በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ሰኔ 2013

ለዘመናት ተደብቆ የቆየ ውድ ሀብት

ለዘመናት ተደብቆ የቆየ ውድ ሀብት

ተመራማሪው ዓይኑን ማመን አቅቶታል። ጥንታዊ የሆነን አንድ የጽሑፍ ቁራጭ ደግሞ ደጋግሞ እየመረመረ ነው። የጽሑፉን የፊደል አጣጣልና ሰዋስው ሲመለከት እስከ ዛሬ በጆርጂያ ቋንቋ ከተዘጋጁት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ሁሉ ጥንታዊ የሆነውን እንዳገኘ እርግጠኛ ሆነ!

ይህ ውድ ሀብት የተገኘው በ1922 ታኅሣሥ ወር መገባደጃ ላይ ነው፤ ይህ የሆነው ጆርጂያዊው ምሁር ኢቫን ዣቫኪሽቪሊ ስለ ጆርጂያ ፊደል አመጣጥ ምርምር እያካሄደ ሳለ ነበር። ምሁሩ ጥናቱን በሚያካሂድበት ወቅት አንድ የኢየሩሳሌም ታልሙድ ቅጂ በድንገት አገኘ። ቅጂውን በጥንቃቄ ሲመረምረው በዕብራይስጥ ከተጻፈው ጽሑፍ ሥር በጆርጂያ ፊደላት የተጻፈ በደንብ ያልጠፋ ጽሑፍ እንዳለ አስተዋለ። *

በታልሙዱ ሥር ተደብቆ የነበረው ጽሑፍ በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. እንደተዘጋጀ የሚገመት የኤርምያስ መጽሐፍ የተወሰነ ክፍል ነው። ይህ ጽሑፍ ከመገኘቱ በፊት በጆርጂያ ቋንቋ ከተዘጋጁት ሁሉ እጅግ ጥንታዊ እንደሆነ የሚታሰበው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በዘጠነኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የተዘጋጀው ነው። ብዙም ሳይቆይ ግን በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. እንዲያውም ከዚያ ቀደም ብሎ የተዘጋጁ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ተገኙ። ኢየሱስና ሐዋርያቱ ከኖሩበት ጊዜ ብዙም ሳይርቅ ማለትም ከጥቂት መቶ ዓመታት በኋላ የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ማግኘት ምን ያህል እንደሚያስደስት አስበው!

ይህንን ትርጉም ያዘጋጀው ማን ነው? በአንድ ግለሰብ የተዘጋጀ ነው ወይስ በቡድን የተሠራ? እስካሁን ድረስ ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሰጥ የታሪክ መረጃ አልተገኘም። ትርጉሙን ያዘጋጀው ማንም ይሁን ማን፣ በአራተኛው መቶ ዘመንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉ ወይም በከፊል በጆርጂያ ቋንቋ ተተርጉሞ እንደነበረ ብሎም የጆርጂያ ሕዝብ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአፍ መፍቻ ቋንቋው የአምላክን ቃል ማግኘት ወይም መማር ይችል እንደነበረ በግልጽ ማየት ይቻላል።

የጆርጂያ ሕዝብ ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር ምን ያህል ትውውቅ እንደነበረው የሚያሳይ ዘገባ ዘ ማርትርደም ኦቭ ሴንት ሹሻኒክ ዘ ኩዊን (የቅድስቲቱ ንግሥት ሹሻኒክ ሰማዕትነት) በተሰኘ በአምስተኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ እንደተጻፈ በሚታመን መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል። የመጽሐፉ ደራሲ የዚችን ንግሥት አሳዛኝ ታሪክ በሚጽፍበት ጊዜ ከመዝሙር መጽሐፍ፣ ከወንጌሎችና ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የተወሰዱ ጥቅሶችንና በተዘዋዋሪ የተጠቀሱ ሐሳቦችን አካትቷል። በተጨማሪም የጆርጂያ ግዛት የሆነችው የካርትሊ አገረ ገዥ የነበረው የሹሻኒክ ባል ማለትም ቫርስኬን የፋርስን ጌቶች ለማስደሰት ሲል “ክርስትናን” ትቶ ዞሮአስትሪያኒዝም ወደሚባለው የፋርስ ሃይማኖት እንደገባና ሚስቱም እንዲሁ እንድታደርግ ለማስገደድ እንደሞከረ ተርኳል። መጽሐፉ እንደሚገልጸው ከሆነ ንግሥቲቱ እምነቷን ለመካድ ፈቃደኛ አልነበረችም፤ እንዲሁም ከመገደሏ በፊት ቅዱሳን መጻሕፍትን በማንበብ መጽናኛ ታገኝ ነበር።

ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ከአምስተኛው መቶ ዘመን  ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስን በጆርጂያ ቋንቋ መተርጎምና መገልበጥ ተቋርጦ አያውቅም። በጆርጂያ ቋንቋ፣ ብዛት ያላቸው በእጅ የተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ሊገኙ የቻሉት ትጉ የሆኑ ገልባጮችና ተርጓሚዎች ከፍተኛ ጥረት በማድረጋቸው ነው። በጆርጂያ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎምና ለማተም የተደረገውን ጥረት የሚያስቃኘንን ትኩረት የሚስብ ታሪክ እስቲ እንመርምር።

የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በብዛት መዘጋጀት ጀመሩ

“እዚህ ግባ የማልባል መነኩሴ የሆንኩት እኔ ጂኦርጂ በከፍተኛ ትጋትና ልፋት ይህን የመዝሙር መጽሐፍ ከአዲሱ ግሪክኛ ወደ ጆርጂያ ቋንቋ ተርጉሜያለሁ።” ይህን የጻፈው በ11ኛው መቶ ዘመን የኖረው ጂኦርጂ ምታስሚንዴሊ የተባለ የጆርጂያ መነኩሴ ነው። ይሁንና ቀድሞውንም ቢሆን ከብዙ መቶ ዓመታት ጀምሮ በጆርጂያ ቋንቋ የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እያለ እንደ አዲስ መተርጎም ለምን አስፈለገ?

በጆርጂያ ቋንቋ በእጅ ከተጻፉት ጥንታዊ ትርጉሞች መካከል እስከ 11ኛው መቶ ዘመን ድረስ ሳይጠፉ የቆዩት በጣም ጥቂት ነበሩ። አንዳንዶቹ መጻሕፍት እስከነጭራሹ ጠፍተው ነበር። በተጨማሪም ቋንቋው በተወሰነ መጠን ተለውጦ ስለነበረ አንባቢዎች የጥንቶቹን ቅጂዎች መረዳት ይቸግራቸው ነበር። ምንም እንኳ በርካታ ተርጓሚዎች በጆርጂያ ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ ከጥፋት ለመታደግ ጥረት ቢያደርጉም ጂኦርጂ የተጫወተው ሚና ግን ከፍተኛ ነበር። ጂኦርጂ በወቅቱ የነበሩትን በጆርጂያ ቋንቋ የተዘጋጁ ትርጉሞች ከግሪክኛው ጋር ለማመሳከር ጥረት አድርጓል፤ እንዲሁም አንዳንድ የጎደሉ ክፍሎችን አልፎ ተርፎም ሙሉ መጻሕፍትን ተርጉሟል። የአንድ ገዳም አስተዳዳሪ እንደመሆኑ መጠን ቀን ላይ ይህን ኃላፊነቱን የሚወጣ ሲሆን ማታ ማታ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ይተረጉም ነበር።

