በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

በመጨረሻ እውነተኛ ነፃነት አገኘሁ!

በመጨረሻ እውነተኛ ነፃነት አገኘሁ!

“እናንተን ፈልጎ የመጣ ማንም የለም፤ እዚሁ መቆየታችሁ አይቀርም” አለ የፖሊስ መኮንኑ እየሳቀ። የመጣነው ከሩሲያ ሲሆን ታታሪ ሠራተኞችና ሰላማዊ ነበርን፤ ታዲያ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከአምስት ዓመታት በኋላ በ1950 በሰሜን ኮሪያ እስረኞች የሆንነው እንዴት ነው?

ሰነዶቼ እንደሚያሳዩት የተወለድኩት በ1924 ነው። የተወለድኩት በሩሲያ ምሥራቃዊ ጫፍ አካባቢ በቻይና ድንበር አቅራቢያ ባለችው ሽማኮቭካ ሳይሆን አይቀርም።

በሩሲያ ምሥራቃዊ ጫፍ በምትገኘው በሽማኮቭካ፣ ፕሪሞርስኪይ ክሬይ መንደር ተወለድኩ

አንድ ቀን አባቴንና ሁለት ታላላቅ ወንድሞቼን ሽፍቶች ወሰዷቸው፤ ከዚያ በኋላ የት እንደደረሱ አልታወቀም። በቤተሰባችን ውስጥ ብዙ ትናንሽ ልጆች ስለነበርን እናቴ ሁላችንንም ማሳደግ ከአቅሟ በላይ ሆነባት። በመሆኑም አንድ ጎረቤታችን በቤተሰባችን ውስጥ የነበርነው ትናንሽ ልጆች የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ወደምታስተዳድረው የወላጅ አልባ ልጆች ማሳደጊያ ወስዶ እናታችን ጥላን እንደሄደች በመናገር እዚያ ሊያስገባን እንደሚችል ሐሳብ አቀረበ።

እኔን ጨምሮ ሕፃናት ልጆቿ ከእሷ ጋር ብንቆይ በረሀብ እንደምንሞት ስለተሰማት እናታችንም በዚህ ሐሳብ ተስማማች። አሁን በ80ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ ሆኜ ሳስበው እናቴ ወደ ሕፃናት ማሳደጊያው ስለላከችን አመስጋኝ ነኝ። ሕይወታችን የተረፈው እንዲህ ዓይነት ውሳኔ በማድረጓ ሳይሆን አይቀርም። ያም ሆኖ ማሳደጊያ ውስጥ እንድንገባ መፍቀዷን ሳስበው አሁንም አዝናለሁ።

እኔና ኢቫን ስንጋባ፣ 1941

በ1941 ወደ ኮሪያ የሄድኩ ሲሆን እዚያም ኢቫን የሚባል አንድ ደግ ሩሲያዊ አገባሁ። በ1942 ሴት ልጃችን ኦሊያ ኮሪያ ውስጥ በሶል ከተማ ተወለደች። በ1945 ኮልያ በ1948 ደግሞ ጆራ የተባሉ ወንዶች ልጆችን ወለድን። ባለቤቴ ሱቃችንን የሚያስተዳድር ሲሆን እኔ ደግሞ ልብስ እሰፋ ነበር። ሶል በጃፓኖች ቁጥጥር ሥር ስለነበረች ልጆቻችን ከትንሽነታቸው ጀምሮ ጃፓንኛ ይናገሩ ነበር፤ ቤት ውስጥ የምንነጋገረው ግን በሩሲያኛ ነበር። እስከ 1950 ድረስ በሶል በነበሩት ሶቪየቶች፣ አሜሪካውያንና ኮሪያውያን መካከል ሰላም ያለ ይመስል ነበር። ሁሉም የሱቃችን ደንበኞች ነበሩ።

