ሰኔ 14 ቀን 2007 የኢስቶኒያ ብሔራዊ ፖስታ ቤት በስተቀኝ በኩል የሚታየውን የመታሰቢያ ቴምብር አወጣ። ከቴምብሩ ጋር ተያይዞ የወጣው ማስታወቂያ “ይህ መታሰቢያ የተዘጋጀው የስታሊን መንግሥት በኢስቶኒያውያን ላይ ባካሄደው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ሰለባ የሆኑትን ሰዎች ለመዘከር ነው” ይላል። ከ1941 እስከ 1951 ባሉት ዓመታት በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢስቶኒያውያን ከአገራቸው በግዳጅ ተፈናቅለው ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ ተደርገዋል።

“ታሪክ አይዋሽም።” ይህ በኢስቶኒያ በጣም የተለመደ አባባል ሲሆን በሌሎች አገሮችም ከዚህ ጋር የሚመሳሰሉ አባባሎች አሉ። ታሪክን መለወጥ ባንችልም ትምህርት ልናገኝበት እንችላለን። የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “አንዱ በሌላው ላይ ገዥ የሚሆንበትን፣ ሌላው ደግሞ ተጨቍኖ የሚኖርበትን የዚህን ዓለም ሁኔታ” እንደተመለከተ ገልጿል።—መክብብ 8:9 የ1980 ትርጉም

ከተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በፊት በኢስቶኒያና በሌሎች የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች የተፈጸመው ነገር ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እውነት መሆኑን ያረጋግጣል። በእነዚህ አገራት የሚኖሩ በርካታ ንጹሐን ሰዎች ሩቅ ወደ ሆኑ ቦታዎች በግዳጅ ተወስደው እንዲሰፍሩ ተደርገዋል ወይም የጉልበት ሥራ በሚሠራባቸው ካምፖች ውስጥ ታስረዋል፤ የዚህ ሁሉ መከራና ሥቃይ መንስኤው ሰብዓዊ አገዛዝ ነው።

የኢስቶኒያ የታሪክ ምሁራን እንደሚገልጹት ከ1941 እስከ 1951 ባሉት ዓመታት ውስጥ በዚህች ትንሽ አገር የሚኖሩ ከ46,000 በላይ ሰላማውያን ሰዎች ተግዘዋል። አብዛኞቹ ይህ እርምጃ የተወሰደባቸው አንድን የፖለቲካ ቡድን በመደገፋቸው ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በዜግነታቸው ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ባላቸው ቦታ ምክንያት ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ግን ጥቃት የተሰነዘረባቸው በእምነታቸው ምክንያት ነው።

ፈሪሃ አምላክ ባላቸው ሰዎች ላይ የተፈጸመ ጥቃት

የታርቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ በ2004 ባወጣው ጥናት ላይ አይጂ ራሄ ታም የተባሉ የታሪክ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “ከ1948 እስከ 1951 ባሉት ዓመታት ውስጥ 72 የይሖዋ ምሥክሮችና አብረዋቸው የነበሩ ሌሎች ሰዎች ታስረዋል። ሚያዝያ 1 ቀን 1951 ግን በባልቲክ አገሮች ብቻ ሳይሆን በሞልዶቫ፣ በምዕራባዊ ዩክሬንና በቤላሩስ የሚገኙ በርካታ ሰዎችን ወደ ሌላ አካባቢ ማጋዝ ተጀመረ።”

ከ1951 በፊት በኢስቶኒያ ይኖሩ የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች ተይዘው ይታሰሩ፣ ሥነ ልቦናዊ ጫና ይደረግባቸው፣ ምርመራ ይካሄድባቸው እንዲሁም ወኅኒ እንዲወርዱ ይደረጉ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮችን ወደ ሌላ አካባቢ ለማጋዝ የተደረገው ዘመቻ ግን እነሱን ከኢስቶኒያ ጨርሶ ለማጥፋት የተደረገ ሴራ ሳይሆን አይቀርም።

ሚያዝያ 1 ቀን 1951 የሚለው ዕለት ከላይ በሚታየው ቴምብር ላይ ሰፍሯል። ቴምብሩ ላይ የሚታየው 382 የሚለው ቁጥር በዚያ ቀን የተጋዙትን የይሖዋ ምሥክሮችና የልጆቻቸውን ብዛት ያመለክታል። በግዞት  ከተወሰዱት መካከል የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ዘመዶቻቸውና ጎረቤቶቻቸውም ይገኙበታል። የዚያን ዕለት በመላ አገሪቱ አፈሳ ሲካሄድ ዋለ። ምሽት ላይ፣ የታፈሱት ሰዎች ወጣት አረጋዊ ሳይባል በእንስሳት መጫኛ ፉርጎ ውስጥ ታጉረው ወደ ሳይቤርያ በሚሄድ ባቡር ተሳፈሩ።

