በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ሰኔ 2013

 ወደ አምላክ ቅረብ

ይሖዋ ‘አያዳላም’

ይሖዋ ‘አያዳላም’

መድልዎ ተፈጽሞብህ ያውቃል? በቆዳህ ቀለም፣ በዘርህ ወይም ደግሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ ባለህ ቦታ ምክንያት ያቀረብከው ጥያቄ ውድቅ የሆነበት፣ ተገቢ የሆነ አገልግሎት ሳታገኝ የቀረህበት አሊያም ንቀት በተሞላበት መንገድ የተስተናገድክበት ጊዜ አለ? ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የደረሰብህ አንተ ብቻ አይደለህም። እንደዚህ ዓይነቶቹ ክብርን ዝቅ የሚያደርጉ ተግባሮች በምድር ላይ የተለመዱ ቢሆኑም በአምላክ ዘንድ ግን ቦታ እንደሌላቸው ማወቁ ያጽናናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘አምላክ አያዳላም’ በማለት በሙሉ ትምክህት ተናግሯል።—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35ን አንብብ።

ጴጥሮስ ይህን የተናገረው ፈጽሞ በማይጠበቅ ቦታ ይኸውም ከአሕዛብ ወገን በሆነው በቆርኔሌዎስ ቤት ውስጥ ሆኖ ነበር። ጴጥሮስ ከአይሁድ ቤተሰብ የተወለደ ሲሆን በዘመኑ አይሁዳውያን አሕዛብን እንደ ርኩስ ነገር ይመለከቷቸው ስለነበር ከእነሱ ጋር ምንም ዓይነት ቅርርብ አይፈጥሩም ነበር። ታዲያ ጴጥሮስ ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት የሄደው ለምንድን ነው? በአጭሩ፣ ሁለቱንም ያገናኛቸው ይሖዋ ስለሆነ ነው። ጴጥሮስ ባየው መለኮታዊ ራእይ ላይ “አምላክ ንጹሕ ያደረገውን ነገር ርኩስ ነው ማለትህን ተው” ተብሎ ተነግሮት ነበር። ጴጥሮስ ባያውቅም ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ ቆርኔሌዎስም ራእይ አይቶ ነበር፤ በዚህ ወቅት ቆርኔሌዎስ ጴጥሮስን እንዲያስጠራው አንድ መልአክ አዝዞት ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 10:1-15) ጴጥሮስ በጉዳዩ ውስጥ የይሖዋ እጅ እንዳለበት ሲገነዘብ ቆርኔሌዎስን ከማናገር ወደ ኋላ አላለም።

ጴጥሮስ “አምላክ እንደማያዳላ በእርግጥ አስተዋልኩ” በማለት ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 10:34) ‘የማያዳላ’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም ‘ፊት የማያይ’ ይኸውም ፊት አይቶ አንዱን ከሌላው የማያበላልጥ የሚል ፍቺ አለው። (ዘ ኪንግደም ኢንተርሊንየር ትራንስሌሽን ኦቭ ዘ ግሪክ ስክሪፕቸርስ) አንድ ምሁር ስለዚህ ቃል ሲናገሩ “ቃሉ የሚያመለክተው ጉዳዩን ግምት ውስጥ በማስገባት ሳይሆን የአንድን ሰው ፊት በመመልከት ይኸውም ግለሰቡን ስለወደደው ወይም ስላልወደደው ብቻ ፍርድ የሚሰጥን ዳኛ ነው” ብለዋል። አምላክ ፊት በማየት ማለትም የሰዎችን ዘር፣ ብሔር፣ የኑሮ ደረጃ ወይም ሌሎች ውጫዊ ነገሮችን በመመልከት አንዱን ከሌላው አያበላልጥም።

ከዚህ ይልቅ ይሖዋ የሚያየው በልባችን ውስጥ ያለውን ነው። (1 ሳሙኤል 16:7፤ ምሳሌ 21:2) ጴጥሮስ በመቀጠል “ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 10:35) አምላክን መፍራት ሲባል እሱን የሚያሳዝን ምንም ነገር ባለማድረግ እሱን እንደምናከብረውና በእሱ እንደምንታመን ማሳየት ማለት ነው። የጽድቅ ሥራ መሥራት ደግሞ በአምላክ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር በፈቃደኝነት መፈጸምን ይጠይቃል። አንድ ሰው፣ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የሚያነሳሳውን አክብሮታዊ ፍርሃት በውስጡ ሲያዳብር ይሖዋ ይደሰትበታል።—ዘዳግም 10:12, 13

ይሖዋ ከሰማይ ሆኖ ወደ ታች ሲመለከት የሚያየው አንድ ዘር ብቻ ይኸውም የሰውን ዘር ነው

መድልዎ ወይም ጭፍን ጥላቻ ደርሶብህ የሚያውቅ ከሆነ ጴጥሮስ አምላክን አስመልክቶ ከተናገረው ሐሳብ ትልቅ ማበረታቻ እንደምታገኝ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሖዋ ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ወደ እውነተኛው አምልኮ እየሳበ ነው። (ዮሐንስ 6:44፤ የሐዋርያት ሥራ 17:26, 27) ዘራቸው፣ ብሔራቸው ወይም የኑሮ ደረጃቸው ምንም ይሁን ምን እሱን የሚያመልኩ ሰዎች የሚያቀርቡትን ጸሎት ሰምቶ ምላሽ ይሰጣል። (1 ነገሥት 8:41-43) ይሖዋ ከሰማይ ሆኖ ወደ ታች ሲመለከት የሚያየው አንድ ዘር ብቻ ይኸውም የሰውን ዘር እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። አንተስ የማያዳላ አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋ ይበልጥ ማወቅ አትፈልግም?

በሰኔ ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል

ዮሐንስ 17-21እስከ የሐዋርያት 1-10