በሰሜን ኮሪያውያን ተማረክን

በ1950 ከመቅጽበት ሁሉም ነገር በድንገት ተለዋወጠ። የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ሶልን ተቆጣጠሩ። እኛም መሸሽ ስላልቻልን ከሌሎች የውጭ አገር ዜጎች ጋር ተያዝን። ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል ከብሪታንያውያን፣ ከሩሲያውያን፣ ከአሜሪካውያንና ከፈረንሳውያን የጦር እስረኞች ጋር በመላው ሰሜን ኮሪያ ወደተለያዩ ሥፍራዎች በእግራችን እንድንጓዝ ተደርገናል። መጠለያዎች ባሉባቸው ቦታዎች ያሳርፉን የነበረ ሲሆን በዚህ ወቅት የቦምብ ሰለባ ላለመሆን እንጠነቀቅ ነበር።

አልፎ አልፎ ማሞቂያ ባላቸው ቤቶች ውስጥ እንሰነብት የነበረ ሲሆን በቂ ምግብም ይሰጠን ነበር። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ የምንበላው ማሽላ ብቻ ነው፤ እንዲሁም ቀዝቃዛ በሆኑ ባለቤት የሌላቸው ሕንፃዎች ውስጥ እንተኛ ነበር። አብረውን ከነበሩት መካከል ብዙዎቹ በተመጣጠነ ምግብ እጥረትና ሌሎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በማጣት ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል። እኔም ልጆቼ ሲሠቃዩ በጣም እጨነቅ ነበር። በሰሜን ኮሪያ የቅዝቃዜው ወቅት የሚጀምረው ቀደም ብሎ ነው። ሌሊቱን በሙሉ ምድጃ ዳር ተቀምጬ ድንጋዮችን እያሞቅሁ በልጆቼ አጠገብ አስቀምጥ እንደነበር ትዝ ይለኛል።

ወቅቱ እየሞቀ ሲመጣ አንዳንድ የገጠር ኮሪያውያን ለምግብነት የሚውሉ የዱር ተክሎችን አሳዩን፤ እኛም የዱር ሽንኩርትና ቅጠላ ቅጠል፣ ፍራፍሬ፣ ወይንና እንጉዳይ መፈለግ ጀመርን። እነዚህ ኮሪያውያን ለእኛ የጥላቻ ስሜት  እንዳልነበራቸው እንዲያውም የደረሰብንን ችግር አይተው እንዳዘኑልን ግልጽ ነበር። በቂ ምግብ ስለማናገኝ የምንመገባቸውን እንቁራሪቶች እንዴት መያዝ እንደምችል ተማርኩ። ልጆቼ እንቁራሪት እንዲሰጣቸው ሲወተውቱ መስማት ልቤን ክፉኛ ያሳዝነው ነበር።

በአንድ ወቅት ጥቅምት ወር ላይ ማንፖ ወደምትባል በሰሜን ኮሪያ የምትገኝ ትንሽ ከተማ እንድንጓዝ ታዘዝን። ለታመሙና ለትናንሽ ልጆች በበሬ የሚጎተቱ ጋሪዎች እንደሚዘጋጁ ተነገረን። ኦሊያ እና አባቷ በእግር ከሚጓዘው ቡድን ጋር እንዲሄዱ ተደረጉ። እኔና ትናንሾቹ ልጆቼ ጋሪዎቹ እስኪመጡ ድረስ ለቀናት ስንጠብቅ ቆየን። በመጨረሻም ጋሪዎቹ መጡ።

የታመሙት እስረኞች ጋሪዎቹ ላይ እንደ እህል ተነባብረው ተጫኑ። ሁኔታው በጣም ይዘገንን ነበር! ትንሹን ጆራን አዝዬ ኮልያን ጋሪው ላይ አንድ ጥግ ላስቀምጠው ስሞክር “እማማ፣ እማማ፣ ከአንቺ ጋር በእግር መሄድ እፈልጋለሁ! እባክሽ ጥለሽኝ አትሂጂ!” እያለ አለቀሰ።

