በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ጥቅምት 2013

ቀለማት ተጽዕኖ የሚያሳድሩብህ እንዴት ነው?

ቀለማት ተጽዕኖ የሚያሳድሩብህ እንዴት ነው?

በዙሪያችን ያሉትን ነገሮች በምንመለከትበት ጊዜ ዓይናችንና አንጎላችን አንድ ላይ ተቀናጅተው መረጃ ለመሰብሰብ ይረዱናል። አንድ ፍሬ ከተመለከትህ በኋላ ፍሬውን ለመብላት ወይም ላለመብላት ትወስናለህ። ሰማዩን ታይና ዛሬ እንደማይዘንብ ትደመድማለህ። አሁን እያነበብካቸው ያሉትን ቃላት በመመልከት ትርጉማቸውን ትረዳለህ። እነዚህን ሁሉ ነገሮች ስታደርግ ቀለማት ተጽዕኖ እያሳደሩብህ ነው። እንዴት?

አንድ ፍሬ ስታይ ቀለሙን በመመልከት ፍሬው መብሰሉንና ጣፋጭ መሆኑን ትለያለህ። የሰማዩ ቀለምና ደመናው ደግሞ የአየሩን ሁኔታ እንድታውቅ ይረዳሃል። በዚህ ርዕስ ላይ የጽሑፉና የወረቀቱ ቀለም በጣም የሚለያይ መሆኑ በቀላሉ ለማንበብ አስችሎሃል። በእርግጥም፣ አስበኸው ባይሆንም እንኳ በዙሪያህ ስላሉ ነገሮች የምታገኘውን መረጃ የምትረዳው ቀለሞችን መሠረት በማድረግ ነው። ይሁን እንጂ ቀለም በስሜትህም ላይ ተጽዕኖ አለው።

ቀለማት በስሜታችን ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ

በአንድ የገበያ ማዕከል ውስጥ ስትዘዋወር ዓይን በሚማርክ መንገድ የታሸጉ ሸቀጦችን ትመለከታለህ። የንግድ ማስታወቂያ አዘጋጆች የሰዎችን ፍላጎት፣ ፆታ እንዲሁም ዕድሜ ከግምት በማስገባት እነዚህን ሰዎች የሚማርኩ የተለያዩ ቀለማትንና የቀለም ቅንጅቶችን በጥንቃቄ እንደሚመርጡ አስተውለህ ይሆናል። ቤት የሚያስጌጡ እንዲሁም የልብስ ዲዛይን የሚያወጡ ሰዎች እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም ቀለማት በሰዎች ስሜት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያደርጉ ያውቃሉ።

ሰዎች በአካባቢያቸው ያለውን ባሕልና ልማድ መሠረት በማድረግ ለቀለማት የተለያየ ትርጉም ይሰጣሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በእስያ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ቀይ ቀለምን ከጥሩ ዕድልና ከደስታ ጋር ሲያዛምዱት በአንዳንድ የአፍሪካ ክፍሎች ደግሞ ቀይ የሐዘን ቀለም ነው። ይሁን እንጂ ሰዎች ያደጉበት አካባቢና ባሕላቸው ምንም ሆነ ምን፣ አንዳንድ ቀለማት በስሜታቸው ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ተመሳሳይ ነው። እስቲ ሦስት ቀለማትን እንደ ምሳሌ እንውሰድና በስሜትህ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ እንመልከት።

ቀይ ዓይን ውስጥ ቶሎ የሚገባ ቀለም ነው። ቀይ ቀለም ብዙውን ጊዜ ከኃይል፣ ከጦርነትና ከአደጋ ጋር ይያያዛል። ቀይ፣ ኃይለኛ ስሜት የሚያሳድር ቀለም ነው፤ ሰውነታችን ምግብን ወደ ኃይል የሚቀይርበትን ሂደት ሊያፋጥን እንዲሁም የአተነፋፈስ ፍጥነትና የደም ግፊት እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት “ቀይ” የሚለው ቃል በዕብራይስጡ “ደም” የሚል ትርጉም ካለው ቃል የመጣ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ “አምላክን በሚሰድቡ ስሞች በተሞላ . . . ደማቅ ቀይ አውሬ ላይ” ስለተቀመጠችና ሐምራዊና ደማቅ ቀይ ልብስ ስለለበሰች አንዲት ነፍሰ ገዳይ ጋለሞታ ይናገራል፤ በዚህ ዘገባ ላይ እነዚህ ቀለማት መጠቀሳቸው በአእምሯችን ውስጥ የማይረሳ ምስል እንዲፈጠር ያደርጋል።—ራእይ 17:1-6

