በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ነሐሴ 2013

 መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

“ሕይወቴ ወዴት አቅጣጫ እያመራ እንደሆነ በቁም ነገር ማሰብ ጀመርኩ”

“ሕይወቴ ወዴት አቅጣጫ እያመራ እንደሆነ በቁም ነገር ማሰብ ጀመርኩ”
  • የትውልድ ዘመን፦ 1941

  • የትውልድ አገር፦ አውስትራሊያ

  • የኋላ ታሪክ፦ አጫሽና ጠጪ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግሁት ዋሪያልዳ በምትባል ኒው ሳውዝ ዌልስ ውስጥ በምትገኝ አንዲት ትንሽ የገጠር ከተማ ነው። የዋሪያልዳ ማኅበረሰብ በጎችንና ከብቶችን እንደ ማርባት እንዲሁም እህል እንደ መዝራት ባሉ የተለያዩ የግብርና ሥራዎች የተሰማሩ ናቸው። ከተማዋ ንጹሕ ከመሆኗም በላይ እምብዛም ወንጀል የማይፈጸምባት ናት።

 

ከአሥር ልጆች መካከል የመጀመሪያው እኔ በመሆኔ በ13 ዓመቴ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ለማቅረብ ሥራ መሥራት ነበረብኝ። በትምህርቴ ብዙ ስላልገፋሁ የተሰማራሁት በግብርና ሙያ ነበር። አሥራ አምስት ዓመት ሲሆነኝ ከብት ጠባቂ በመሆን ያልተገሩ ፈረሶችን አላምድ ነበር።

በግብርና ሥራ ላይ መሰማራቴ ጥሩም ሆነ መጥፎ ጎን ነበረው። በአንድ በኩል ሥራዬንና የምውልበትን አካባቢ በጣም እወደው ነበር። ምሽት ላይ እሳት ካቀጣጠልኩ በኋላ ቁጭ ብዬ ከጫካው የሚመጣውን ነፋሻማ አየር እየተነፈስኩ ጨረቃዋንና በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ እመለከት ነበር። በዚህ ወቅት ‘እነዚህን አስደናቂ ነገሮች በሙሉ የፈጠረ አንድ አካል መኖር አለበት’ ብዬ አስብ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ በሥራ ቦታዬ ለአንዳንድ ጎጂ ልማዶች ተጋለጥኩ። ብዙ ጊዜ ሰዎች ሲሳደቡ እሰማ ነበር፤ እንዲሁም ሲጋራ በቀላሉ ማግኘት እችል ነበር። ብዙም ሳይቆይ ማጨስና መሳደብ የሕይወቴ ክፍል ሆነ።

አሥራ ስምንት ዓመት ሲሞላኝ ወደ ሲድኒ ሄድኩ። ጦር ሠራዊቱ ውስጥ ለመግባት ብሞክርም በትምህርቴ ብዙ ስላልገፋሁ ተቀባይነት ሳላገኝ ቀረሁ። ይሁንና ሌላ ሥራ በማግኘቴ ሲድኒ ውስጥ አንድ ዓመት ቆየሁ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘሁት በዚህ ጊዜ ነበር። ባቀረቡልኝ ግብዣ መሠረት አንድ ቀን በስብሰባቸው ላይ ተገኘሁ፤ በዚህ ወቅት የሚያስተምሩት ትምህርት እውነት እንደሆነ ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደብኝም።

ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ወደ ጫካ ሕይወቴ ተመለስኩ። በመጨረሻም ኩዊንስላንድ በምትገኘው ጉንዲዊንዲ መኖር ጀመርኩ። በዚያም ሥራ አገኘሁ እንዲሁም ትዳር መሠረትኩ፤ የሚያሳዝነው መጠጣትም ጀመርኩ።

 በኋላም ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለድን። ልጆቹ ከተወለዱ በኋላ ግን ሕይወቴ ወዴት አቅጣጫ እያመራ እንደሆነ በቁም ነገር ማሰብ ጀመርኩ። ሲድኒ ሳለሁ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ የሰማሁት ነገር ትዝ አለኝ፤ እናም ሕይወቴን ስለምመራበት መንገድ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ ተሰማኝ።

በአውስትራሊያ ያለውን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ አድራሻ የያዘ አንድ የቆየ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት አገኘሁ። ከዚያም እንዲረዱኝ ደብዳቤ ጻፍኩ። በዚህ ምክንያት ደግና አፍቃሪ የሆነ አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲረዳኝ ተላከልኝ። ወዲያው ከዚህ ሰው ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናሁ ስሄድ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልገኝ ተረዳሁ። በተለይ በጣም ልቤን የነካው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ 2 ቆሮንቶስ 7:1 ነበር። ይህ ጥቅስ “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን” እንድናነጻ ያበረታታል።