ኮልያ ወደኋላ እንዳይቀር ቀሚሴን ሙጭጭ አድርጎ ይዞ ከኋላዬ ድክ ድክ እያለ ይከተለኝ ጀመር። ለቀናት በዘለቀው በዚህ አስከፊ ጉዞ ወቅት ብዙ እስረኞች ተረሽነዋል። አሞራዎች ከኋላችን እየተከተሉ በመንገድ ላይ የወደቁትን አስከሬኖች ይበሉ ነበር። በመጨረሻ ከባለቤቴና ከኦሊያ ጋር ስንገናኝ ተቃቅፈን ተላቀስን። ያንን ዕለት ሌሊቱን ሙሉ ቁጭ ብዬ ድንጋዮችን በእሳት እያሞቅሁ ልጆቼ አጠገብ ሳስቀምጥ አደርኩ። ሆኖም ሁሉም ልጆቼ አጠገቤ ስለነበሩ አእምሮዬ ሰላም አግኝቶ ነበር።

በ1953 ሰሜን ኮሪያን እና ደቡብ ኮሪያን በሚለየው 38 ፓራለል በሚባለው ቦታ አቅራቢያ ስንደርስ ሁኔታዎች በተወሰነ መጠን እየተሻሻሉ መጡ። ንጹሕ ልብሶች፣ ጫማዎች፣ ዳቦና ከረሜላም ጭምር ይሰጠን ነበር። ብዙም ሳይቆይ ብሪታንያውያን ቀጥሎም ፈረንሳውያን እስረኞች ተፈቱ። እኛን ግን እንደ ዜጎቹ ቆጥሮ ያስፈታን አገር አልነበርንም። የመጨረሻዎቹ እስረኞች ተፈትተው ሲሄዱ እኛ ብቻ ቀረን። ተስፋችን ጨልሞ ስለነበር መብላት እስኪያቅተን ድረስ አለቀስን። ኮሪያዊው መኮንን በመግቢያው ላይ የተገለጸውን ስሜት የሚጎዳ ሐሳብ የተናገረው በዚህ ጊዜ ነበር።

አዲስ ሕይወት በዩናይትድ ስቴትስ

የሚገርመው ነገር ከዚያ ብዙም ሳይቆይ፣ ከወታደሮች ነፃ የሆነውን ቀጠና ተሻግረን ወደ ደቡብ  ኮሪያ ተወሰድን። የአሜሪካ ወታደራዊ ቢሮ የምርመራ ጥያቄ ካቀረበልን በኋላ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንድንገባ ተፈቀደልን። በመርከብ ወደ ሳን ፍራንሲስኮ፣ ካሊፎርኒያ ሄድን፤ በዚያም አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት እርዳታ አደረገልን። ውሎ አድሮ ወደ ቨርጂኒያ የተዛወርን ሲሆን እዚያም የምናውቃቸው ሰዎች ራሳችንን ችለን መኖር እንድንችል በደግነት ረዱን። ከጊዜ በኋላም ወደ ሜሪላንድ ሄደን አዲስ ሕይወት ጀመርን።

ከባሌና ከሁለት ልጆቻችን ጋር፣ 1954

እንደ ምንጣፍ ማጽጃ (ቫክዩም ክሊነር) ያሉት ቀላል ነገሮች እንኳ በጣም ያስገርሙን ነበር። ስደተኞች ከመሆናችንም ሌላ ለአገሩ አዲስ በመሆናችን ለረጅም ሰዓታት ጠንክረን እንሠራ ነበር። ይሁን እንጂ ኑሮውን የለመዱት ስደተኞች አዲስ የመጡ ስደተኞችን መጠቀሚያ ሲያደርጓቸው ስመለከት አዘንኩ። እዚያ ከደረስን ብዙም ሳንቆይ አንድ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቄስ “ወደተባረከች አገር መጥታችኋል። ለማደግ ከፈለጋችሁ ከአገራችሁ ሰዎች ጋር እንዳትቀላቀሉ!” አለን። ቄሱ ይህን ማለቱ ያስደነገጠኝ ከመሆኑም ሌላ ግራ አጋባኝ። ‘እርስ በርስ መረዳዳት የለብንም ማለት ነው?’ ብዬ አሰብኩ።

