በጣም የምታደንቀው ምን ዓይነት ስጦታ ነው? አብዛኞቻችን፣ አንድ ሰው ግዴታ እንዳለበት ተሰምቶት ሳይሆን በፍቅር ተገፋፍቶ ስጦታ ሲሰጠን ደስ እንደሚለን ጥርጥር የለውም። ስጦታ ከመስጠት ጋር በተያያዘ አንድ ሰው ለመስጠት የተነሳሳበትን ምክንያት ትልቅ ቦታ እንሰጠዋለን። አምላክም ለዚህ ነገር ትልቅ ቦታ የሚሰጥ መሆኑ ይበልጥ ሊያሳስበን ይገባል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የጻፈውን በ2 ቆሮንቶስ 9:7 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ልብ በል።

ጳውሎስ ይህን ሐሳብ የጻፈው ለምን ነበር? የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች፣ በይሁዳ የሚኖሩ የተቸገሩ የእምነት አጋሮቻቸውን እንዲረዱ ሊያበረታታቸው ፈልጎ ነበር። ታዲያ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እርዳታ እንዲሰጡ ለማስገደድ ሞክሮ ይሆን? በፍጹም፤ ከዚህ ይልቅ እንዲህ ብሎ ጻፈ፦ “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ እያንዳንዱ ሰው ቅር እያለው ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ።” እስቲ ይህን ምክር ጠለቅ ብለን እንመርምረው።

“በልቡ ያሰበውን።” አንድ እውነተኛ ክርስቲያን፣ ስጦታ የሚሰጠው ለመስጠት “በልቡ” ስለወሰነ እንደሆነ ጳውሎስ ገልጿል። ከዚህ ለማየት እንደምንችለው አንድ ክርስቲያን የእምነት ባልንጀሮቹ ስለሚያስፈልጋቸው ነገር ትኩረት ይሰጣል። አንድ ምሁር እንደተናገሩት እዚህ ጥቅስ ላይ “ያሰበውን” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “አስቀድሞ መወሰን የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል።” ስለዚህ አንድ ክርስቲያን የእምነት አጋሮቹ ስለሚያስፈልጋቸው ነገር በቁም ነገር ያስባል እንዲሁም የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት ምን ማድረግ እንደሚችል ራሱን ይጠይቃል።—1 ዮሐንስ 3:17

“ቅር እያለው ወይም ተገዶ ሳይሆን።” ጳውሎስ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሊያደርጓቸው የማይገቡ ሁለት ነገሮችን ጠቅሷል፤ ይኸውም ቅር እያላቸው ወይም ተገድደው መስጠት የለባቸውም። “ቅር እያለው” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ አገላለጽ ቃል በቃል ሲተረጎም “እያዘነ” ማለት ነው። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው ቅር እያለው ወይም እያመነታ የሚሰጥ ሰው “ገንዘቡን አውጥቶ መስጠቱን ሲያስበው ልቡ ያዝናል።” ተገዶ የሚሰጥ ሰው ደግሞ እንዲህ የሚያደርገው ጫና እንደተደረገበት ስለተሰማው ነው። ታዲያ አንድ ሰው ስጦታ የሰጠን ቅር እያለው ወይም ተገዶ ቢሆን ደስ ይለናል?

“አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ።” አንድ ክርስቲያን ለመስጠት ከወሰነ በኋላ ይህን የሚያደርገው በደስታ ሊሆን እንደሚገባ ጳውሎስ ተናግሯል። በእርግጥም ደስታ የሚገኘው በጥሩ ልብ ተነሳስቶ በመስጠት ነው። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) አንድ ሰው በደስታ የሚሰጥ ከሆነ ይህ ለሌሎች በግልጽ ይታያል። እንዲያውም “በደስታ” የሚለው ቃል፣ ሰጪው በውስጡ ያለውን ስሜት እንዲሁም በሚሰጥበት ወቅት የሚታይበትን ስሜት ሊገልጽ ይችላል። በደስታ የሚሰጥ ሰው በሚያደርግልን ነገር ልባችን ይነካል። እንዲህ ያለው ሰጪ የአምላክንም ልብ ያስደስታል። አንድ ሌላ ትርጉም “አምላክ መስጠት የሚወዱ ሰዎችን ይወዳል” ይላል።—ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን

“አምላክ መስጠት የሚወዱ ሰዎችን ይወዳል”

ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የጻፈው ሐሳብ ከመስጠት ጋር በተያያዘ ለክርስቲያኖች ጥሩ መመሪያ ይሆናቸዋል። ጊዜያችንንም ሆነ ጉልበታችንን ወይም ቁሳዊ ንብረታችንን ስንሰጥ ይህን የምናደርገው በፈቃደኝነት እንዲሁም ለሌሎች በተለይም ለተቸገሩ መስጠት ከልብ ስለሚያስደስተን ሊሆን ይገባል። እንዲህ ስናደርግ እኛ የምንደሰት ከመሆኑም ሌላ በአምላክ ዘንድም ተወዳጅ እንሆናለን፤ ምክንያቱም ‘እሱ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወዳል።’

በመስከረም ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል

1ኛ እና 2ኛ ቆሮንቶስ