በመላው ዓለም የሚገኙ ሁለት ቢሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች በየዓመቱ ታኅሣሥ 25 ቀን የገና በዓልን ያከብራሉ፤ ቁጥራቸው ከ200 ሚሊዮን የማያንስ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ይህንኑ በዓል ጥር 7 (እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ታኅሣሥ 29) ዕለት ያከብራሉ። የገና በዓልን ጨርሶ ማክበር የማይፈልጉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችም አሉ። እነዚህ ሰዎች በዓሉን የማያከብሩት ለምንድን ነው?

አንደኛው ምክንያት እነዚህ ሰዎች የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች አባላት አለመሆናቸው ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሰዎች የአይሁድ፣ የሂንዱ፣ የሺንቶ ወይም የሌላ እምነት ተከታዮች ሊሆኑ ይችላሉ። አምላክ መኖሩን የሚጠራጠሩ ወይም በአምላክ የማያምኑ ሌሎች ሰዎች ደግሞ የገና በዓል አፈ ታሪክ እንደሆነ ይሰማቸዋል።

የሚገርመው ነገር ግን፣ በኢየሱስ እንደሚያምኑ የሚናገሩ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል ሰዎችም እንኳ በገና በዓል ወቅት የሚከናወኑትን ልማዶች አይቀበሉም። ለምን? ቢያንስ አራት ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ።

በመጀመሪያ ደረጃ፣ እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ የተወለደው በታኅሣሥ ወይም በጥር ወር እንደሆነ አያምኑም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ የተወለደበትን ዕለት ለይቶ አይነግረንም። ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ በደፈናው ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “በዚያው አገር፣ ሌሊት ሜዳ ላይ መንጎቻቸውን ሲጠብቁ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ። በድንገት የይሖዋ መልአክ መጥቶ አጠገባቸው ቆመ፤ . . . መልአኩ . . . እንዲህ አላቸው፦ ‘. . . በዛሬው ዕለት በዳዊት ከተማ አዳኝ ተወልዶላችኋል፤ እሱም ጌታ ክርስቶስ ነው።’”—ሉቃስ 2:8-11

ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኢየሱስ የተወለደው እረኞች መንጎቻቸውን ይዘው ውጭ ማደር በሚችሉበት ወቅት ይኸውም በጥቅምት ወር መጀመሪያ አካባቢ ነው። በታኅሣሥ እና በጥር ወራት በቤተልሔም አቅራቢያ ባሉ አካባቢዎች ከፍተኛ ቅዝቃዜ አለ። በመሆኑም እረኞች መንጎቻቸውን ከሌሊቱ ቅዝቃዜ ለመጠበቅ የሚያሳድሯቸው በረት ውስጥ ነበር።

ሁለተኛው ምክንያት፦ ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲያከብሩ ያዘዘው ብቸኛ በዓል ልደቱ ሳይሆን የሞቱ መታሰቢያ ነው፤ የጥንት ተከታዮቹ ይህን በዓል ያከበሩት ቀላል የሆነ የኅብረት ማዕድ በመመገብ ነበር። (ሉቃስ 22:19, 20) ከዚህም በተጨማሪ ማርቆስና ዮሐንስ በጻፏቸው ወንጌሎች ላይ ስለ ኢየሱስ ልደት ምንም እንዳልተገለጸ ልብ ማለት ያስፈልጋል።

ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲያከብሩ ያዘዘው ብቸኛ በዓል ልደቱ ሳይሆን የሞቱ መታሰቢያ ነው

ሦስተኛው ምክንያት፦ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ልደት እንዳከበሩ የሚገልጽ ታሪካዊ መረጃ አናገኝም። እነዚህ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ያከብሩ እንደነበር ግን የታወቀ ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:23-26) ክርስቲያን ነን የሚሉ ሃይማኖቶች ታኅሣሥ 25 ቀን የገና በዓል እንዲከበር የደነገጉት ኢየሱስ ከተወለደ ከ300 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ነው። የሚገርመው ነገር በ17ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ የእንግሊዝ ፓርላማ በአገሪቱ የገና በዓል እንዳይከበር አዋጅ አውጥቶ ነበር። በዩናይትድ ስቴትስም የማሳቹሴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተመሳሳይ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር። ለምን? ዘ ባትል ፎር ክሪስማስ የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “የኢየሱስ ልደት ታኅሣሥ 25 እንደሆነ የሚያሳይ የመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የታሪክ ማስረጃ የለም።” ይኸው መጽሐፍ አክሎም ፒዩሪታኖች * ገና “ክርስቲያናዊ ልማድ እንዲመስል ተደርጎ የቀረበ የአረማውያን በዓል” እንደሆነ ያስቡ እንደነበር ገልጿል።

አራተኛውና የመጨረሻው ምክንያት፦ የበዓሉ አመጣጥ በራሱ ጥሩ አይደለም። የገና በዓል የመነጨው ሮማውያን የግብርና አምላክ ለሆነው ለሳተርንና ለፀሐይ አምላክ ለሶል ኢንቪክተስ ወይም ለሚትራ ያደርጓቸው ከነበሩት ክብረ በዓላት ነው። ክሪስትያን ራትሽ እና ክሎውድያ ሙዌልኤይብሊንግ የተባሉት የአንትሮፖሎጂ ባለሙያዎች በጻፉት ፓጋን ክሪስማስ በተሰኘው መጽሐፍ ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ አለ፦ “በቅድመ ክርስትና ዘመን እንደነበሩት ሌሎች በርካታ ልማዶችና እምነቶች ሁሉ፣ ፀሐይ በየዓመቱ መመለሷን በማሰብ ይደረግ የነበረው ጥንታዊ ክብረ በዓልም የኢየሱስ የልደት በዓል ተደርጎ መከበር ጀመረ።”

ከእነዚህ ምክንያቶች አንጻር እውነተኛ ክርስቲያኖች የገና በዓልን የማያከብሩት ለምን እንደሆነ አስተዋልክ?

^ စာပိုဒ်၊ 9 ፒዩሪታን የሚለው ስም በ16ኛው መቶ ዘመን የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን አባላት ለነበሩ ፕሮቴስታንቶች የተሰጠ ስያሜ ሲሆን እነዚህ ሰዎች ቤተ ክርስቲያናቸውን ከካቶሊክ ሃይማኖት ርዝራዦች ለማጥራት የተነሱ ነበሩ።