በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ጥቅምት 2012

ሙስና በተስፋፋበት ዓለም ውስጥ ሐቀኛ መሆን ይቻላል?

ሙስና በተስፋፋበት ዓለም ውስጥ ሐቀኛ መሆን ይቻላል?

“በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር [እንመኛለን።]”—ዕብራውያን 13:18

የወረስነው ኃጢአት፣ የምንኖርበት ዓለም እንዲሁም ዲያብሎስ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩብን ቢሆንም ተጽዕኖውን መቋቋም እንችላለን! እንዴት? ወደ አምላክ በመቅረብና በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ጊዜ የማይሽራቸው መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ነው። እስቲ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የዚህን ሥርዓት የአኗኗር ዘይቤ መኮረጅ አቁሙ።”—ሮም 12:2

“መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሐቀኛ መሆን የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች እንድገነዘብ ረድቶኛል።”—ጊልዬርም

እውነተኛ ታሪክ፦ በብራዚል የሚኖረው ጊልዬርም በንግድ ሥራ ላይ የተሠማራ ሲሆን በሙያው ስኬታማ ነው። ጊልዬርም ሐቀኛ ሆኖ መሥራት ቀላል እንዳልሆነ ይናገራል። እንዲህ ብሏል፦ “በንግድ ሙያ ላይ የተሠማራ ሰው ሳያስበው ሐቀኝነት የጎደላቸው ድርጊቶች መፈጸም ሊጀምር ይችላል፤ ግለሰቡ ይህን የሚያደርገው የሚሠራበት ድርጅት ያወጣቸው ግቦች ላይ ለመድረስ ወይም ከውድድር ላለመውጣት ሲል ሊሆን ይችላል።” ጊልዬርም አክሎም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ብዙ ሰዎች ጉቦ መስጠትም ሆነ መቀበል ችግር እንዳለው አይሰማቸውም።  ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አፍስሰህ ሥራ በምትጀምርበት ጊዜ ብዙ ወጪዎች ስለሚኖሩህ በሐቀኝነት መሥራት ተፈታታኝ ይሆንብሃል።”

ያም ቢሆን ግን ጊልዬርም ሐቀኝነቱን እንዲያጎድል የሚደርስበትን ጫና መቋቋም ችሏል። እንዲህ ብሏል፦ “የንግድ ሰዎች አንዳንድ ሕጎችን መጣሳቸው እንደ ስህተት በማይቆጠርበት ዓለም ውስጥም ቢሆን ሐቀኛ ሆኖ መሥራት ይቻላል። በእርግጥ ይህን ለማድረግ ጠንካራ የሥነ ምግባር አቋም ሊኖርህ ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሐቀኛ መሆን የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች እንድገነዘብ ረድቶኛል። ሐቀኛ የሆነ ሰው ንጹሕ ሕሊና እና ውስጣዊ ሰላም ያለው ከመሆኑም ሌላ ለራሱ አክብሮት ይኖረዋል። እንዲህ ያለው ሰው በሌሎችም ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል።”

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሱ ፈተናና ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ፤ እንዲሁም ሰዎችን ጥፋትና ብልሽት ውስጥ በሚዘፍቁ ከንቱና ጎጂ በሆኑ ብዙ ምኞቶች ይያዛሉ። ምክንያቱም የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነው።”—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10

“በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን የላቁ የሥነ ምግባር መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረጌ ጥሩ ስም ስላተረፈልኝ ደስተኛ ነኝ።”—አንድሬ

እውነተኛ ታሪክ፦ አንድሬ፣ ከጥበቃና ከደኅንነት ጋር የተያያዙ መሣሪያዎችን የሚገጥም ድርጅት ባለቤት ነው። ከደንበኞቹ መካከል አንድ ትልቅ የእግር ኳስ ክለብ ይገኝበታል። በአንድ ወቅት፣ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ግጥሚያ ከተካሄደ በኋላ አንድሬ ለክለቡ ለሰጠው አገልግሎት ክፍያ ለመቀበል የአስተዳደር ቢሮዎች ወደሚገኙበት አካባቢ ሄደ። የገንዘብ ክፍሉ ሠራተኞች ከትኬት ሽያጭ የተሰበሰበውን ገቢ እየቆጠሩ ስለነበር በሥራ ተወጥረዋል። የክፍሉ ኃላፊ እየተጣደፈ ስለነበር አንድሬን ጨምሮ አገልግሎት ለሰጡት ሌሎች ሰዎች ገንዘባቸው በችኮላ ከፍሎ አሰናበታቸው።

አንድሬ እንዲህ ይላል፦ “ወደ ቤት እየሄድኩ ሳለ የገንዘብ ክፍሉ ኃላፊ ትርፍ ገንዘብ እንደሰጠኝ ተገነዘብኩ። ሰውየው ተጨማሪ ገንዘብ የሰጠው ለማን እንደሆነ ማወቅ እንደማይችል ተሰምቶኝ ነበር። ሆኖም ያ ምስኪን ሰው የጎደለውን ገንዘብ ከገዛ ኪሱ መተካት እንደሚኖርበት ግልጽ ነው። ስለዚህ ወደ ሰውየው ተመልሼ ለመሄድ ወሰንኩ። ደጋፊዎች አካባቢውን ቢያጨናንቁትም እንደምንም አልፌ ወደ ሰውየው በመሄድ ገንዘቡን መለስኩለት። ኃላፊው በዚህ በጣም ተገረመ። ከዚያ ቀደም ማንም ሰው የወሰደውን ትርፍ ገንዘብ መልሶለት አያውቅም።”

አንድሬ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “በዚያ ወቅት ሐቀኛ መሆኔ በኃላፊው ዘንድ አክብሮት እንዳተርፍ አድርጎኛል። ይህ ሁኔታ ካጋጠመኝ በርካታ ዓመታት ያለፉ ሲሆን መጀመሪያ ላይ ለክለቡ አገልግሎት ይሰጡ ከነበሩት ድርጅቶች መካከል እስከ አሁን የቀጠልኩት እኔ ብቻ ነኝ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን የላቁ የሥነ ምግባር መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረጌ ጥሩ ስም ስላተረፈልኝ ደስተኛ ነኝ።”

ጎጂ ተጽዕኖዎችን በአምላክ እርዳታ መቋቋም እንደምንችል ማወቁ የሚያበረታታ ነው። ያም ቢሆን ግን ሰዎች በግለሰብ ደረጃ የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ ሙስናን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አይችሉም። ሙስና በጣም ሥር የሰደደ ችግር ከመሆኑ የተነሳ ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች መንስኤዎቹን በራሳቸው ጥረት ሊያስወግዱ አይችሉም። ይህ ሲባል ታዲያ ሙስና ጨርሶ ሊወገድ አይችልም ማለት ነው? የእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች የመጨረሻ ክፍል መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ የሚሰጠውን የሚያበረታታ ሐሳብ ያብራራል።