በ1970 በርኒ ባትልማን የሚባል አንድ የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱስን ሊያወያየን ወደ ቤታችን መጣ። እሱም እንደ እኛ ጠንካራና በግልጽ የሚናገር ሰው ነበር። ከበርኒ ጋር ለሰዓታት አወራን። ያደግሁት በኦርቶዶክስ የወላጅ አልባ ሕፃናት ማሳደጊያ ውስጥ በመሆኑ የቤተ ክርስቲያኗን ትምህርቶች ጠንቅቄ አውቅ ነበር። ይሁን እንጂ የራሴ መጽሐፍ ቅዱስ ሊኖረኝ እንደሚገባ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም። በርኒ አንድ መጽሐፍ ቅዱስ አመጣልንና “ስለምወዳችሁ ይህን መጽሐፍ ቅዱስ እሰጣችኋለሁ” አለን። በተጨማሪም የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪ ከሆነ ቤን የሚባል የቤላሩስ ተወላጅ ጋር አስተዋወቀን።

ቤንና ሚስቱ መጽሐፍ ቅዱስን እያወጡ ለጥያቄዎቼ በደግነት መልስ ሰጡኝ። ይሁንና የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን እንደቀየሩት እርግጠኛ ነበርኩ። በተለይም ደግሞ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተማርኩት ማርያም ሌሎች ልጆች እንደሌሏት ስለነበረ በይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎች ላይ ከኢየሱስ ሌላ ልጆች እንዳሏት መገለጹ በጣም አበሳጨኝ።

አንዲት ፖላንዳዊት ጓደኛዬ ጋ ደውዬ በፖላንድ ቋንቋ በተተረጎመው መጽሐፍ ቅዱሷ ላይ ማቴዎስ 13:55, 56 ምን እንደሚል እንድታይልኝ ጠየቅኋት። ጥቅሱን አውጥታ ኢየሱስ በእርግጥም ታናናሽ ወንድሞች እንደነበሩት ስታነብልኝ ደነገጥሁ! ጓደኛዬም በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኝ ቤተ መጻሕፍት የምትሠራ አንዲት የምታውቃት ሴት ጋ ደውላ ይህንን ጥቅስ እዚያ ባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በሙሉ እንድታይላት ጠየቀቻት። ሴትየዋም በሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ጥቅሱ ኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች እንዳሉት እንደሚገልጽ ነገረቻት!

ሌሎች ብዙ ጥያቄዎችም ነበሩኝ። ልጆች የሚሞቱት  ለምንድን ነው? አገራት የሚዋጉት ለምንድን ነው? ሰዎች አንድ ቋንቋ እየተናገሩም እንኳ እርስ በርስ መስማማት የሚያቅታቸው ለምንድን ነው? ለጥያቄዎቼ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘሁት መልስ እጅግ አስደሰተኝ። አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ ዓላማው እንዳልነበረ ተማርኩ። በተለያዩ ጦርነቶች የሞቱ የምወዳቸውን ሰዎች ዳግመኛ እንደማያቸው ስማር ደስታዬ ወሰን አልነበረውም። ቀስ በቀስ ይሖዋ እውን ሆነልኝ።

ወንድ ልጄ ቬትናም ዘምቶ ከተመለሰ በኋላ ስሜቱ በጣም ይረበሽ ነበር፤ በመሆኑም አንድ ቀን በምስሎች ፊት ቆሜ አምላክ ልጄን እንዲረዳው እየለመንኩ እያለ ጸሎቴን ማቅረብ ያለብኝ ለምስሎች ሳይሆን ሕያው አምላክ ለሆነው ለይሖዋ እንደሆነ ተሰማኝ። ምስሎቹን ሳፈራርሳቸው ምንም የማይረቡ ነገሮች እንደሆኑ ተገነዘብኩ። ምስሎቹን የገዛኋቸው ከቤተ ክርስቲያን ነበር፤ በዚያን ዕለት ምሽት ግን ሁሉንም አስወገድኳቸው።

ካደግሁበት ሃይማኖት መውጣት ቀላል አልነበረም። ይሁን እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ ለተማርኳቸው ነገሮች ከምንም በላይ ትልቅ ቦታ መስጠት ጀምሬ ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላ ሴት ልጄንና ባለቤቴን ይዤ በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ወደሚገኘው ቄስ ሄድኩ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና ጥቅሶች ያሰፈርኩበትን ማስታወሻ ደብተር ይዤ ነበር። ቄሱ ጥቅሶቹን አውጥቼ ሳነብለት ራሱን እየነቀነቀ “አዪዪ፣ በቃ ጠፍተሻል” አለኝ። ከዚያም ሁለተኛ ደጃፉ እንዳንደርስ ነግሮ አባረረን።

