በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

  ከአምላክ ቃል ተማር

አምላክ መላውን ምድር የሚያስተዳድር አንድ መንግሥት ያቋቁማል?

አምላክ መላውን ምድር የሚያስተዳድር አንድ መንግሥት ያቋቁማል?

ይህ ርዕስ በአእምሮህ ሊመላለሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን በማንሳት መልሶቹን መጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ የት ቦታ ላይ ማግኘት እንደምትችል ይጠቁምሃል። የይሖዋ ምሥክሮች ለጥያቄዎቹ በተሰጡት መልሶች ላይ ከአንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኞች ናቸው።

1. የሰው ዘር መላውን ምድር የሚያስተዳድር አንድ መንግሥት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

በዘመናችን የሰው ዘር የሚያጋጥሙት አብዛኞቹ ችግሮች ዓለም አቀፋዊ ይዘት አላቸው። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ አብዛኞቹ ሰዎች በድህነትና በጭቆና ቀንበር ሥር ለመኖር ተገድደዋል። በሌሎች አገሮች ውስጥ የሚገኙ ብዙ ሰዎች ደግሞ በቅንጦት ተንደላቅቀው ይኖራሉ። የምድራችን ሀብት ለሁሉም እኩል እንዲዳረስ የሚያደርግ ዓለም አቀፋዊ የሆነ መስተዳድር የግድ ያስፈልጋል።—መክብብ 4:1ን እና 8:9ን አንብብ።

2. ዓለምን ለማስተዳደር ብቃቱ ያለው ማን ነው?

ከሰዎች መካከል ዓለምን ለማስተዳደር ብቃቱ ያለው ማንም የለም፤ በመሆኑም ብዙዎች፣ ዓለማችን በአንድ ገዥ መተዳደር አለባት የሚለው ሐሳብ አይዋጥላቸውም። በሁሉም ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የሚችል ሰው የለም። ከዚህም ሌላ፣ ሥልጣን የማያሳውረው ሰው እንዴት ሊኖር ይችላል? አንድ አምባገነን መሪ መላውን የሰው ዘር ያስተዳድር የሚለው ሐሳብ ጨርሶ ለመቀበል የሚከብድ ነገር ነው።—ምሳሌ 29:2ን እና ኤርምያስ 10:23ን አንብብ።

ይሖዋ አምላክ፣ የሰውን ዘር ለዘላለም እንዲያስተዳድር ልጁን ኢየሱስን መርጦታል። (ሉቃስ 1:32, 33) ኢየሱስ በምድር ላይ ኖሯል። በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የታመሙትን ይፈውስ፣ ቅን የሆኑ ሰዎችን ያስተምር እንዲሁም ከልጆች ጋር ጊዜ ያሳልፍ ነበር። (ማርቆስ 1:40-42፤ 6:34፤ 10:13-16) በመሆኑም ኢየሱስ ብቃት ያለው መሪ ነው።—ዮሐንስ 1:14ን አንብብ።

 3. መላውን ምድር የሚያስተዳድር አንድ መንግሥት ማቋቋም ይቻላል?

አምላክ፣ ከሰማይ ሆኖ ምድርን እንዲያስተዳድር ልጁን ሾሞታል። (ዳንኤል 7:13, 14) አንድ ሰብዓዊ መሪ ተገዥዎቹን ለማስተዳደር በግዛቱ ሥር ባሉ ከተሞች በሙሉ እንዲገኝ አይጠበቅበትም፤ በተመሳሳይም ኢየሱስ የሰውን ዘር ለማስተዳደር በምድር ላይ በአካል መገኘት አያስፈልገውም።—ማቴዎስ 8:5-9, 13ን አንብብ።

ሁሉም ሰዎች ለኢየሱስ ለመገዛት ፈቃደኞች ይሆናሉ? አይሆኑም። ኢየሱስን ንጉሣቸው አድርገው የሚቀበሉት መልካም የሆነውን ነገር የሚወዱ ሰዎች ብቻ ናቸው። ይሖዋ፣ እሱ የሾመውን አፍቃሪና ጻድቅ ንጉሥ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎችን ከምድር ላይ ያስወግዳቸዋል።—ማቴዎስ 25:31-33, 46ን አንብብ።

4. ዓለምን የሚያስተዳድረው ገዥ ወደፊት ምን ያከናውናል?

እረኛ በጎቹን እንደሚሰበስብ ሁሉ ኢየሱስም ቅን የሆኑ ሰዎችን ከሁሉም ብሔራት እየሰበሰበ ነው፤ እንዲሁም እነዚህን ሰዎች ስለ አምላክ ፍቅራዊ መንገዶች እያስተማራቸው ነው። (ዮሐንስ 10:16፤ 13:34) እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን እና አገዛዙን በቅንዓት ይደግፋሉ። (መዝሙር 72:8፤ ማቴዎስ 4:19, 20) በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የኢየሱስ ታማኝ ተገዥዎች ኢየሱስ ንጉሥ እንደሆነ በኅብረት እያወጁ ነው።—ማቴዎስ 24:14ን አንብብ።

ኢየሱስ በሥልጣኑ በመጠቀም በቅርቡ የሰውን ዘር ብልሹ ከሆኑ መንግሥታት አገዛዝ ነፃ ያወጣዋል። ኢየሱስ በምድር ላይ እንዲነግሡ ከታማኝ ተከታዮቹ መካከል አንዳንድ ሰዎችን የመረጠ ሲሆን እነዚህ ሰዎች ከእሱ ጋር በሰማይ ሆነው ምድርን ያስተዳድራሉ። (ዳንኤል 2:44፤ 7:27) የኢየሱስ መንግሥት፣ ምድር ይሖዋን በማወቅ እንድትሞላ ያደርጋል፤ እንዲሁም በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ የጠፋው ገነት እንደገና በምድር ላይ እንዲቋቋም ያደርጋል።—ኢሳይያስ 11:3, 9ን እና ማቴዎስ 19:28ን አንብብ።