“ዛሬ በሕይወት ያሉ ሰዎች ከዚህ ቀደም በሌላ አካል እንደኖሩ የማይታበል ሐቅ ነው፤ ሰዎች ከሞቱ በኋላ እንደገና ሌላ አካል ይዘው የሚወለዱ መሆኑ እንዲሁም የሞቱ ሰዎች ነፍሳት በሕይወት መኖራቸውን የሚቀጥሉ መሆኑም የተረጋገጠ ነገር ነው።”—ፕላቶ፣ የግሪክ ፈላስፋ፣ 5ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ.፣ “ሶቅራጥስ” የተናገረውን ሲጠቅስ

“ነፍስ ከአካል ተለይታ መኖር ስለማትችልና ራሷ አካል ስላልሆነች በተለያዩ አካሎች ውስጥ ልትኖር እንዲሁም ከአንዱ አካል ወደ ሌላው ልትሸጋገር ትችላለች።”—ጆርዳኖ ብሩኖ፣ ጣሊያናዊ ፈላስፋ፣ 16ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም.

“ሰዎች የሚሞቱ ይመስላሉ እንጂ ከሕልውና ውጭ አይሆኑም፤ . . . ሲሞቱ በሌላ አዲስ አካል መኖራቸውን ስለሚቀጥሉ ዓለምን በመስኮት ማየት የሚጀምሩ ያህል ነው።”—ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን፣ አሜሪካዊ ደራሲና ገጣሚ፣ 19ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም.

ስለ ማንነትህ ጥያቄ ተፈጥሮብህ ያውቃል? ከአሁን በፊት በሌላ አካል እንደኖርክ ተሰምቶህ ያውቃል? ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ከጥንት ዘመን ጀምሮ የተለያየ ባሕል ያላቸው ሰዎች እንዲህ ያሉትን ጥያቄዎች ሲያወጡና ሲያወርዱ ኖረዋል። አንዳንዶች ለእነዚህ ጥያቄዎች ሪኢንካርኔሽን ተብሎ የሚጠራው ጽንሰ ሐሳብ መልስ እንደሚሆን ተሰምቷቸዋል። በዚህ ጽንሰ ሐሳብ መሠረት አንድ ሰው ሲሞት በውስጡ ያለችው የማትጨበጥ “ነፍስ” ከሥጋው ወጥታ በሌላ አካል ውስጥ በመግባት (ሰው፣ እንስሳ ወይም ዕፅዋት ሊሆን ይችላል) እንደ አዲስ ትወለዳለች፤ ይህ ሂደት እየተደጋገመ እንደሚቀጥል ይታመናል።

 እንዲህ ዓይነቱ እምነት አንዳንድ ሰዎችን ሊያረካቸው ቢችልም እውነት መሆኑን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል? በመጀመሪያ ግን፣ ይህ ጽንሰ ሐሳብ የመነጨው ከየት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

የሪኢንካርኔሽን እምነት የመነጨው ከየት ነው?

የታሪክ ጸሐፊዎችና ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ ክርስቶስ ከመወለዱ ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት በተቆረቆረችው በጥንቷ ባቢሎን የኖሩ ሰዎች፣ ነፍስ እንደማትሞት ያምኑ ነበር። ሞሪስ ጃስትሮ የተባሉት ምሁር ዘ ሪሊጅን ኦቭ ባቢሎኒያ ኤንድ አሲሪያ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት የባቢሎን የሃይማኖት ምሁራን የማትሞት ነፍስ እንዳለች የሚገልጹ የተለያዩ ግምታዊ ሐሳቦች ነበሯቸው። እኚህ ሰው አክለው እንደተናገሩት ባቢሎናውያን “ሞት ወደ ሌላ ዓይነት ሕይወት የሚያሳልፍ መሸጋገሪያ” እንደሆነ ያምኑ ነበር። እነዚህ የጥንት ምሁራን “ሰው ሲሞት በሆነ መልኩ ሕልውናው እንደሚቀጥል የሚገልጽ ጽንሰ ሐሳብ ያመነጩት፣ የሞተ ሰው ለዘላለም ከሕልውና ውጭ ሆኖ እንደሚቀር አምነው መቀበል ስለከበዳቸው እንደሆነ ጥርጥር የለውም።”

ከዚህ የባቢሎናውያን እምነት በመነሳት፣ ሰው ሲሞት ነፍሱ ከእሱ ወጥታ አዲስ የሚወለድ ሌላ ሰው ውስጥ እንደምትገባ የሚገልጽ ሐሳብ በጥንቱ ዓለም በሌሎች አካባቢዎችም ብቅ ማለት ጀመረ። የሕንድ ፈላስፎች አንድ ሰው በቀጣይ ሕይወቱ የሚወለድበትን አካል የሚወስነው በቀድሞ ሕይወቱ ያደረገው ነገር እንደሆነ የሚገልጽ ጽንሰ ሐሳብ አመነጩ፤ ይህን ሁኔታ ካርማ ብለው ይጠሩታል። ተደማጭነት ያላቸው የግሪክ ፈላስፎች የሪኢንካርኔሽንን እምነት መቀበላቸው ደግሞ ይህ እምነት ሰፊ ተቀባይነት እንዲያገኝ አደረገ።

