አባቴና አያቴ የሚኖሩት በአሁኗ ሞልዶቫ ሰሜናዊ ክልል በሚገኝ ክቲዣኒ በተባለ የገበሬዎች መንደር ሲሆን የሚኖሩበት ቤት ተሠርቶ አላለቀም ነበር። ታኅሣሥ 1939 በዚሁ ቤት ውስጥ ተወለድኩ። በ1930ዎቹ መጀመሪያ ላይ አያቴና አባቴ የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። እናቴም፣ አያቴ ከመንደሩ ቄስ የበለጠ መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚያውቅ ስትገነዘብ የይሖዋ ምሥክር ሆነች።

የሦስት ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ፣ አጎቴና አያቴ በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት ተይዘው የጉልበት ሥራ ወደሚሠራባቸው ካምፖች ተወሰዱ። በሕይወት ተርፎ ወደ ቤቱ የተመለሰው አባቴ ብቻ ነው። አባቴ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በ1947 ወደ ቤቱ ሲመለስ ወገቡ ላይ ጉዳት ደርሶበት ነበር። አካሉ በጣም ተጎድቶ የነበረ ቢሆንም በእምነቱ ጸንቷል።

በሕይወታችን ያጋጠሙን ከፍተኛ ለውጦች

የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለሁ የእኛን ቤተሰብ ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሞልዶቫውያን የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ሳይቤሪያ በግዞት ተወሰዱ። ሐምሌ 6 ቀን 1949፣ ከብቶች በሚጓጓዙባቸው የባቡር ፉርጎዎች ውስጥ ታጎርን። ለ12 ቀናት ያህል ከ6,400 ኪሎ ሜትር የሚበልጥ ርቀት ያለማቋረጥ ከተጓዝን በኋላ ሌብያዤ የሚባለው የባቡር ጣቢያ ስንደርስ ቆምን። የአካባቢው ባለሥልጣናት ባቡር ጣቢያው ጋ እየጠበቁን ነበር። በትናንሽ ቡድኖች ከከፋፈሉን በኋላ ወዲያውኑ ወደተለያየ ቦታ እንድንሄድ አደረጉ። የእኛ ቡድን፣ ወና በሆነ አንድ አነስተኛ ትምህርት ቤት ውስጥ መኖር ጀመረ። በድካም ዝለን እንዲሁም ልባችን በሐዘን ተሰብሮ ነበር። ከእኛ ጋር የነበሩ አንዲት አረጋዊት፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ያቀናበሩትን አንድ መዝሙር ማንጎራጎር ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ ሁላችንም ቀጥሎ ያሉትን ስንኞች ከእኚህ አረጋዊት ጋር በሙሉ ልባችን አብረን መዘመር ጀመርን፦

“ብዙ ወንድሞቻችንን ሩቅ ቦታ ወሰዷቸው።

ወደ ሰሜንና ወደ ምሥራቅ አጋዟቸው።

መከራ ገጠማቸው፣ የአምላክን ፈቃድ በማድረጋቸው፤ የሞትን ያህል የከበዱ ፈተናዎችን ተወጥተዋል በጽናት።”

ከጊዜ በኋላ እሁድ እሁድ፣ ከቤታችን 13 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በሚገኝ ሥፍራ በሚደረግ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስብሰባ ላይ መካፈል ቻልን። ብዙውን ጊዜ ገና በደንብ ሳይነጋ ከቤታችን በመውጣት እስከ ወገብ የሚደርስ ጥልቀት ባለው በረዶ ላይ እንጓዛለን፤ ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚደርስበት ወቅት ነበር። ሃምሳ ወይም ከዚያ በላይ የምንሆን ሰዎች በአንዲት ትንሽ ክፍል ውስጥ ታጭቀን እንሰበሰብ ነበር። ስብሰባውን የምንጀምረው ሁለት ወይም ሦስት መዝሙሮች በመዘመር ነው። ከዚያም ልባዊ ጸሎት ይቀርብና ለአንድ ሰዓት ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች ላይ ውይይት ይደረጋል። ቀጥሎም መዝሙሮች እንዘምርና በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች ላይ ውይይት እናደርጋለን። ይህ በመንፈሳዊ በጣም የሚያጠናክር ጊዜ ነበር!

ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ገጠሙን

በዣንኮይ ባቡር ጣቢያ፣ በ1974 ገደማ

በግዞት የተወሰድነው የይሖዋ ምሥክሮች በ1960 ከበፊቱ የበለጠ ነፃነት ተሰጠን። ድሆች ብንሆንም ወደ ሞልዶቫ ለጉብኝት መሄድ የቻልኩ ሲሆን በዚያም ከኒና ጋር ተዋወቅሁ፤ የኒና ወላጆችና አያቶችም የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ብዙም ሳይቆይ ከኒና ጋር ተጋባንና ወደ ሳይቤሪያ ተመልሰን ሄድን፤ እዚያም ሴት ልጃችን ዲና በ1964፣ ወንድ ልጃችን ቪክቶር ደግሞ በ1966 ተወለዱ። ከሁለት ዓመታት በኋላ ወደ ዩክሬን ሄድንና ዣንኮይ የምትባል አንዲት ከተማ ውስጥ በአንድ አነስተኛ ቤት መኖር  ጀመርን፤ ዣንኮይ የምትገኘው በክራይሜያ ባሕረ ገብ መሬት ላይ ካለችው ከያልታ ከተማ 160 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ነው።

በመላዋ ሶቪየት ኅብረት እንደነበረው ሁሉ በክራይሜያም የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ታግዶ ነበር። ይሁን እንጂ እገዳው ያን ያህል ጥብቅ አልነበረም፤ እንዲሁም ባለሥልጣናቱ እግር በእግር እየተከታተሉ ስደት አያደርሱብንም ነበር። በመሆኑም አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች የመዘናጋትና የቸልተኝነት መንፈስ ይታይባቸው ጀመር። በሳይቤሪያ ብዙ ሥቃይ ስላሳለፉ አሁን ጠንክረው በመሥራት በቁሳዊ ረገድ በተወሰነ መጠን የተመቻቸ ሕይወት ለመምራት ጥረት ማድረጋቸው ተገቢ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር።

አስደሳች ለውጥ

መጋቢት 27 ቀን 1991፣ በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት በሙሉ ሥራችን ሕጋዊ እውቅና ተሰጠው። ወዲያውኑ በመላው አገሪቱ በሰባት ቦታዎች የ2 ቀን ትልቅ ስብሰባ ለማድረግ እቅድ ተያዘ። እኛ የምንካፈለው ነሐሴ 24 በኦዴሳ፣ ዩክሬን በሚደረገው ስብሰባ ላይ ነበር። ስብሰባው የሚካሄድበትን ትልቅ የእግር ኳስ ስታዲየም ለማዘጋጀት አንድ ወር ቀደም ብዬ እዚያ ደረስኩ።

ቀኑን ሙሉ ስንሠራ እንውልና ማታ ላይ በስታዲየሙ በሚገኙት አግዳሚ ወንበሮች ላይ እንተኛ ነበር። እህቶች በቡድን ተከፋፍለው በስታዲየሙ ዙሪያ ያለውን መናፈሻ አጸዱ። ሰባት መቶ ኩንታል የሚያህል ጥራጊ ተጭኖ ተወሰደ። የመስተንግዶ ክፍል ውስጥ የሚሠሩት ወንድሞች ወደ ስብሰባው እንደሚመጡ ለሚጠበቁት 15,000 ልዑካን ማረፊያ ለመፈለግ ከተማዋን ሲያስሱ ይውሉ ነበር። ከዚያም በድንገት ያልጠበቅነው ነገር ተከሰተ!