ኤላ ቱም

በዚህ ወቅት ከተጋዙት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል በወቅቱ የ25 ዓመት ወጣት የነበረችው ኤላ ቱም * ትገኝበታለች። በጊዜው የተለመደ የነበረውን የምርመራ ዘዴ በተመለከተ እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ወታደር በፍርሃት እንድርድ ለማድረግ የሞከረ ሲሆን መስበክ እንዳቆም አዘዘኝ። በአንድ ወቅት ‘መኖር ትፈልጊያለሽ ወይስ ከአምላክሽ ጋር ተጣብቀሽ በሳይቤርያ ምድረ በዳ መሞት ይሻልሻል?’ ሲል ጠየቀኝ።” ኤላ ግን በድፍረት ምሥራቹን መስበኳን ቀጠለች። በዚህም የተነሳ ወደ ሳይቤርያ የተጋዘች ሲሆን ለስድስት ዓመታት ያህል የጉልበት ሥራ ከሚሠራበት አንድ ካምፕ ወደ ሌላው ስትዘዋወር ቆይታለች።

ፍትሕ በጎደለው መንገድ ያለ ፍርድ ከተጋዙት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ሂሲ ለምበር የምትባል ወጣት የይሖዋ ምሥክር ትገኝ ነበር። ሂሲ ሚያዝያ 1 ቀን 1951 ስለተፈጸመው ሁኔታ ስታስታውስ እንዲህ ትላለች፦ “ምንም ሳናስበው በማታ ድንገት መጡና ‘ግማሽ ሰዓት ነው ያላችሁ። ጓዛችሁን ጠቅልሉ!’ አሉን።” ጨለማውን ተገን በማድረግ፣ ሂሲና የስድስት ዓመት ሴት ልጇ ወደ ባቡር ጣቢያ ተወሰዱ። ሲጥ ሲጥ የሚል ድምፅ እያሰማ የሚጓዘው አሮጌ ባቡር በየጣቢያው ተጨማሪ የይሖዋ ምሥክሮችን እየሰበሰበ ማዝገሙን ተያያዘው። ሂሲ እንዲህ ብላለች፦ “በእንስሳት መጫኛ ፉርጎ ውስጥ ታጎርን። የእንስሳቱ እዳሪ በረዶ መሆኑ በጀን እንጂ ሽታውን መቋቋም አንችልም ነበር። ልክ እንደ እንስሳት ተፋፍገን ተጫንን።”

ሁለት ሳምንት የፈጀው የባቡር ጉዞ በጣም አድካሚና አሰቃቂ ነበር። ፉርጎዎቹ በሰው ከመጨናነቃቸውም ሌላ ቆሻሻ ነበሩ። ወጣት አረጋዊ ሳይባል ሁሉም የሚያዋርድና ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ነገር ይፈጸምባቸው ነበር። አንዳንዶቹ ያለቅሱ የነበረ ሲሆን ምግብ አንበላም ያሉም ነበሩ። የይሖዋ ምሥክሮች ግን መንፈሳዊ መዝሙሮችን በመዘመር እርስ በርስ ይበረታቱ እንዲሁም ያላቸውን ምግብ ተካፍለው ይበሉ ነበር። እስረኞቹ የሚሄዱበት ቦታ “የዕድሜ ልክ መኖሪያቸው” እንደሚሆንና “መመለሻ እንደሌላቸው” ተነግሯቸው ነበር።

ሂሲ ለምበር እና ልጇ ማጃ

ሂሲ በዚህ የመከራ ጊዜ የእምነት ባልደረቦቿ ያደረጉላትን ልብ የሚነካ ነገር ታስታውሳለች። እንዲህ ብላለች፦ “አንድ የባቡር ጣቢያ ስንደርስ ባቡራችን ከሞልዶቫ ከመጣ ባቡር አጠገብ ቆመ። በዚህ ባቡር ውስጥ ያለ ሰው ማንነታችንና ወዴት እንደምንሄድ ጠየቀን። እኛም ከኢስቶኒያ የመጣን የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆንን እና የምንሄድበትን እንደማናውቅ ነገርነው። ከሞልዶቫ በመጣው በዚህ ባቡር ውስጥ የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች የተባባልነውን ሲሰሙ በፉርጎው ላይ በነበረ ቀዳዳ በኩል ትልቅ ዳቦና ፍራፍሬ ወረወሩልን።” ሂሲ በመቀጠል “የይሖዋ ምሥክሮች የተጋዙት ከተለያዩ አካባቢዎች ይኸውም ከመላው የሶቪየት ኅብረት ሪፑብሊኮች እንደሆነ የተገነዘብነው በዚህ ወቅት ነበር” ብላለች።

