በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ጥቅምት 2013

 ወደ አምላክ ቅረብ

‘ይሖዋ በነፃ ይቅር ብሏችኋል’

‘ይሖዋ በነፃ ይቅር ብሏችኋል’

“ሌሎችን ይቅር የማይል ሰው፣ ራሱ የሚሻገርበትን ድልድይ የሚያፈርስ ያህል ነው።” በ17ኛው መቶ ዘመን የኖሩት ኤድዋርድ ኸርበርት የተባሉ ብሪታንያዊ የታሪክ ምሁር የተናገሩት ይህ ሐሳብ፣ ሌሎችን ይቅር እንድንል ከሚያነሳሱን ምክንያቶች አንዱን ያጎላል፤ ይኸውም ይዋል ይደር እንጂ እኛም ይቅር እንዲሉን ሌሎችን መጠየቅ ሊያስፈልገን ይችላል። (ማቴዎስ 7:12) ይሁን እንጂ ይቅር ባይ እንድንሆን የሚያነሳሳን ከዚህ ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ምክንያት አለ። በቆላስይስ 3:13 ላይ የሚገኘውን ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረውን ሐሳብ ልብ በል።—ጥቅሱን አንብብ።

ሁላችንም ፍጹማን ባለመሆናችን አንዳንድ ጊዜ ሌሎችን ልናበሳጭ ወይም ልናስቀይም እንችላለን፤ እነሱም እንዲሁ ሊያደርጉን ይችላሉ። (ሮም 3:23) ታዲያ እንደ እኛው ፍጽምና ከጎደላቸው ሰዎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ መሪነት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ቻዮችና ይቅር ባዮች እንድንሆን መክሮናል። ይህ ምክር የተጻፈው ከሁለት ሺህ ዓመት ገደማ በፊት ቢሆንም ዛሬም ጠቃሚ ነው። እስቲ ጳውሎስ የሰጠውን ምክር እንመርምር።

“እርስ በርስ መቻቻላችሁን . . . ቀጥሉ።” ‘መቻቻላችሁን ቀጥሉ’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ሆደ ሰፊ ወይም ታጋሽ መሆንን ያመለክታል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው ክርስቲያኖች፣ “የአንዳንዶች ድክመት ወይም ደስ የማይል ባሕርይ ቢያበሳጫቸውም እነዚህን ሰዎች ለመታገሥ ፈቃደኛ በመሆን” ይህን ባሕርይ ያሳያሉ። “እርስ በርስ” የሚሉት ቃላት እንዲህ ዓይነቱ መቻቻል ከሁለቱም ወገኖች የሚጠበቅ ነገር እንደሆነ ይጠቁማሉ። በሌላ አባባል፣ እኛም ሌሎችን ሊያበሳጩ የሚችሉ ባሕርያት እንዳሉን የምናስታውስ ከሆነ ሌሎች ደስ የማይለን ነገር ቢያደርጉም ይህ ሁኔታ በመካከላችን ያለውን ሰላም እንዲያደፈርሰው አንፈቅድም። ይሁን እንጂ ሌሎች ቢበድሉንስ?

“እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።” አንድ ምሁር እንደገለጹት፣ ‘በነፃ ይቅር ማለት’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ምሕረትን ወይም ይቅርታን ለመግለጽ የሚያገለግለው . . . የተለመደ ቃል ሳይሆን በቸርነት የሚደረግን ይቅርታ የሚያጎላ ጠለቅ ያለ ትርጉም ያለው ቃል ነው።” አንድ ሌላ ጽሑፍ ደግሞ ይህ ቃል “ሌሎችን የሚያስደስት ነገር ማድረግን፣ ውለታ መዋልን፣ ደግነት ማሳየትን” ሊያመለክት እንደሚችል ይገልጻል። እኛም ‘በሌላው ላይ ቅር የተሰኘንበት ነገር’ በሚኖረን ጊዜም ጭምር በፈቃደኝነት ይቅር በማለት ቸርነት እናሳያለን። ይሁንና እንዲህ ዓይነቱን ውለታ ለመዋል ፈቃደኛ መሆን የሚኖርብን ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት፣ እኛም የበደለንን ግለሰብ ልንበድለው የምንችል መሆኑ ነው፤ በዚህ ጊዜ እኛን ይቅር በማለት ውለታውን እንዲመልስልን እንፈልግ ይሆናል።

“ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።” ሌሎችን በነፃ ይቅር እንድንል የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ይሖዋ እኛን በነፃ ይቅር የሚለን መሆኑ ነው። (ሚክያስ 7:18) ይሖዋ ንስሐ ለገቡ ኃጢአተኞች የሚውልላቸውን ታላቅ ውለታ እስቲ ለአንድ አፍታ አስበው። ከእኛ በተለየ መልኩ ይሖዋ ኃጢአት አይሠራም። ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን በፈቃደኝነትና ሙሉ በሙሉ ይቅር የሚላቸው የእነዚህ ሰዎች ይቅርታ እንደማያስፈልገውና ውለታውን ፈጽሞ መመለስ እንደማይችሉ እያወቀ ነው። እውነትም ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን በነፃ ይቅር በማለት ረገድ ተወዳዳሪ የለውም!

ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን በነፃ ይቅር በማለት ረገድ ተወዳዳሪ የለውም!

የይሖዋ ምሕረት፣ ወደ እሱ እንድንቀርብና እሱን እንድንመስለው ያነሳሳናል። (ኤፌሶን 4:32 እስከ 5:1) እንግዲያውስ ራሳችንን እንዲህ ብለን ብንጠይቅ መልካም ነው፦ ‘ይሖዋ በልግስና ይቅር እያለኝ እኔ፣ ላደረሰብኝ በደል ከልቡ የተጸጸተን እንደ እኔው ያለ ኃጢአተኛ ሰው ይቅር ማለት እንዴት ይከብደኛል?’—ሉቃስ 17:3, 4