ኢየሱስ የአምላክ ልጅ የተባለው ለምንድን ነው?

አምላክ ቃል በቃል ልጆች የምትወልድለት ሚስት የለውም። እሱ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ፈጣሪ ነው። ሰዎች የተፈጠሩት የአምላክን ባሕርያት ማንጸባረቅ እንዲችሉ ተደርገው ነው። በመሆኑም አምላክ የፈጠረው የመጀመሪያው ሰው ማለትም አዳም “የአምላክ ልጅ” ተብሎ ተጠርቷል። በተመሳሳይም ኢየሱስ የአባቱ ዓይነት ባሕርያት እንዲኖሩት ተደርጎ ስለተፈጠረ “የአምላክ ልጅ” ተብሏል።—ሉቃስ 3:38ን እና ዮሐንስ 1:14, 49ን አንብብ።

ኢየሱስ የተፈጠረው መቼ ነው?

አምላክ ኢየሱስን የፈጠረው አዳምን ከመፍጠሩ በፊት ነው። እንዲያውም አምላክ ኢየሱስን ከፈጠረው በኋላ መላእክትን ጨምሮ ሌሎች ነገሮችን በሙሉ ለመሥራት በእሱ ተጠቅሟል። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን የአምላክ “ፍጥረት ሁሉ በኩር” በማለት የሚጠራው ለዚህ ነው።—ቆላስይስ 1:15, 16ን አንብብ።

ኢየሱስ በቤተልሔም ከመወለዱ በፊት በሰማይ መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ ይኖር ነበር። ጊዜው ሲደርስ ኢየሱስ ሰው ሆኖ መወለድ እንዲችል አምላክ ከሰማይ ወደ ማርያም ማኅፀን አዛወረው።—ሉቃስ 1:30-32ን፣ ዮሐንስ 6:38⁠ን እና 8:23ን አንብብ።

አምላክ፣ ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ እንዲወለድ ያደረገው ለምንድን ነው? ኢየሱስ የፈጸመው ልዩ ተልእኮስ ምንድን ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማግኘት የምትችል ሲሆን መልሶቹም አምላክና ኢየሱስ ስላደረጉልህ ነገር ያለህ እውቀትና አድናቆት እንዲጨምር ያደርጋሉ።