በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ሚያዝያ 2013

 መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
  • የትውልድ ዘመን፦ 1960
  • የትውልድ አገር፦ ፊንላንድ
  • የኋላ ታሪክ፦ የሄቪ ሜታል ሙዚቀኛ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦

ያደግሁት የወደብ ከተማ በሆነችው በቱርኩ ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሠራተኞች በሚኖሩበት ሠፈር ነው። አባቴ በቦክስ ውድድር ሻምፒዮን ሆኖ ያውቃል፤ እኔና ታናሽ ወንድሜም ቦክስ መጋጠም እንወድ ነበር። ትምህርት ቤት ውስጥ ብዙ ጊዜ ልጆች እንድደባደብ ይፈታተኑኝ ነበር፤ እኔም ለመቧቀስ አመንትቼ አላውቅም። በአሥራዎቹ ዕድሜዬ ውስጥ እያለሁ አገር ካማረረ አንድ የወሮበሎች ቡድን ጋር ተቀላቀልኩ፤ በመሆኑም ይባስ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ እንደባደብ ነበር። በተጨማሪም ሄቪ ሜታል ሙዚቃ መጫወት ጀመርኩ፤ የሮክ ሙዚቃ ኮከብ የመሆን ምኞትም አደረብኝ።

የተወሰኑ ታምቡሮች ገዛሁና የሙዚቃ ባንድ አቋቋምኩ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የባንዱ ዋና ዘፋኝ ለመሆን በቃሁ። መድረክ ላይ ቅጥ ያጣ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስደስተኝ ነበር። የባንዱ አባላት ኃይለኞች በመሆናችንና ሥርዓት የሌለው ሁኔታ ይታይብን የነበረ በመሆኑ ቀስ በቀስ ሰፊ እውቅና አገኘን። እንዲያውም በብዙ ተመልካቾች ፊት መጫወት የጀመርን ሲሆን ሥራዎቻችንን ለቀረጻ ያበቃንባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ በተለይ የመጨረሻው ሥራችን በመገናኛ ብዙኃን ላይ ጥሩ ሽፋን አግኝቷል። በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ ባንዳችን በሰፊው እንዲታወቅ ለማድረግ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄድን። እዚያም በኒው ዮርክና በሎስ አንጀለስ የተወሰኑ ዝግጅቶች ያቀረብን ሲሆን ወደ ፊንላንድ ከመመለሳችን በፊት ደግሞ ከሙዚቃ ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች ጋር የተወሰነ ግንኙነት መሠረትን።

የባንዱ አባል መሆኔ ቢያስደስተኝም እንኳ ሕይወቴ ትርጉም እንዲኖረው እመኝ ነበር። በሙዚቃው ዓለም አንዱ በሌላው ላይ ተረማምዶ ለማደግ የሚያደርገው ጥረት ግራ መጋባት የፈጠረብኝ ሲሆን መረን የለቀቀው አኗኗሬም ብስጭት ላይ ጣለኝ። መጥፎ ሰው እንደሆንኩኝ ይሰማኝ ነበር፤ ደግሞም ሲኦል ውስጥ እቃጠላለሁ የሚለው ሐሳብ ያስጨንቀኝ ነበር። ለጥያቄዎቼ መልስ ለማግኘት የተለያዩ መንፈሳዊ ጽሑፎችን አገላብጫለሁ፤ በተጨማሪም አምላክን ፈጽሞ ላስደስተው እንደማልችል ቢሰማኝም እንዲረዳኝ አጥብቄ መጸለይ ጀመርኩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

የምተዳደረው በአካባቢያችን በሚገኝ ፖስታ ቤት ተቀጥሬ በመሥራት ነበር። አንድ ቀን ከሥራ ባልደረቦቼ አንዱ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነ ተገነዘብኩ። እኔም የጥያቄ መዓት አዥጎደጎድኩበት። የሰጠኝ አሳማኝና ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆነ መልስ የማወቅ ጉጉቴን ስለቀሰቀሰው ከእሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን  ለማጥናት ፈቃደኛ ሆንኩ። ለተወሰኑ ሳምንታት ካጠናሁ በኋላ የሙዚቃ ባንዱ በዩናይትድ ስቴትስ አንድ አልበም የማውጣት አጋጣሚ ያገኘ ሲሆን የቀረጻ ውሉ ክፍያም አጓጊ ነበር። ይህ በሕይወቴ ሙሉ የማላገኘው ዕድል እንደሆነ ተሰማኝ።

መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠናኝን የይሖዋ ምሥክር አንድ ተጨማሪ አልበም መሥራት እንደምፈልግና ከዚያ በኋላ ግን በሕይወቴ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በጥብቅ እንደምከተል ነገርኩት። በዚህ ጊዜ አስጠኚዬ የራሱን አስተያየት ከመስጠት ይልቅ በማቴዎስ 6:24 ላይ የተመዘገቡትን የኢየሱስን ቃላት እንዳነብ ጠየቀኝ። ጥቅሱ “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል የለም” ይላል። ኢየሱስ የተናገረው ነገር ምን ትርጉም እንዳለው ሲገባኝ ተገረምኩ። ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ ለአስጠኚዬ ኢየሱስን መከተል ስለምፈልግ ባንዱን እንደለቀቅሁ ስነግረው እሱ ደግሞ በተራው ተገረመ!

መጽሐፍ ቅዱስ ጉድለቶቼን ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳይ መስታወት ሆኖልኛል። (ያዕቆብ 1:22-25) መጥፎ ባሕርይ እንዳለኝ ይኸውም ኩሩና ዝነኛ ለመሆን የምቋምጥ ሰው እንደሆንኩ ተገነዘብኩ። ጸያፍ አነጋገር እጠቀም እንዲሁም እደባደብ፣ አጨስና በጣም እጠጣ ነበር። አኗኗሬ ምን ያህል ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር እንደሚቃረን ስገነዘብ በራሴ ተስፋ ቆረጥኩ። ይሁን እንጂ አስፈላጊዎቹን ለውጦች ለማድረግ ቆርጬ ነበር።—ኤፌሶን 4:22-24

‘በሰማይ የሚኖረው አባታችን መሐሪ ነው፤ ደግሞም ከጥፋታቸው ንስሐ የሚገቡ ሰዎችን ቁስል መፈወስ ይፈልጋል’

በተለይ መጀመሪያ ላይ፣ ቀድሞ በሠራኋቸው መጥፎ ነገሮች የተነሳ በጸጸት ስሜት ተውጬ ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠናኝ የይሖዋ ምሥክር በጣም ረድቶኛል። መጽሐፍ ቅዱስ በኢሳይያስ 1:18 ላይ “ኀጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል” በማለት የሚናገረውን ሐሳብ አሳየኝ። (ኢሳይያስ 1:18) ይህም ሆነ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች፣ በሰማይ የሚኖረው አባታችን መሐሪ እንደሆነና ከጥፋታቸው ንስሐ የሚገቡ ሰዎችን ቁስል መፈወስ እንደሚፈልግ በእርግጠኝነት እንዳምን አደረጉኝ።

ይሖዋን እውን እንደሆነ አካል አድርጌ መመልከት ስጀምርና ለእሱ ያለኝ አድናቆት እያደገ ሲሄድ ሕይወቴን ለእሱ ለመወሰን ፍላጎት አደረብኝ። (መዝሙር 40:8) በመሆኑም በ1992 በሴንት ፒተርስበርግ፣ ሩሲያ በተደረገ የይሖዋ ምሥክሮች ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ተጠመቅኩ።

ያገኘሁት ጥቅም፦

በይሖዋ አገልጋዮች መካከል በርካታ ጥሩ ወዳጆች አፍርቻለሁ። አንዳንዴ እየተገናኘን ለዛ ያለው ሙዚቃ በመጫወት ከአምላክ ባገኘነው በዚህ ስጦታ እንደሰታለን። (ያዕቆብ 1:17) በተለይ ለእኔ ልዩ በረከት የሆነልኝ ውድ ባለቤቴ የሆነችውን ክርስቲናን ማግኘቴ ነው። ከእሷ ጋር ብዙ ነገሮችን ይኸውም የሕይወትን ውጣ ውረድ አብረን የተጋፈጥን ከመሆኑም ሌላ ውስጣዊ ስሜቴን አጋራታለሁ።

የይሖዋ ምሥክር ባልሆን ኖሮ ዛሬ በሕይወት መኖሬ አጠራጣሪ ነው። ከዚህ በፊት ችግሮችና አደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ በየጊዜው እገባ ነበር። አሁን ግን ዓላማ ያለው ሕይወት እመራለሁ፤ ደግሞም ሁሉም ነገር መልክ እንደያዘ ይሰማኛል።