ወደ ዘመናችን ስንመጣ ደግሞ በምዕራባውያን አገሮች የሚኖሩ ሰዎች ስለ ሪኢንካርኔሽን ለማወቅ ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል። የምሥራቃውያን እምነትና ሃይማኖታዊ ልማዶች የታዋቂ ሰዎችንና የወጣቱን ትውልድ ትኩረት እየሳቡ ነው። በአሁኑ ጊዜ፣ ሰዎች ቀድሞ እንደነበራቸው በሚያስቡት ሕይወታቸው እንዳጋጠማቸው የሚያምኑትን ነገር ማወቅ ያለውን ፋይዳ የሚያብራሩ ብዛት ያላቸው መጻሕፍትና የኢንተርኔት ድረ ገጾች አሉ። የቀድሞ ሕይወትን በማወቅ የሚሰጥ ሕክምና (ፓስት ላይፍ ቴራፒ) በብዙ አገሮች በስፋት ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል። ይህ ሕክምና፣ የሰዎችን ጤንነትና ባሕርይ ለመረዳት ሂፕኖሲስ የተባለውን ዘዴ (አንድን ሰው ሰመመን ውስጥ በማስገባትና ማሰብ የሚችለውን የአእምሮውን ክፍል በማደንዘዝ አእምሮውን መቆጣጠርን ያመለክታል) ተጠቅሞ ቀድሞ እንደነበራቸው በሚታሰበው ሕይወት ያጋጠማቸውን ነገር መመርመርን ያካትታል።

ሪኢንካርኔሽን እውነት ነው?

ከጥንት ጀምሮ ሰዎች በሪኢንካርኔሽን ያምኑ የነበረ ቢሆንም ‘ይህ ጽንሰ ሐሳብ በእውነታ ላይ የተመሠረተ ነው?’ ብለን መጠየቃችን የተገባ ነው። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የሪኢንካርኔሽን እምነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተመሠረተው የክርስትና እምነት ጋር ይስማማ እንደሆነ ማወቅ እንፈልጋለን። (ዮሐንስ 17:17) ፈጣሪያችን ይሖዋ፣ የሕይወት ምንጭና “ምስጢርን የሚገልጥ አምላክ” ስለሆነ ሕይወትንና ሞትን በሚመለከት ሰዎች በሌላ መንገድ ሊያውቋቸው የማይችሏቸውን ነገሮች ይገልጽልናል። በመሆኑም ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በመመርመር ስለዚህ ጉዳይ አጥጋቢ መልስ እንደምናገኝ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዳንኤል 2:28፤ የሐዋርያት ሥራ 17:28

መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ከመረመርን አምላክ ስለዚህ ጉዳይ የሚሰጠውን መልስ በቀላሉ ማወቅ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ በዘፍጥረት 3:19 ላይ አዳምና ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ ከጣሱ በኋላ አምላክ ለአዳም የተናገረውን ሐሳብ እናገኛለን። አምላክ “ከምድር ስለ ተገኘህ፣ ወደ መጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ እንጀራህን በፊትህ ላብ ትበላለህ፤ ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ” ብሎት ነበር። አዳም የተፈጠረው ከዐፈር ነበር። ሲሞት ደግሞ ወደ ዐፈር ተመልሷል። አምላክ ከተናገረው ከዚህ ግልጽና የማያሻማ ሐሳብ በመነሳት ሰው ከሞተ በኋላ ምን እንደሚሆን መረዳት እንችላለን። አንድ ሰው ሲሞት ከሕልውና ውጭ ይሆናል እንጂ ሌላ ሰው ሆኖ ድጋሚ አይወለድም። * ሙቀት የቅዝቃዜ፣ ደረቅ የእርጥብ እንዲሁም ብርሃን የጨለማ ተቃራኒ እንደሆኑ ሁሉ ሞትም የሕይወት ተቃራኒ ነው። የሞቱ ሰዎች ሕይወት የላቸውም! ይህ ሐሳብ ለመረዳት ቀላል እና ምክንያታዊ አይደለም?

ታዲያ አንዳንድ ሰዎች ቀድሞ እንደነበራቸው በሚያስቡት ሕይወት ያጋጠሟቸውን ነገሮች እንደሚያስታውሱ የሚናገሩት ለምንድን ነው? እስካሁን ከተመለከትነው አንጻር ለዚህ ሌላ ምክንያት መኖር አለበት። ነቅተንም ሆነ ተኝተን እያለ አእምሯችን ስለሚሠራበት መንገድ እንዲሁም አንዳንድ መድኃኒቶች ወይም አሰቃቂ ገጠመኞች በአእምሯችን ላይ ስለሚያስከትሉት ውጤት የተሟላ እውቀት የለንም። በአእምሯችን ውስጥ በተቀመጡ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መረጃዎች ላይ የተመሠረቱ ሕልሞቻችንና በምናባችን የምናስባቸው ነገሮች በእውን የተፈጸሙ እስኪመስሉን ድረስ ቁልጭ ብለው ሊታዩን ይችላሉ። በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ ክፉ መንፈሳዊ  ኃይሎች እውን ያልሆኑ ነገሮች እውን እንደሆኑ እንዲሰማን የሚያደርጉ እንግዳ ነገሮች እንዲታዩን ሊያደርጉ ይችላሉ።—1 ሳሙኤል 28:7-19