በጂኦርጂ ዘመን የኖረው ኤፍሬም ምጺሬ፣ የጂኦርጂ የትርጉም ሥራ አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲሄድ አድርጓል። ለተርጓሚዎች እንደ መመሪያ ሆኖ የሚያገለግል ደንብ አዘጋጅቷል። ይህ ደንብ ለትርጉም ሥራ የሚሆኑ መሠረታዊ መመሪያዎችን ይዟል፤ ለምሳሌ ያህል፣ በተቻለ መጠን መጽሐፍ ቅዱስን ከመጀመሪያው ቋንቋ ላይ መተርጎም እንደሚገባ እንዲሁም በዚህ ቋንቋ የተገለጸውን ሐሳብ በቀጥታ ለማስተላለፍ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ ሆኖም የቋንቋው ለዛ እንዳይጠፋ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ይገልጻል። በተጨማሪም በጆርጂያ ቋንቋ ትርጉሞች ውስጥ የግርጌ ማስታወሻዎችንና የሕዳግ ማጣቀሻዎችን ማስገባትን ያስተዋወቀው እሱ ነው። ኤፍሬም በርከት ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን ሙሉ በሙሉ በአዲስ መልክ ተርጉሟል። የጂኦርጂና የኤፍሬም ሥራዎች ከዚያ በኋላ ለተካሄዱት የትርጉም ሥራዎች ጠንካራ መሠረት ጥለዋል።

በአጠቃላይ ሲታይ በቀጣዩ መቶ ዓመት በጆርጂያ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ላይ ጥሩ እድገት ታይቷል። በጄላቲ እና በኢካልቶ በሚገኙ ከተሞች የትምህርት ተቋማት ተቋቁመው ነበር። በአሁኑ ጊዜ በጆርጂያ የጥንታዊ ጽሑፎች ብሔራዊ ማዕከል ውስጥ ተጠብቆ የሚገኘው ጄላቲ ባይብል ተብሎ የሚጠራው መጽሐፍ ቅዱስ ከጄላቲ ወይም ከኢካልቶ ምሁራን መካከል በአንዱ የተዘጋጀና ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደሆነ አብዛኞቹ ምሁራን ይስማማሉ።

መጽሐፍ ቅዱስን የመተርጎም ሥራ በጆርጂያ ሕዝብ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር? በ12ኛው መቶ ዘመን ጆርጂያዊ ገጣሚ የነበረው ሾታ ረስታቬሊ፣ ለብዙ ዘመናት ከፍተኛ ተጽዕኖ ከማሳደሩ የተነሳ ሁለተኛው የጆርጂያ መጽሐፍ ቅዱስ ተብሎ እስከመጠራት የደረሰውን ቬፕኪስትካኦሳኒ (የአውሬ ለምድ የለበሰ የቤተ መንግሥት ወታደር) የተሰኘ ግጥም ጽፎ ነበር። የዘመናችን ምሁር  የሆኑት ጆርጂያዊው ኬከሊድዜ እንደገለጹት ከሆነ ግጥሙ ከመጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ የተጠቀሰ ይሁንም አይሁን “የጻፋቸው አንዳንድ ሐሳቦች የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በቀጥታ የሚያንጸባርቁ ናቸው።” ግጥሙ በገሃዱ ዓለም የማይሆኑ ነገሮች የበዙበት ቢሆንም እንደ እውነተኛ ወዳጅነት፣ ለጋስነት፣ ለሴቶች አክብሮት ማሳየት እና ለማናውቃቸው ሰዎች ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማሳየት ያሉ ርዕሰ ጉዳዮችን በተደጋጋሚ ይዳስሳል። እነዚህና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምራቸው የሥነ ምግባር እሴቶች በጆርጂያ ሕዝብ አስተሳሰብ ላይ ለብዙ ዘመናት የዘለቀ ተጽዕኖ ያሳደሩ ሲሆን አሁንም ድረስ እንደ ሥነ ምግባር ደንብ ይመለከቷቸዋል።