ኮሪና እና ኤነ የተባሉት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ከስድስት ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ከእናታቸው ተለያይተው ቆይተዋል። የይሖዋ ምሥክር የሆነችው እናታቸው ቀደም ሲል ታስራ የጉልበት ሥራ ወደሚሠራበት ካምፕ ተወስዳ ነበር። ሁለቱ ወጣቶች ደግሞ ብዙዎች በተጋዙበት ምሽት ከቤታቸው ተጎትተው በባቡር ውስጥ ታጎሩ። ኮሪና የተደረገላትን ውለታ በማስታወስ እንዲህ ትላለች፦ “በባቡሩ ላይ የነበረች ሁለት ልጆች ያሏት አንዲት የይሖዋ ምሥክር እንደምትንከባከበን እንዲሁም ከእሷና ከልጆቿ ጋር እንደ ቤተሰብ ሆነን መኖር እንደምንችል ነገረችን።”

ጉዟቸውን ሲያጠናቅቁ ምን ገጠማቸው? አጥንት የሚሰብር  ቅዝቃዜ ወዳለበት የሳይቤርያ ምድረ በዳ በደረሱ ማግስት ሰብዓዊ ክብርን የሚያዋርድ “የባሪያ ገበያ” ተጀመረ። በማሳቸው ላይ የሚሠሩ ሠራተኞችን ለመምረጥ ሲሉ ከአካባቢው የመንግሥት እርሻዎች የመጡ ሰዎች ነበሩ። ኮሪና እንዲህ ትላለች፦ “ሰዎቹ እርስ በርስ ሲነታረኩ እንሰማ ነበር፤ ‘አንተ ለትራክተርህ ነጂ አግኝተሃል። ይሄኛውን የምወስደው እኔ ነኝ’ ወይም ‘እኔ ሁለት አረጋውያን ደርሰውኛል። አንተም አረጋውያን መውሰድ አለብህ’ ይባባሉ ነበር።”

ኤነ እና እህቷ ኮሪና

ኮሪናና ኤነ ደፋሮች ነበሩ። “እናታችን በጣም ትናፍቀን ነበር፤ እንደገና በእሷ እቅፍ ውስጥ ለመግባት እጅግ እንመኝ ነበር” በማለት ከጊዜ በኋላ ተናግረዋል። ያም ቢሆን በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆነው የቀጠሉ ሲሆን ደስታቸውንም አላጡም። ኮሪና አክላ እንዲህ ብላለች፦ “የሚያሞቅ ልብስ ሳንለብስ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ባለበት ሁኔታ እንድንሠራ የምንገደድበት ጊዜ ስለነበር በአንድ በኩል ሳስበው እናታችን ከእኛ ጋር አለመሆኗ ጥሩ ነበር።”

በኢስቶኒያም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ ንጹሐን ሰዎች ከፍተኛ ግፍ እንደተፈጸመባቸው አሌ የማይባል ሐቅ ነው፤ ከእነዚህ መካከል የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ። (“ለመገመት የሚያዳግት ‘የሽብር ማዕበል’” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በኢስቶኒያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በቀደሙት ዘመናት ይህ ሁሉ ግፍ ቢደርስባቸውም ዛሬም ሥራቸውን በደስታ ያከናውናሉ።

ብሩሕ ተስፋ አለን

ይሖዋ አምላክ ግፍን እንደሚጠላ መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል። “ይህን የሚያደርግ ሁሉ ክፋትንም የሚያደርግ ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነው” ይላል። (ዘዳግም 25:16 የ1954 ትርጉም) አምላክ በቀደሙት ዘመናት የክፋት ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን ቢታገሥም በቅርቡ ግፍንና ክፋትን ያስወግዳል። መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል፦ “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታስስ አታገኘውም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።”—መዝሙር 37:10, 11

አዎ፣ ወደፊት ብሩሕ የሆነ ጊዜ ይጠብቀናል! ያለፉትን ነገሮች መለወጥ ባንችልም የወደፊት ሕይወታችንን አስተማማኝ ለማድረግ የሚያስችል እርምጃ መውሰድ እንችላለን። ወደ አምላክ በመቅረብ እውነተኛ ጽድቅ በሚሰፍንበት ዓለም ውስጥ አስደሳች ሕይወት መምራት ስለምትችልበት መንገድ ተማር።—ኢሳይያስ 11:9

^ စာပိုဒ်၊ 10 የኤላ ቱም የሕይወት ታሪክ በሚያዝያ 2006 ንቁ! ከገጽ 20-24 ላይ ወጥቷል።