ነሐሴ 19 ቀን ይኸውም ስብሰባችን ሊጀምር አምስት ቀን ብቻ ሲቀረው የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ፕሬዚዳንት ሚክሃይል ጎርባቾቭ በያልታ አቅራቢያ ሽርሽር ላይ ሳሉ ተይዘው ታሰሩ። ስብሰባ እንድናደርግ የተሰጠን ፈቃድ ተሰረዘ። ከዚያም ወደ ስብሰባው ሊመጡ የተዘጋጁት ልዑካን ስብሰባውን ወደሚያደራጀው ቢሮ እየደወሉ “የአውቶብስ እና የባቡር ቲኬት ቆርጠን ነበር፤ ታዲያ ምን እናድርግ?” እያሉ መጠየቅ ጀመሩ። ስብሰባውን የሚያደራጁት ወንድሞች አጥብቀው ከጸለዩ በኋላ ይህን ጥያቄ ላቀረቡት ሁሉ “የሚሆነው ባይታወቅም ኑ!” አሏቸው።

ወንድሞች መዘጋጀታቸውንና መጸለያቸውን ቀጠሉ። የመጓጓዣ ክፍሉ ከተለያዩ የሶቪየት ኅብረት ክፍሎች የመጡ ልዑካንን እየተቀበለ ወደተመደቡበት ቦታ ማድረስ ጀመረ። የስብሰባው ኮሚቴ አባላት በየዕለቱ ጠዋት ላይ የከተማዋን ባለሥልጣናት ለማነጋገር ይሄዳሉ። ይሁን እንጂ ጥሩ ዜና ይዘው መመለስ አልቻሉም።

ለጸሎቶቻችን መልስ አገኘን

ሐሙስ ነሐሴ 22 ይኸውም ስብሰባው ሊጀምር ከታሰበበት ዕለት ሁለት ቀን ቀደም ብሎ የስብሰባው ኮሚቴ አባላት መልካም ዜና ይዘው ተመለሱ፤ ስብሰባው እንዲካሄድ ተፈቀደ! በስብሰባው መክፈቻ ላይ በአንድነት ስንዘምርና አብረን ስንጸልይ ደስታችን ወሰን አልነበረውም። የቅዳሜው ፕሮግራም ከተደመደመ በኋላ እያወራንና ከቀድሞ ወዳጆቻችን ጋር እየተጫወትን አመሸን። እነዚህ ወንድሞች ጠንካራ እምነት ስላላቸው እጅግ አስቸጋሪ ፈተናዎችን ጸንተው ተቋቁመዋል።

በኦዴሳ ያደረግነው ትልቅ ስብሰባ፣ 1991

ከዚያ ስብሰባ በኋላ ባሉት 22 ዓመታት ከፍተኛ መንፈሳዊ እድገት ታይቷል። በመላው ዩክሬን የመንግሥት አዳራሾች ተገንብተዋል፤ በ1991 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር 25,000 የነበረ ሲሆን አሁን ግን ከ150,000 በላይ ሆኗል!

አሁንም በመንፈሳዊ ሀብታሞች ነን

ቤተሰባችን አሁንም የሚኖረው በዣንኮይ በሚገኘው ቤታችን ነው፤ በዚህች ከተማ ውስጥ 40,000 ያህል ሰው ይኖራል። በ1968 ከሳይቤሪያ ወደዚህ ስንመጣ በአካባቢው የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰቦች ጥቂት ነበሩ፤ አሁን ግን በዣንኮይ ስድስት ጉባኤዎች አሉ።

የእኔ ቤተሰብ ቁጥርም ጨምሯል። እኔና ባለቤቴ፣ ልጆቻችን፣ የልጆቻችን ልጆች እና የእነሱ ልጆች በአጠቃላይ አራት ትውልድ የምንሆን የቤተሰቤ አባላት በአሁኑ ወቅት ይሖዋን እያገለገልን ነው።