ይህ ሁኔታ የራሷ አቋም ያላትንና የማወቅ ጉጉት የነበራትን ልጄን ኦሊያን አስገረማት። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ መመርመርና ብዙም ሳይቆይ ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ወደሚያደርጓቸው ስብሰባዎች አብራኝ መሄድ ጀመረች። እኔ በ1972 የተጠመቅሁ ሲሆን ኦሊያ ደግሞ በቀጣዩ ዓመት ተጠመቀች።

የቤተሰባችን መርሕ

ሜሪላንድ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የአትክልት ቦታዬ ውስጥ፣ በ1990 ገደማ

የቤተሰባችን መርሕ፣ ‘ያለፈውን ረስተህ በዛሬ ላይ አትኩር’ የሚል ነው። ስለዚህ አንድ ነገር ትክክል እንደሆነ ካመንንበት አዲስ ነገር ቢሆንም እንኳ ከማድረግ ፈጽሞ ወደኋላ አንልም። እኔና ልጄ ከአምላክ ጋር መቀራረብ ስንጀምር ወደ ሰዎች ቤት ሄደን ስለምንማረው ነገር ለመናገር በጣም ጓጓን። እርግጥ ነው፣ የሚሰማኝን በግልጽና ፊት ለፊት እናገር ስለነበር አንዳንድ ጊዜ አብረውኝ የሚሰብኩት የይሖዋ ምሥክሮች ጣልቃ ገብተው ትምህርቱን ለስለስ ባለ መንገድ ማብራራት ያስፈልጋቸው ነበር። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ፣ እንደ እኔው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከተለያዩ አገሮች የመጡ የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው ሰዎችን እንዴት ማነጋገር እንዳለብኝ ተማርኩ።

እኔና ሴት ልጄ፣ አይረን ከርቴን እየተባለ የሚጠራው በምሥራቅ የሚገኙ የኮሚኒስት አገሮችን ከምዕራቡ ዓለም የለየው ሁኔታ ቢወገድ ወደ ሩሲያ ሄደን ሰዎች ስለ አምላክ እንዲማሩ እንደምንረዳ አዘውትረን እናወራ ነበር። በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ስናወራው የነበረው ሁኔታ ሲፈጸም ኦሊያ ወደ ሩሲያ በመሄድ የሁለታችንም ሕልም እውን እንዲሆን አደረገች። ኦሊያ በሩሲያ መኖር የጀመረች ሲሆን በዚያም ለ14 ዓመታት ያህል አምላክን በሙሉ ጊዜዋ ስታገለግል ቆይታለች። መጽሐፍ ቅዱስን ለብዙ ሰዎች ያስጠናች ሲሆን በሩሲያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከእንግሊዝኛ ወደ ሩሲያኛ በመተርጎሙ ሥራም እገዛ አድርጋለች።

አሁን የአልጋ ቁራኛ ሆኛለሁ፤ ልጆቼም በተቻለ መጠን ተመችቶኝ እንድኖር ለማድረግ ይጥራሉ። በወጣትነቴ ያጋጠመኝ ያ ሁሉ መከራ አልፎ የተሻለ ሕይወት እንድኖር ስላስቻለኝ አምላክን አመሰግነዋለሁ። እረኛ የነበረው ዳዊት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው መዝሙሩ ላይ ያሰፈረው ሐሳብ በሕይወቴ ሲፈጸም አይቻለሁ፤ “[አምላክ] በዕረፍት ውሃ ዘንድ ይመራኛል፤ ነፍሴንም ይመልሳታል። ስለ ስሙም፣ በጽድቅ መንገድ ይመራኛል።”—መዝሙር 23:2, 3 *

^ စာပိုဒ်၊ 29 ማርዪያ ኪሊን ራሷ የተናገረችው የሕይወት ታሪኳ እየተጠናቀረ ሳለ መጋቢት 1 ቀን 2010 በሞት አንቀላፍታለች።