መከራ የበዛውና የሰው ልጆች መከራን ለማስወገድ ያደረጉት ጥረት ያልተሳካው ለምን እንደሆነ ለመረዳት የችግሩን ዋነኛ መንስኤ ለይተን ማወቅ ያስፈልገናል። መንስኤዎቹ የተለያዩና ውስብስብ ቢሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ለይተን እንድናውቃቸው ስለሚረዳን አመስጋኞች ነን። መከራ የበዛው ለምን እንደሆነ የሚጠቁሙ አምስት ዋና ዋና ምክንያቶች በዚህ ርዕስ ላይ ይብራራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ምን እንደሚል እንድትመረምር እንጋብዝሃለን፤ ይህን ስታደርግ የአምላክ ቃል፣ ለዚህ ከባድ ጉዳይ መንስኤው በእርግጥ ምን እንደሆነ በግልጽ ለመረዳት የሚያስችለን እንዴት እንደሆነ ትገነዘባለህ።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

የመጥፎ አገዛዝ ውጤት

“ክፉዎች ሲገዙ . . . ሕዝብ ያቃስታል” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ምሳሌ 29:2

ታሪክ እንደሚያሳየው፣ ጨካኝ የሆኑና በተገዢዎቻቸው ላይ ይህ ነው የማይባል መከራ ያደረሱ በርካታ አምባገነን ገዥዎች በዓለም ላይ ተነስተዋል። እርግጥ ነው፣ ሁሉም መሪዎች እንደዚህ ናቸው ማለት አይደለም። አንዳንዶቹ መሪዎች ወገኖቻቸውን ለመርዳት በቅን ልቦና የተነሳሱ ሊሆኑ ይችላሉ። ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ግን ብዙውን ጊዜ ውስጥ ለውስጥ በሚደረግ ሽኩቻ እንዲሁም ለሥልጣን በሚደረግ ትግል የተነሳ ጥረታቸው ሁሉ መና ይቀራል። ወይም ደግሞ ሥልጣናቸውን ለግል ጥቅማቸው ይጠቀሙበት ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ሕዝቦችን ለከፋ ጉዳት ይዳርጋል። የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ዋና ጸሐፊ ሄነሪ ኪሲንጀር “ታሪክ፣ ሳይሳኩ የቀሩ ጥረቶች እና ሳይፈጸሙ የቀሩ ውጥኖች . . . የሚወሱበት መድረክ ነው” በማለት ተናግረዋል።

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው፣ ሰው ‘አካሄዱን በራሱ አቃንቶ ሊመራ አይችልም።’ (ኤርምያስ 10:23) ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች፣ የራሳቸውን አካሄድ በተሳካ ሁኔታ ለመምራት የሚያስፈልገው ጥበብና ማስተዋል ይጎድላቸዋል። ታዲያ ሰዎች የራሳቸውን አካሄድ አቃንተው መምራት የማይችሉ ከሆነ አንድን አገር በተሳካ ሁኔታ መምራት እንዴት ይችላሉ? ሰብዓዊ መሪዎች መከራን ማስወገድ የማይችሉት ለምን እንደሆነ ተረዳህ? አብዛኛውን ጊዜ እንዲያውም፣ የመከራ መንስኤ መጥፎ መስተዳድር ወይም መጥፎ አገዛዝ ነው!

የሐሰት ሃይማኖት የሚያሳድረው ተጽዕኖ

ኢየሱስ “በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 13:35

የየትኛውም ሃይማኖት መሪዎች ስለ ፍቅርና ስለ አንድነት ይሰብካሉ። ሐቁ ሲታይ ግን፣ ምዕመኖቻቸው ጭፍን ጥላቻንና መድልዎን እንዲያስወግዱ የሚያነሳሳቸው ጠንካራ ፍቅር እንዲኖራቸው መርዳት አልቻሉም። ብዙውን ጊዜ ሃይማኖት፣ ሰዎች ፍቅርን እንዲያዳብሩ ከመርዳት ይልቅ በሕዝቦችና በተለያዩ ብሔሮች መካከል መከፋፈል፣ ጠባብነትና ግጭት እንዲኖር ምክንያት ሆኗል። የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ሀንስ ኩንግ፣ ክርስትና እና የዓለም ሃይማኖቶች (እንግሊዝኛ) በተሰኘው መጽሐፋቸው ማጠቃለያ ላይ “ከሁሉ የከፋ ጽንፈኝነትና ጭካኔ የታየባቸው ፖለቲካዊ ትግሎች፣ የሃይማኖት ተጽዕኖና ግፊት ያለባቸው እንዲሁም በሃይማኖት እውቅና የተሰጣቸው ናቸው” በማለት ጽፈዋል።

በተጨማሪም የብዙ ሃይማኖቶች መሪዎች፣ ከጋብቻ በፊትና  ከጋብቻ ውጭ የሚደረግ የፆታ ግንኙነትን እንዲሁም ግብረ ሰዶማዊነትን በግልጽ ሲደግፉ ይታያሉ። ይህም ለበሽታ፣ ለጽንስ ማስወረድ፣ ላልተፈለጉ እርግዝናዎች እንዲሁም ለትዳርና ለቤተሰብ መፍረስ ምክንያት በመሆኑ ተዘርዝሮ የማያልቅ ሥቃይና መከራ አስከትሏል።