በመሆኑም ማጨሴንና አልኮል ከልክ በላይ መጠጣቴን ለማቆም ወሰንኩ። ከሱሶቹ ጋር ለረጅም ጊዜ አብሬ ስለኖርኩ እነዚህን ለውጦች ማድረግ ቀላል አልነበረም። ይሁን እንጂ አምላክን በሚያስደስት መንገድ ለመኖር ቆርጬ ነበር። ከሁሉ በላይ የረዳኝ በሮም 12:2 ላይ የሚገኘውን “የዚህን ሥርዓት የአኗኗር ዘይቤ መኮረጅ አቁሙ፤ ከዚህ ይልቅ . . . አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ” የሚለውን ጥቅስ ተግባራዊ ማድረጌ ነው። መጥፎ ልማዶቼን ለማስወገድ አስተሳሰቤን መለወጥና አምላክ እንዲህ ላሉ ልማዶች ያለው ዓይነት አመለካከት ማዳበር ይኸውም ጎጂ መሆናቸውን መገንዘብ እንደሚያስፈልገኝ ተረዳሁ። በእሱ እርዳታ፣ ማጨሴንና ከልክ በላይ መጠጣቴን ማቆም ቻልኩ።

‘መጥፎ ልማዶቼን ለማስወገድ አስተሳሰቤን መለወጥ እንደሚያስፈልገኝ ተረዳሁ’

ከሁሉ ይበልጥ ፈታኝ የሆነብኝ ግን መሳደቤን ማቆም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ በኤፌሶን 4:29 ላይ “የበሰበሰ ቃል ከቶ ከአፋችሁ አይውጣ” በማለት የሚሰጠውን ምክር አውቀው ነበር። ያም ሆኖ መጥፎ ቃላት የመናገር ልማዴን ቶሎ ማስወገድ አልቻልኩም። በኢሳይያስ 40:26 ላይ በሚገኙት ቃላት ላይ ማሰላሰል ጠቃሚ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ይህ ጥቅስ በከዋክብት የተሞሉትን ሰማያት በሚመለከት እንዲህ ይላል፦ “ዐይናችሁን አንሡ፤ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤ እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? የከዋክብትን ሰራዊት አንድ በአንድ የሚያወጣቸው፣ በየስማቸው የሚጠራቸው እርሱ ነው። ከኀይሉ ታላቅነትና ከችሎታው ብርታት የተነሣ፣ አንዳቸውም አይጠፉም።” አምላክ፣ በማየት የምደሰትበትን ግዙፉን ጽንፈ ዓለም ለመፍጠር የሚያስችል ኃይል ካለው እሱ የሚደሰትብኝ ዓይነት ሰው ለመሆን የሚያስፈልገኝን ለውጥ እንዳደርግ ለእኔ ኃይል ለመስጠት እንደሚችል ጥርጥር የለውም ብዬ አሰብኩ። በብዙ ጸሎትና ጥረት ቀስ በቀስ አንደበቴን መቆጣጠር ቻልኩ።

ያገኘሁት ጥቅም፦

ከብት ጠባቂ ሳለሁ በምሠራበት ቦታ የነበሩት ሰዎች ጥቂቶች ስለነበሩ ከሰዎች ጋር ለመጨዋወት ብዙ አጋጣሚ አልነበረኝም። ሆኖም በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ በሚሰጡት ሥልጠናዎች አማካኝነት ሐሳቤን እንዴት መግለጽ እንዳለብኝ ተማርኩ። ሥልጠናው ካስገኘልኝ ጥቅም አንዱ ለሌሎች ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች የመናገር ችሎታ ማዳበር ነው።—ማቴዎስ 6:9, 10፤ 24:14

ላለፉት በርካታ ዓመታት በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኜ እያገለገልኩ ነው። የእምነት አጋሮቼን ለመርዳት የምችለውን ሁሉ ማድረጌ ለእኔ ትልቅ መብት ነው። ትልቁ በረከት ግን ታማኝና አፍቃሪ ከሆነችው ሚስቴ እንዲሁም ከምወዳቸው ልጆቼ ጋር ይሖዋን በአንድነት ማገልገሌ ነው።

ይሖዋ በትምህርት ብዙም ላልገፋሁት ለእኔ ከእሱ የመማር መብት ስለሰጠኝ አመሰግነዋለሁ። (ኢሳይያስ 54:13) በምሳሌ 10:22 ላይ ከሚገኘው “የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤ መከራንም አያክልባትም” ከሚለው ሐሳብ ጋር ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ። እኔና ቤተሰቤ ስለ ይሖዋ የበለጠ የምንማርበትንና እሱን ለዘላለም የምናገለግልበትን ጊዜ በናፍቆት እንጠባበቃለን።