በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ከቤኒን የተላከ ደብዳቤ

ምን ውስጥ ነው የገባሁት?

ምን ውስጥ ነው የገባሁት?

በምዕራብ አፍሪካ ጎህ እየቀደደ ነው። እየተቀቀለ ያለው ሩዝና የስጎው መዓዛ አካባቢውን አውዶታል። ሴቶቹ፣ ሲያዩት እንኳ የሚከብድ ሸክም ጭንቅላታቸው ላይ አስቀምጠው ጠብቀው ይጓዛሉ። ከት ብለው የሚስቁ ሰዎች ድምፅ እንዲሁም ገበያ ላይ ዋጋ የሚደራደሩ ሰዎች እሰጥ አገባ ይሰማል። ገና ማለዳ ቢሆንም ጀምበሯ ማቃጠል ጀምራለች።

ልጆቹ፣ ዮቮ ወይም ነጭ መሆኔን ሲያዩ የተለመደውን ዘፈናቸውንና ውዝዋዜያቸውን ጀመሩ። “ዮቮ፣ ዮቮ፣ ቦን ስዋ” በማለት ሲዘፍኑ ከቆዩ በኋላ “ሽልማት አይሰጠንም?” ይላሉ። ከመካከላቸው አንደኛው ልጅ ግን አይዘፍንም ነበር። መንገዴን ስቀጥል ይህ ልጅ ተከተለኝና በእጁ እንቅስቃሴ የሆነ ምልክት ያሳየኝ ጀመር። እንቅስቃሴው የምልክት ቋንቋ ይመስል ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ የአሜሪካ የምልክት ቋንቋ ፊደላትን የተማርኩ ቢሆንም በቤኒን የሚነገረው ፈረንሳይኛ ነው።

እንደምንም ታግዬ ስሜ የሚጻፍባቸውን ስምንት ፊደላት በምልክት ቋንቋ አሳየሁት። የልጁ ፊት በፈገግታ ተሞላ። ከዚያም እጄን ይዞ ጠባብ በሆነ መንገድ እየመራኝ በአካባቢው የተለመደ ዓይነት አሠራር ወዳለው ከሸክላ የተገነባ ባለ ሁለት ክፍል መኖሪያ ቤቱ ወሰደኝ። ቤተሰቡ ሲያዩኝ ተሰበሰቡ። ሁሉም የቤተሰቡ አባላት በምልክት ቋንቋ ይነጋገሩ ነበር። ታዲያ ምን ብላቸው ይሻላል? ስሜን በምልክት ቋንቋ ከነገርኳቸው በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር የመጣሁ ሚስዮናዊት እንደሆንኩና ተመልሼ እንደምመጣ ወረቀት ላይ ጽፌ ሰጠኋቸው። መስማት የሚችሉ ጎረቤቶቻቸውም የመጡ ሲሆን ሁሉም ራሳቸውን በመነቅነቅ ፈቃደኛ እንደሆኑ ገለጹ። ‘ምን ውስጥ ነው የገባሁት?’ ብዬ አሰብኩ።

ወደ ቤት ከተመለስኩ በኋላ ‘ለእነዚህ ሰዎች “የደንቈሮም ጆሮዎች ይከፈታሉ” እንደሚሉት ያሉትን የአምላክ ተስፋዎች የሚነግራቸው ሰው ሊኖር ይገባል’ ብዬ አሰብኩ። (ኢሳይያስ 35:5) በጉዳዩ ላይ ምርምርም አደረግሁ። በቤኒን በቅርብ የተደረገ የሕዝብ ቆጠራ እንደሚያሳየው 12,000 መስማት የተሳናቸውና የመስማት ችግር ያለባቸው ሰዎች አሉ። መስማት የተሳናቸው በሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚጠቀሙት የፈረንሳይኛን የምልክት ቋንቋ ሳይሆን የአሜሪካን የምልክት ቋንቋ እንደሆነ ሳውቅ ደስ አለኝ። ይሁን እንጂ እዚህ ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንዳቸውም የአሜሪካን የምልክት ቋንቋ እንደማያውቁ ስገነዘብ አዘንኩ። ለአንዲት የአካባቢው እህት “የአሜሪካን የምልክት ቋንቋ የሚያውቅ ሰው መጥቶ ቢረዳቸው እንዴት ጥሩ ነበር” አልኳት። እሷም “ይኸው አንቺ አለሽ አይደል እንዴ?” ብላ መለሰችልኝ። ደግሞም ትክክል ነበረች! የአሜሪካን የምልክት ቋንቋ ለመማር የሚረዳ ራስ አገዝ መጽሐፍና የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ቋንቋ ያዘጋጇቸውን ዲቪዲዎች አዘዝኩ። የአሜሪካን የምልክት ቋንቋ በደንብ የምታውቅ አንዲት እህት ከካሜሩን  ወደ ቤኒን ተዛውራ ስትመጣ አጋዥ ለማግኘት ሳቀርብ የነበረው ጸሎት ተመለሰልኝ።

