ኢየሱስ ጨው የጨውነት ጣዕሙን ሊያጣ እንደሚችል መናገሩ ስህተት ነበር?

ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ተከታዮቹን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ሆኖም ጨው የጨውነት ጣዕሙን ቢያጣ ጨውነቱን እንዴት መልሶ ሊያገኝ ይችላል? ከዚህ በኋላ ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ለምንም ነገር አያገለግልም።” (ማቴዎስ 5:13) ጨው፣ ምግብ ሳይበላሽ እንዲቆይ ለማድረግ የሚያስችል ማዕድን ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረው ተከታዮቹ ሌሎች በመንፈሳዊም ሆነ በሥነ ምግባር እንዳይበከሉ መጠበቅ እንደሚችሉ እና ይህን የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው ለመጠቆም መሆን አለበት።

በሙት ባሕር ዳርቻ ላይ የሚገኘው የጨው ክምችት

ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ ኢየሱስ ጨው የጨውነት ጣዕሙን ሊያጣ እንደሚችል የተናገረውን ሐሳብ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “በሙት ባሕር አካባቢ የሚገኘው አብዛኛው ጨው ከሌሎች ማዕድናት ጋር የተደባለቀ ነው፤ በመሆኑም ጨዉ ቢሟሟ የሚቀረው ነገር ከጨዉ ጋር ተደባልቀው የነበሩት ምንም ጣዕም የሌላቸው ማዕድናት ብቻ ይሆናሉ።” ኢየሱስ ጣዕሙን ያጣው ጨው ‘ወደ ውጭ ከመጣል በቀር ለምንም ነገር አያገለግልም’ ማለቱ የተገባ ነው የምንለው ከዚህ አንጻር ነው። ኢንሳይክሎፒዲያው አክሎ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ከሙት ባሕር የሚገኘው ጨው ከባሕር ከሚገኙ ሌሎች የጨው ዓይነቶች ጋር ሲወዳደር ጥራቱ ዝቅተኛ ቢሆንም ይህን ጨው በቀላሉ ከባሕሩ ዳርቻ መሰብሰብ ይቻል ነበር፤ በመሆኑም በፓለስቲና በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለው ይህ ዓይነቱ ጨው ነው።”

ኢየሱስ አንድ የብር ሳንቲም ስለጠፋባት ሴት የተናገረው ምሳሌ ለአድማጮቹ ምን ትርጉም ነበረው?

ድራክማ ሳንቲም

ኢየሱስ፣ አሥር የብር ሳንቲሞች ያሏት አንዲት ሴት አንዱ የብር ሳንቲም ሲጠፋባት መብራት አብርታ ቤቷን በደንብ በመጥረግ ሳንቲሙን እንደፈለገችው የሚገልጽ ምሳሌ ተናግሮ ነበር። (ሉቃስ 15:8-10) በኢየሱስ ዘመን አንድ የብር ሳንቲም (ድራክማ) አንድ ሰው ከሚያገኘው የቀን ደሞዝ ብዙም አያንስም ነበር፤ በመሆኑም በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደጠፋ የተገለጸው ሳንቲም ዋጋ ያን ያህል ትንሽ አልነበረም። ይሁንና ሳንቲሙን ተፈላጊ እንዲሆን ያደረገው ምክንያት ይህ ብቻ አልነበረም።

አንዳንድ የማመሳከሪያ ጽሑፎች እንደሚገልጹት ሴቶች ሳንቲሞችን እንደ ጌጥ ይጠቀሙባቸው ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው ሳንቲም ሴትየዋ ከቤተሰቦቿ በውርስ ያገኘችው ወይም በጥሎሽ የተሰጣት እንደ ውድ ንብረት የምትመለከተው ጌጥ ሊሆን ይችላል። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ ሴትየዋ የጠፋባትን የብር ሳንቲም ለመፈለግ ከፍተኛ ጥረት ማድረጓ አያስደንቅም።

በኢየሱስ ዘመን የነበሩት አብዛኞቹ ቤቶች ወደ ውስጥ የሚገባውን ብርሃንና ሙቀት በተቻለ መጠን ለመቀነስ እንዲያስችሉ ታስበው የተሠሩ ናቸው። እንዲሁም እነዚህ ቤቶች የሚኖሯቸው ጥቂት መስኮቶች ብቻ ነበር። የቤቶቹ ወለል ላይ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ጭድ ወይም የደረቀ አገዳ ይጎዘጎዝ ነበር። በመሆኑም ወለሉ ላይ የወደቀ ሳንቲም ፈልጎ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። አንድ ተንታኝ ይህን ጉዳይ አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፦ “እንደ ሳንቲም ያለ ትንሽ ነገር መሬት ላይ ቢወድቅ ዕቃውን ፈልጎ ለማግኘት የሚያስችለው ከሁሉ የተሻለው ዘዴ መብራት አብርቶ ቤቱን መጥረግ ነበር።”