አረንጓዴ ከቀይ ቀለም ተቃራኒ የሆነ ስሜት ይፈጥራል፤ ሰውነታችን ምግብን ወደ ኃይል የሚቀይርበት ሂደት ዝግ እንዲል የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ የመረጋጋት ስሜት ይፈጥራል። አረንጓዴ፣ እረፍት የሚሰጥ ቀለም ሲሆን ብዙውን ጊዜ ከመረጋጋት ጋር ይያያዛል። አረንጓዴ የሆኑ የአትክልት ቦታዎችንና ኮረብቶችን ስናይ መንፈሳችን ዘና ይላል። የዘፍጥረት ዘገባ፣ አምላክ ለሰው ልጆች ለምለም ወይም አረንጓዴ የሆኑ ዕፅዋትንና ተክሎችን እንደሰጣቸው ይናገራል።—ዘፍጥረት 1:11, 12, 30

ነጭ ብዙውን ጊዜ ከብርሃን፣ ከሰላምና ከንጽሕና ጋር ይዛመዳል። በተጨማሪም ከጥሩነት፣ ከየዋህነትና ልበ ንጹሕ ከመሆን ጋር ይያያዛል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ የተጠቀሰው ቀለም ነጭ ነው። በራእይ የታዩ አንዳንድ ሰዎችና መላእክት ነጭ የለበሱ ሲሆን ይህም ጽድቅንና መንፈሳዊ ንጽሕናን  ይጠቁማል። (ዮሐንስ 20:12፤ ራእይ 3:4፤ 7:9, 13, 14) ነጭና ንጹሕ በፍታ የለበሱ ጋላቢዎች የተቀመጡባቸው ነጭ ፈረሶችም የጽድቅ ጦርነት ምሳሌዎች ናቸው። (ራእይ 19:14) አምላክ ኃጢአትን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆኑን ጎላ አድርጎ ሲገልጽ ነጭ ቀለምን ተጠቅሟል፤ “ኀጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል፤ እንደ ደም ቢቀላም እንደ ባዘቶ ነጭ ይሆናል” ብሏል።—ኢሳይያስ 1:18

ቀለማት በማስታወስ ረገድ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈሩ ስለ ቀለማት የሚገልጹ ሐሳቦች እንደሚያሳዩት አምላክ ቀለማት በሰዎች ስሜት ላይ የሚያመጡትን ለውጥ በሚገባ ያውቃል። ለምሳሌ ያህል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የራእይ መጽሐፍ ጦርነትን፣ ረሃብን እንዲሁም በምግብ እጥረትና በቀሳፊ በሽታዎች ምክንያት ያለ ዕድሜ መቀጨትን ጨምሮ በዛሬው ጊዜ ስለሚታዩት ሁኔታዎች አስቀድሞ ተናግሯል። ይህን ትንቢት ለማስታወስ እንዲረዳን ሲባል የተለያዩ ቀለማት ባላቸው ፈረሶች ላይ ስለተቀመጡ ጋላቢዎች የሚገልጽ አስደናቂ ራእይ በዚህ መጽሐፍ ላይ ተመዝግቦልናል፤ የፈረሶቹ የተለያዩ ቀለማት የየራሳቸው ትርጉም አላቸው።

የመጀመሪያው ፈረስ ነጭ ሲሆን ክርስቶስ ኢየሱስ የሚያካሂደውን የጽድቅ ጦርነት ያመለክታል። ቀጥሎ የታየው ፈረስ ፍም የሚመስል ቀይ ቀለም አለው፤ ይህም በሕዝቦች መካከል የሚደረገውን ጦርነት የሚወክል ነው። ይህን ፈረስ ተከትሎ የመጣው አስፈሪ ጥቁር ፈረስ ደግሞ ረሃብን ያመለክታል። ከዚያም “ግራጫ ፈረስ” ብቅ አለ፤ በዚህ ፈረስ ላይ “የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበር።” (ራእይ 6:1-8) የእያንዳንዱ ፈረስ ቀለም፣ ፈረሱ የሚያመለክተውን ነገር እንድናስብ ያደርገናል። በመሆኑም የተለያየ ቀለም ያላቸውን እነዚህን ፈረሶችና ስለ ዘመናችን የያዙትን ትምህርት በቀላሉ ማስታወስ እንችላለን።

ቀለማት፣ በአእምሯችን ውስጥ ቁልጭ ብሎ የሚታየን ምስል ለመፍጠር እንደተሠራባቸው የሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ። በእርግጥም የብርሃን፣ የቀለማትና የሰው ዓይን ፈጣሪ የሆነው አምላክ፣ ለመረዳት ቀላል የሆኑና የማይረሱ ምስሎችን በአንባቢያን አእምሮ ውስጥ በመፍጠር ለማስተማር ሲል ቀለማትን አስደናቂ በሆነ መንገድ ተጠቅሞባቸዋል። ቀለማት መረጃዎችን ለመሰብሰብና የሰበሰብነው መረጃ ያለውን ትርጉም ለመረዳት ያስችሉናል። ቀለማት ስሜታችንን ይነካሉ። ቀለማት አስፈላጊ የሆኑ ሐሳቦችን እንድናስታውስ ይረዱናል። በእርግጥም ቀለማት አፍቃሪው ፈጣሪያችን በሕይወት እንድንደሰት ሲል የሰጠን ስጦታዎች ናቸው።