የምልክት ቋንቋ ለመማር ጥረት እያደረግሁ መሆኑን ብዙ ሰዎች ሰሙ። በመሆኑም ብሪስ የተባለውን ሠዓሊ ሄጄ እንዳነጋግር ሐሳብ አቀረቡልኝ። የብሪስ የሥዕል ቤት የተሠራው የዘንባባ ቅጠሎችን በማገጣጠም ሲሆን ውብቅ የሚያደርግ የአየር ጠባይ ላለበት ለዚህ አካባቢ ተስማሚ ነው። ብሪስ የቀለም መቀቢያ ብሩሹን ግድግዳው ላይ ይጠርግ ስለነበር ግድግዳው በቀለማት አሸብርቋል። ብሪስ ሁለት በርጩማዎችን አምጥቶ አቧራቸውን በመጠራረግ እንድንቀመጥበት ካዘጋጀ በኋላ መናገር እስክጀምር ዓይን ዓይኔን ያየኝ ጀመር። እኔም ዲቪዲውን ማጫወቻዬ ውስጥ አስገባሁ። ብሪስ በርጩማውን ይዞ ወደ ትንሿ ዲቪዲ ማጫወቻ ቀረብ ብሎ ተቀመጠ። ከዚያም “ገባኝ! ገባኝ!” በማለት በምልክት ቋንቋ ተናገረ። የጎረቤት ልጆች ዙሪያችንን ከብበው ተንጠራርተው ያዩ ነበር። ከመካከላቸው አንዱ “ድምፅ የሌለው ፊልም የሚያዩት ለምንድን ነው?” ሲል ሰማሁት።

ብሪስ ጋ በሄድኩ ቁጥር በዲቪዲ ማጫወቻው ዙሪያ የሚኮለኮሉት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጣ። ብዙም ሳይቆይ ብሪስና ሌሎች ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን መምጣት ጀመሩ። ስብሰባውን ለእነሱ ለመተርጎም የማደርገው ጥረት ችሎታዬን እንዳሻሽል ረዳኝ። የቡድኑ ቁጥር እያደገ ሲሄድ አንዳንዶች ራሳቸው ፈልገውኝ ይመጡ ጀመር። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ቀን በመኪናዬ እየተጓዝኩ ሳለ መንገድ ላይ ፍየሎችና አሳማዎች ገቡብኝ፤ ከእነሱ ለመሸሽ ስል መንገዱ ላይ ያለ ጉድጓድ ውስጥ በመግባቴ አሮጌዋ መኪናዬ የሚንጓጓ ድምፅ ማሰማት ጀመረች። ከዚያም በድንገት ጓ የሚል ድምፅ ከኋላ በኩል ሰማሁ። ‘ወይኔ፣ መኪናዬ ድጋሚ ተበላሽታ ባልሆነ ብቻ!’ ብዬ አሰብኩ። ደግነቱ ግን ድምፁ የመጣው ከሌላ አቅጣጫ ነበር፤ መስማት የተሳነው አንድ ሰው ሊያናግረኝ ስለፈለገ ከኋላዬ እየሮጠ መኪናዬን በመምታት ሊያስቆመኝ እየሞከረ ነበር!

የአሜሪካን የምልክት ቋንቋ የሚጠቀሙ ቡድኖች በሌሎች ከተሞችም መቋቋም ጀመሩ። በየዓመቱ በምናደርገው ትልቅ ስብሰባ ላይ በምልክት ቋንቋ የሚደረጉ ፕሮግራሞች ሲዘጋጁ ለማስተርጎም ከተጠየቁት መካከል አንዷ እኔ ነበርኩ። መድረኩ ላይ ወጥቼ ተናጋሪው እስኪጀምር በምጠብቅበት ጊዜ እዚህ ተመድቤ ማገልገል የጀመርኩበትን ወቅት ለአንድ አፍታ መለስ ብዬ አሰብኩ። ‘አፍሪካ ውስጥ የማገለግል ሚስዮናዊት እንደመሆኔ መጠን ምን ተጨማሪ ነገር ማከናወን እችላለሁ?’ እያልኩ አስብ ነበር። በፊቴ የተሰበሰቡትን የምልክት ቋንቋ ተናጋሪዎች ስመለከት የጥያቄዬ መልስ መስማት የተሳናቸውን መርዳት እንደሆነ ተሰማኝ። ከእንግዲህ ‘ምን ውስጥ ነው የገባሁት?’ ብዬ አላስብም።