የንጉሣውያን ቤተሰብ መጽሐፍ ቅዱስን ለማተም ያደረገው ጥረት

በ17ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ የጆርጂያ ንጉሣዊ ቤተሰብ መጽሐፍ ቅዱስን ለማሳተም ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ለዚህም ሲባል ንጉሥ ቫክታንግ ስድስተኛ በዋና ከተማዋ ተብሊሲ አንድ ማተሚያ ቤት አቋቋመ። ይሁን እንጂ ለኅትመት የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ አልነበረም። የጆርጂያ መጽሐፍ ቅዱስ እንደገና የተደበቀ ያህል ሆኖ ነበር። ማግኘት የተቻለው ያልተሟሉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ሲሆን ጽሑፎቹ የተተረጎሙበት ቋንቋም ቢሆን ጊዜ ያለፈበት ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን አርሞና አሟልቶ የማዘጋጀቱ ሥራ የቋንቋ ሊቅ ለነበረው ሱልካን ሳባ ኦርቤሊያኒ በአደራ ተሰጠ።

ኦርቤሊያኒ ሥራውን በጥንቃቄ ማከናወኑን ተያያዘው። ኦርቤሊያኒ ግሪክኛንና ላቲንን ጨምሮ በርካታ ቋንቋዎችን ያውቅ ስለነበረ በጆርጂያ ቋንቋ ከተዘጋጁት ጥንታዊ መጽሐፍ ቅዱሶች በተጨማሪ የተለያዩ ምንጮችን ማመሳከር ችሎ ነበር። ይሁን እንጂ ያልተበረዘ አመለካከት ይዞ ለመተርጎም ያደረገው ጥረት የጆርጂያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አላስደሰተም። ቀሳውስቱ ቤተ ክርስቲያኗን ክዷል ብለው የከሰሱት ከመሆኑም በላይ ንጉሡ መጽሐፍ ቅዱስን የመተርጎሙን ሥራ እንዲያስቆም ማሳመን ቻሉ። አንዳንድ የጆርጂያ የታሪክ ምንጮች እንደሚገልጹት ከሆነ በአንድ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ላይ ቀሳውስቱ ኦርቤሊያኒ ለብዙ ዓመታት የለፋበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዲያቃጥል አስገድደውታል።

ደስ የሚለው ነገር፣ እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቆ የቆየ ምጽኪየታ የሚባል (ሳባስ ባይብል በመባልም ይታወቃል) አንድ ጥንታዊ ጽሑፍ ኦርቤሊያኒ በእጁ የጻፈውን አስተያየት ይዟል። ይሁን እንጂ ቀሳውስቱ የተቃወሙት ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መሆኑን አንዳንዶች ይጠራጠራሉ። ኦርቤሊያኒ ያዘጋጀው እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው በተጨማሪ ክፍሎቹ ላይ የቀረበውን ሐሳብ ብቻ ነው።

ብዙ ችግሮች ቢኖሩም አንዳንድ የንጉሣውያን ቤተሰቦች መጽሐፍ ቅዱስን ለማተሙ ሥራ ቅድሚያ መስጠታቸውን ቀጥለው ነበር። ከ1705 እስከ 1711 ባሉት ዓመታት የተወሰነው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ታትሞ ነበር። ባካሪ እና ቫኩሽቲ የሚባሉት ጆርጂያውያን መሳፍንት ላደረጉት ጥረት ምስጋና ይግባውና በመጨረሻ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ በ1743 ታትሞ ወጣ። መጽሐፍ ቅዱስ ከዚያ በኋላ ሊደበቅ አልቻለም።

^ አን.3 በጥንት ጊዜ የጽሕፈት መሣሪያዎችን ማግኘት አስቸጋሪና ውድ ነበር። ስለዚህ ከዚህ በፊት የተጻፈውን ነገር ፍቆ በላዩ ላይ እንደ አዲስ መጻፍ የተለመደ ነገር ነበር። እንዲህ ዓይነቶቹ ጥንታዊ የእጅ ጽሑፎች ፓሊምፕሰስት ተብለው የሚጠሩ ሲሆን ትርጉሙ “እንደገና የተፋቀ” ማለት ነው።