በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ወደ አምላክ ቅረብ

አምላክ በእርግጥ ስለ አንተ ያስባል?

አምላክ በእርግጥ ስለ አንተ ያስባል?

“ወደ አምላክ ለመቅረብ በማደርገው ጥረት ከሁሉ የበለጠ ከባድ የሆነብኝ ነገር ‘አልረባም’ የሚለውን ስሜት መቋቋም ሳይሆን አይቀርም።” ይህን ሐሳብ የተናገረችው ሴት፣ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ስለ እሷ እንደሚያስብ ማመን ይከብዳት ነበር። አንተስ እንደ እሷ ይሰማሃል? ከሆነ ‘በእርግጥ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ በግለሰብ ደረጃ ያስብላቸዋል?’ የሚል ጥያቄ ይፈጠርብህ ይሆናል። የዚህ ጥያቄ መልስ ‘አዎን’ የሚል ነው። ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብም ይህንን ያረጋግጣል።—ዮሐንስ 6:44ን አንብብ።

ስለ ይሖዋ ባሕርይም ሆነ ስለ አምላክ ፈቃድ ከማንም ይበልጥ የሚያውቀው ኢየሱስ የተናገረውን እስቲ እንመልከት። (ሉቃስ 10:22) ኢየሱስ “የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም” ብሏል። በመሆኑም አንድ ሰው የክርስቶስ ተከታይም ሆነ የሰማዩ አባታችን የይሖዋ አገልጋይ ሊሆን የሚችለው ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ከሳበው ብቻ ነው። (2 ተሰሎንቄ 2:13) ኢየሱስ የተናገረው ይህ ሐሳብ ምን ትርጉም እንዳለው በመመርመር ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ እናገኛለን።

ይሖዋ ወደ እሱ ይስበናል ሲባል ምን ማለት ነው? ኢየሱስ በዚህ ጥቅስ ላይ “ካልሳበው” ብሎ ሲናገር የተጠቀመበት የግሪክኛ ግስ ዓሦች የያዘ መረብን ከውኃ ውስጥ ጎትቶ ከማውጣት ጋር በተያያዘም ሊሠራበት ይችላል። (ዮሐንስ 21:6, 11) ታዲያ ዓሦቹ ያለፍላጎታቸው በመረብ እንደሚጎተቱ ሁሉ ይሖዋም እሱን እንድናገለግለው ያስገድደናል ማለት ነው? በፍጹም። ይሖዋ የራሳችንን ምርጫ የማድረግ ነፃነት ሰጥቶናል፤ በመሆኑም በግድ ልባችንን ለመክፈት አይሞክርም። (ዘዳግም 30:19, 20) አንድ ምሁር ይህን ሁኔታ ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል፦ “የልባችን በር፣ ከውጭ በኩል ለመክፈት የሚያስችል እጀታ የለውም። በመሆኑም መከፈት ያለበት ከውስጥ ነው።” ይሖዋ እሱን የሚፈልጉ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎችን ለማግኘት በዓለም ላይ ያሉ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ልብ ይመረምራል። (1 ዜና መዋዕል 28:9) ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ሰዎችን ሲያገኝ ወደ እሱ የሚስብበት መንገድ ልብ የሚነካ ነው። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው?

ይሖዋ፣ “ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎችን ወደ እሱ የሚስበው በግድ ሳይሆን ቀስ ብሎ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 13:48) ይህን የሚያደርገው በሁለት መንገዶች ይኸውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ምሥራች በግለሰብ ደረጃ እንዲደርሰን በማድረግ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን በመጠቀም ነው። ይሖዋ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመቀበል ፈቃደኛ ልብ ያለው ሰው ሲያገኝ ግለሰቡ ይህን እውነት እንዲያውቅና በሕይወቱ ተግባራዊ ማድረግ እንዲችል በመንፈሱ አማካኝነት ይረዳዋል። (1 ቆሮንቶስ 2:11, 12) በመሆኑም አምላክ ባይረዳን ኖሮ እውነተኛ የኢየሱስ ተከታዮች እንዲሁም ለይሖዋ ያደርን አገልጋዮች መሆን ፈጽሞ አንችልም ነበር።

“የልባችን በር፣ ከውጭ በኩል ለመክፈት የሚያስችል እጀታ የለውም። በመሆኑም መከፈት ያለበት ከውስጥ ነው”

ታዲያ ኢየሱስ በዮሐንስ 6:44 ላይ የተናገረው ሐሳብ ስለ ይሖዋ አምላክ ምን ያስተምረናል? ይሖዋ ሰዎችን ወደ እሱ የሚስበው በልባቸው ውስጥ መልካም ነገር ስላገኘና በግለሰብ ደረጃ ስለሚያስብላቸው ነው። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ሴት ይህንን እውነት ማወቋ አጽናንቷታል። እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋ አገልጋይ መሆን ከሁሉ የላቀ መብት ነው። በመሆኑም ይሖዋ የእሱ አገልጋይ እንድሆን ከመረጠኝ በእሱ ዓይን ውድ ነኝ ማለት ነው።” አንተስ? ይሖዋ ለአገልጋዮቹ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብላቸው ማወቅህ ወደ እሱ ይበልጥ እንድትቀርብ አያነሳሳህም?

በግንቦት ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል

ሉቃስ 22-24ዮሐንስ 1-16