የሰዎች አለፍጽምና እና የራስ ወዳድነት ምኞቶች

“እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል። ከዚያም ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች።”—ያዕቆብ 1:14, 15

ሁላችንም በወረስነው አለፍጽምና ምክንያት ስህተት መሥራት የሚቀናን ሲሆን ‘የሥጋችንን ፈቃድ’ ላለመፈጸም መታገል ይኖርብናል። (ኤፌሶን 2:3) በውስጣችን ያለውን መጥፎ ምኞት ለመፈጸም የተመቻቸ ሁኔታ ሲፈጠር ደግሞ ከምኞታችን ጋር የምናደርገው ትግል ይበልጥ ከባድ ይሆናል። ለመጥፎ ምኞቶች ከተሸነፍን መዘዙ የከፋ ሊሆን ይችላል።

ደራሲ ፊሮዝ ሜታ “ብዙውን ጊዜ ለመከራ ምክንያት የሆነው፣ በምኞት መቋመጣችን እንዲሁም ተድላን በማሳደድና ሥጋዊ ፍላጎትን በማርካት ላይ ማተኮራችን ብሎም ስግብግብና የሥልጣን ጥመኞች መሆናችን ነው” በማለት ጽፈዋል። አልኮልን፣ ዕፅን፣ ቁማርን፣ የፆታ ብልግናን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት ሱስና ምኞት፣ ብዙ “ጨዋ ዜጎች” እንዲበላሹ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ በቤተሰቦቻቸው፣ በወዳጆቻቸውና በሌሎች ላይ መከራ አስከትሏል። የሰው ዘር ፍጽምና የጎደለው ከመሆኑ አንጻር በሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ መስማማታችን አይቀርም፦ “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ በአንድነት ሆኖ በመቃተትና አብሮ በመሠቃየት ላይ እንደሚገኝ እናውቃለን።”—ሮም 8:22

የክፉ መናፍስት ተጽዕኖ

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰይጣን “የዚህ ሥርዓት አምላክ” እንደሆነና ግብረ አበሮቹም አጋንንት ተብለው የሚጠሩ ኃያላን የሆኑ ክፉ መናፍስት እንደሆኑ ይገልጻል።—2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ራእይ 12:9

አጋንንትም እንደ ሰይጣን ሁሉ ሰዎችን ይቆጣጠራሉ እንዲሁም ያስታሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ ሲናገር ይህንን ሐቅ መግለጹ ነበር፦ “ትግል የምንገጥመው ከደምና ከሥጋ ጋር ሳይሆን ከመንግሥታት፣ ከሥልጣናት፣ ይህን ጨለማ ከሚቆጣጠሩ የዓለም ገዥዎች እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራዎች ካሉ ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ነው።”—ኤፌሶን 6:12

አጋንንት በሰዎች ላይ ጥቃት መሰንዘር ቢያስደስታቸውም ዋነኛው ግባቸው ግን ይህ አይደለም። ዋናው ዓላማቸው ሰዎችን ከልዑሉ አምላክ ከይሖዋ ማራቅ ነው። (መዝሙር 83:18) እንደ ኮከብ ቆጠራ፣ አስማትና ጥንቆላ የመሳሰሉት ተግባሮች አጋንንት ሰዎችን ለማታለልና ለመቆጣጠር ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ጥቂቶቹ ናቸው። ይሖዋ ከእነዚህ አደጋዎች እንድንጠበቅ የሚያስጠነቅቀን እንዲሁም ሰይጣንንና አጋንንቱን ለሚቃወሙ ሰዎች ጥበቃ የሚያደርገው ለዚህ ነው።—ያዕቆብ 4:7

የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ውስጥ ነው

ሁለት ሺህ ከሚያህሉ ዓመታት በፊት የተጻፈ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት “በመጨረሻዎቹ ቀኖች ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ” ይላል።

ትንቢቱ በመቀጠል፣ ዘመናችንን ለመቋቋም የሚያስቸግር እንዲሆን የሚያደርገው ነገር ምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ . . . ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ፣ አምላክን ከመውደድ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ።” በእርግጥም በዛሬው ጊዜ ለምናየው መከራ ሁሉ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ፣ የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ውስጥ መሆኑ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-4

እስካሁን ከመረመርናቸው ምክንያቶች አንጻር፣ ሰዎች በቅን ልቦና ተነሳስተው የሚጥሩ ቢሆንም መከራን ለማስቆም ያልቻሉበት ምክንያት ግልጽ ነው። ታዲያ እርዳታ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው? “የዲያብሎስን” እንዲሁም የተከታዮቹን “ሥራ ለማፍረስ” ቃል የገባው ፈጣሪያችን እርዳታ ሊያደርግልን ይችላል። (1 ዮሐንስ 3:8) የሚቀጥለው ርዕስ፣ አምላክ ለመከራ መንስኤ የሚሆኑትን ነገሮች በሙሉ ለማስወገድ ምን እርምጃ እንደሚወስድ ያብራራል።