“‘አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።’ ይህ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው።”ኢየሱስ ክርስቶስ፣ 33 ዓ.ም. *

አንዳንዶች አምላክን መውደድ ከባድ ይሆንባቸዋል። እነዚህ ሰዎች፣ አምላክ ሚስጥራዊና ሊቀረብ የማይችል አልፎ ተርፎም ጨካኝ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ቀጥሎ የቀረቡትን አስተያየቶች ተመልከት፦

  • “አምላክ እንዲረዳኝ ብጸልይም ለእኔ ቅርብ እንደሆነና እንደሚያስብልኝ አይሰማኝም ነበር። አምላክን የምመለከተው እንደ አንድ አካል ሳይሆን ስሜት እንደሌለው ነገር አድርጌ ነበር።”—ማርኮ፣ ጣሊያን

  • “አምላክን ለማገልገል ከልቤ ብፈልግም ልቀርበው እንደምችል አልተሰማኝም። አምላክ እኛን ለመቅጣት የተቀመጠ ጨካኝ አካል እንደሆነ አስብ ነበር። አፍቃሪና አሳቢ እንደሆነ ተሰምቶኝ አያውቅም ነበር።”—ሮዛ፣ ጓቲማላ

  • “ልጅ ሳለሁ አምላክ ስህተቶቻችንን እንደሚፈላልግና አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው እኛን ለመቅጣት ተዘጋጅቶ እንደሚጠብቀን አምን ነበር። እያደር ደግሞ አምላክ፣ የማይቀረብ እንደሆነ አድርጌ ማሰብ ጀመርኩ። ስለ አምላክ ሳስብ፣ ሕዝቡን ቢያስተዳድርም ለእነሱ ምንም ግድ እንደሌለው ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሆነ ይሰማኝ ነበር።”—ሬይሞንድ፣ ካናዳ

አንተስ ምን ይመስልሃል? አምላክን መውደድ ከባድ ነው? ክርስቲያኖች፣ ለብዙ ዘመናት ይህን ጥያቄ ሲጠይቁ ኖረዋል። እንዲያውም በመካከለኛው ዘመን፣ የሕዝበ ክርስትና እምነት ተከታይ በሆኑ አገሮች ውስጥ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ሁሉን ቻይ ወደሆነው አምላክ ጸሎት እንኳ አያቀርቡም ነበር። ለምን? በጣም ይፈሩት ስለነበረ ነው። የታሪክ ምሁር የሆኑት ዊል ዱራንት ጉዳዩን እንደሚከተለው በማለት ገልጸውታል፦ “አንድ ኃጢአተኛ ሰው፣ እጅግ አስፈሪ ወደሆነውና ወደማይቀረበው አምላክ ለመጸለይ እንዴት ሊደፍር ይችላል?”

ለመሆኑ ሰዎች፣ አምላክን ‘እጅግ አስፈሪና የማይቀረብ’ እንደሆነ አድርገው እንዲያዩት ያደረጋቸው ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ምን ያስተምራል? ስለ አምላክ እውነቱን መማር እሱን እንድትወደው ሊያነሳሳህ ይችላል?