ሰዎች እንደመሆናችን መጠን በሕይወት መቀጠልና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማወቅ እንፈልጋለን። ይሁንና ይህ ፍላጎት የመነጨው ከየት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈጣሪ “በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን [እንዳኖረ]” የሚገልጽ ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ይዟል። (መክብብ 3:11) ሰዎች ለዘላለም መኖር የሚፈልጉበትን ምክንያት ከዚህ መረዳት ይቻላል።

ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ በሰዎች ልብ ውስጥ ለዘላለም የመኖርን ምኞት ካኖረ ይህ ምኞት የሚሳካበትን መንገድም ይገልጽልናል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈጣሪ ታዛዥ የሆኑ ሰዎች ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ የማድረግ ታላቅ ዓላማ እንዳለው ይገልጽልናል። መዝሙራዊው ንጉሥ ዳዊት “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ተናግሯል። (መዝሙር 37:29) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጸው የአምላክ ዓላማ ጋር ተያያዥነት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ ትምህርት የሞቱ ሰዎች እንደሚነሱ የሚገልጸው ትምህርት ነው።—የሐዋርያት ሥራ 24:15፤ 1 ቆሮንቶስ 15:16-19

ትንሣኤ—ሙታን ያላቸው የተረጋገጠ ተስፋ

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከሞት ተነስተው በምድር ላይ መኖር ስለቻሉ ስምንት ሰዎች የሚገልጹ ዘገባዎች ይዟል፤ እነዚህ ታሪኮች ሲፈጸሙ በቦታው የዓይን ምሥክሮች ነበሩ። * በእነዚህ ታሪኮች ላይ፣ የሞቱት ሰዎች ራሳቸው ትንሣኤ አገኙ እንጂ በሌላ ሰው አካል አልተወለዱም። ከሞት ወደ ሕይወት የተመለሱትን ሰዎች ቤተሰቦቻቸውና ጓደኞቻቸው ወዲያውኑ አውቀዋቸዋል። የሟቾቹ ዘመዶች፣ ሟቾቹ ሌላ አካል ይዘው እንደሚወለዱ በማሰብ በአቅራቢያቸውም ሆነ ራቅ ባለ ስፍራ የተወለዱትን ሕፃናት ለማየት እንደሄዱ የሚገልጽ ሐሳብም የለም።—ዮሐንስ 11:43-45

የአምላክ ቃል፣ በቅርቡ ይህ ክፉ ዓለም ጠፍቶ በምትኩ በሚቋቋመው የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ከሞቱ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ትንሣኤ እንደሚያገኙ የሚገልጽ መሆኑ ያጽናናል። (2 ጴጥሮስ 3:13, 14) ሁሉንም ከዋክብት በስማቸው የሚጠራቸው አምላክ የማስታወስ ችሎታው ፍጹምና ገደብ የለሽ በመሆኑ በቢሊዮን የሚቆጠሩ የሞቱ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ያሳለፏቸውን ነገሮች በሙሉ ያስታውሳል! (መዝሙር 147:4፤ ራእይ 20:13) አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ በቅርብ ከሞቱት ጀምሮ ቀደም ባሉት ትውልዶች የሞቱት ሰዎች ተራ በተራ ትንሣኤ እያገኙ ሲሄዱ ሰዎች ቅድመ አያቶቻቸውን በአካል የማግኘት አጋጣሚ ይኖራቸዋል። ይህ ምንኛ አስደናቂና በደስታ የሚያስፈነድቅ ተስፋ ነው!

^ စာပိုဒ်၊ 13 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ላይ “ሙታን የት ናቸው?” የሚለውን ምዕራፍ 6⁠ን ተመልከት።

^ စာပိုဒ်၊ 18 ከሞት ስለተነሱ ሰዎች የሚገልጹት ስምንት ዘገባዎች 1 ነገሥት 17:17-242 ነገሥት 4:32-372 ነገ 13:20, 21ሉቃስ 7:11-17፣ ሉቃ 8:40-56፣ ዮሐንስ 11:38-44የሐዋርያት ሥራ 9:36-42 እና 20:7-12 ላይ ይገኛሉ። እነዚህን ዘገባዎች በምታነብበት ጊዜ ሰዎቹ ከሞት የተነሱት ብዙ የዓይን ምሥክሮች ባሉበት እንደሆነ ልብ በል። ከእነዚህ በተጨማሪ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የሚገልጽ ዘጠነኛ ዘገባ አለ።—ዮሐንስ 20:1-18