጋ የሚሰጥ አድናቂ አምላክ ነው። ይህን ማወቅህ ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ ያነሳሳሃል? ከሆነ ይሖዋን የሚያስደስተው ዓይነት እምነት ማዳበርና እምነትህን በተግባር ማሳየት ስለምትችልበት መንገድ የበለጠ ለማወቅ ለምን ጥረት አታደርግም? እንዲህ ዓይነት እምነት ስታዳብር ይሖዋ ወሮታህን አትረፍርፎ ይከፍልሃል።

በኅዳር ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል

ከቲቶ 1-3; ፊልሞና 1-25; ዕብራውያን 1-13ያዕቆብ 1-5